ፈር ቀዳጅ ነው የተባለው የአልዛይመር መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Empics
በአልዛይመር ምክንያት አንጎል ላይ ሚደርሰውን ጉዳት እንዲዘገይ የሚያደርገው የመጀመሪያው መድኃኒት ጠቃሚ እና ታሪካዊ ነው ተባለ።
የምርምር ግኝቱ የተለመደውን የመርሳት በሽታ ለመከላከል የተደረገውን የአስር ዓመታት ስኬት አልባ ጉዞን ያበቃ እና አዲስ ዘመንን ያሳየ ተብሏል።
ለኬንማብ የተሰኘው ይህ መድኃኒት አነስተኛ ውጤት ሲኖረው፣ በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ያለው ተጽዕኖ አከራካሪ ሆኗል።
መድኃኒቱ የሚሠራው በሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እያለ በመሆኑ በዚህ ወቅት በርካታ ሰዎች በሽታውን እንዳለባቸው ለመለየት ስለሚቸገሩ የመጠቀም ዕድሉ ሊያመልጣቸው ይችላል ተብሏል።
ለኬንማብ የአልዛይመርስ ህመም ባለባቸው ሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚፈጠረውን ቤታ አሚሎይድ ያጠቃል።
ለአንዳንዶች እነዚህ የሙከራ ውጤቶች ዜና እንደ ድል እና የአዲስ ምዕራፍ ማስጀመሪያ ተደርገው ተወስደዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የአልዛይመር ምርምር ማዕከል ግኝቶቹን “አበረታች” ብሎታል።
ከ30 ዓመታት በላይ አሚሎይድን ታሳቢ በማድረግ ሲመራመሩ ከቆዩ ተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ሃርዲ “ታሪካዊ” ብለውታል።
አክለውም “የአልዛይመር ሕክምናዎችን ጅማሬን እያየን ነው” ብለዋል። የኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ታራ ስፒረስ-ጆንስ ደግሞ “ለረዥም ጊዜ 100 በመቶ ውድቀት ስላጋጠመን ውጤቱ ትልቅ ነው” ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የአልዛይመር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ምልክቶቹን ለመቆጣጠር የሚረዱ ሌሎች መድኃኒቶች ይሰጣቸዋል። ነገር ግን አንዳቸውም የበሽታውን ሂደት አይለውጡትም።
ልክ ሰውነት ቫይረሶችን ወይም ባክቴሪያዎችን እንደሚያጠቃው ለኬንማብም-አሚሎይድን ከአንጎል ውስጥ እንዲያጸዳ ተደርጎ የተነደፈ ነው።
አሚሎይድ በአንጎል ነርቭ ሴሎች መካከል ባለው ክፍተት ውስጥ የሚከማች እና የአልዛይመር መለያ የሆኑ ልዩ ግድግዳዎችን የሚፈጥር ፕሮቲን ነው።
መጠነ ሰፊ ሙከራው 1,795 የአልዛይመር በሽታ ያለባቸውን በጎ ፈቃደኞች አሳትፏል። በየሁለት ሳምንቱ የሌካነማብ መርፌዎች ይወጉ ነበር።
በሳን ፍራንሲስኮ በአልዛይመር በሽታ ክሊኒካዊ ሙከራዎች ላይ የቀረበው እና በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲስን ላይ የታተመው ውጤት የሚያሳየው መድኃኒቱ ፍጹም ፈውስ የሚሰጥ አይደለም።
በሽታው የሰዎችን የአዕምሮ ኃይል መቀማቱን ቢቀጥልም ህክምናው በተጀመረ በ18 ወራት ውስጥ ዕድገቱ በአንድ አራተኛ ያህል ቀንሷል።
መረጃውን በአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች እየተገመገመ ነው። በቅርቡም ለኬንማብ በሰፊው ለሕዝብ ጥቅም ስለመፈቀዱ ይወስናሉ። መድኃኒቱን የሠሩት ኤሳይ እና ባዮጂን የተባሉት ኩባንያዎች በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት በሌሎች አገሮች የማጽደቅ ሂደቱን ለመጀመር አቅደዋል።
ለውጥ ያመጣል?
በሳይንቲስቶች እና በዶክተሮች መካከል ለኬንማብ “በእውነተኛው ዓለም” ስላለው ተጽዕኖ ክርክር አለ።
የሰዎችን የሕመም ምልክቶች ደረጃ በመጠቀም የመድኃኒቱ ቀስ በቀስ ተጽዕኖው መቀነሱ ተስተውሏል።
ፕሮፌሰር ስፓይረስ-ጆንስ በሽታው ላይ “ትንሽ ተፅዕኖ” እና “አስደናቂ እንኳን ባይሆንም እኔ እወስደዋለሁ” ብለዋል።
የአልዛይመርስ ሪሰርች ዩኬ ባልደረባ ሆኑት ዶ/ር ሱዛን ኮልሃስ ደግሞ “መጠነኛ የሆነ ውጤት ነው...ነገር ግን ትንሽ እፎይታ ይሰጠናል” ብለዋል። ቀጣዩ የመድኃኒቱ ዕድገት የተሻለ እንደሚሆንም ተናግሯል።
አብረው የሚመጡ አደጋዎችም አሉ። የአንጎል ስካን በማድረግ የአንጎል ደም መፍሰስ (17 በመቶ ተሳታፊዎች ላይ) እና የአንጎል እብጠት (13 በመቶ ተሳታፊዎች ላይ) የመፈጠር ስጋት አሳይቷል።
በአጠቃላይ መድኃኒቱ ከተሰጣቸው ሰዎች ውስጥ 7 በመቶ የሚሆኑት የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላጋጠማቸው ሙከራውን ማቆም ነበረባቸው።
ወሳኙ ጥያቄ ከሙከራ 18 ወራት በኋላ ምን እንደሚከሰት ነው። አሁንም ያሉት መልሶች መላምቶች ናቸው።












