በአሜሪካ የጽዳት ሠራተኛው ኤሌክትሪክ በማቋረጡ ወሳኝ የምርምር ናሙናዎችን ከጥቅም ውጪ አደረገ

በአሜሪካ አንድ የጽዳት ሠራተኛ እጅግ ውድ የምርምር ናሙናዎች የተቀመጡበትን የቤተ ሙከራ ማቀዝቀዣ የኤሌክትሪክ ኃይል በማጥፋቱ ከፍተኛ ውጤት ያስገኛሉ የተባሉ የምርምር ሥራዎች ከጥቅም ውጪ ሆኑ።

ማቀዝቀዣው “ታላቅ ዕመርታን” ያስገኛሉ የተባሉ እና ለአስርታት የተከማቹ እጅግ ተፈላጊ የምርምር ናሙናዎች ተቀምጠውበት የነበረ ሲሆን፣ የጽዳት ሠራተኛው ማቀዝቀዣው የሚያወጣውን “የሚረብሽ” ድምጽ ለማስቆም ሲል ነበር እንዲጠፋ ያደረገው።

ምንም እንኳን የማቀዝቀዣውን ድምጽ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚያስረዳ ምልክት ቢኖረውም፣ ከንባብ ስህተት የተነሳ የሚያገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቆረጥ በመደረጉ ናሙናዎቹ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

በፍሪጁ ውስጥ ከዜሮ በታች በ80 ሴሊሺየስ እንዲቀመጡ የተደረጉት ናሙናዎች “በማያገለግሉበት ሁኔታ” ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። ይህም አንድ ሚሊየን ዶላር የሚገመት ጉዳት እንደሆነ የላብራቶሪው ጠበቃ አሳውቀዋል።

ጉዳት ያጋጠመው ቤተ ሙከራ ባለቤት የሆነው ትምህርት ቤት፣ የጽዳት ሠራተኛውን የቀጠረው የጽዳት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በአግባቡ ሥልጠና አልሰጠም በሚል ከሶታል።

በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ ውስጥ የሚገኘው ሬንሴለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲቲዩት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ለጽዳት ድርጅቱ ሥራውን እንዲያከናውንለት ኮንትራት የሰጠው።

የፀሐይ ኃይልን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር በሚያስችለው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ታላቅ ዕመርታን ያስገኛል የተባለው እና በአንድ ታዋቂ ፕሮፌሰር የሚመራው የፎቶሴንቴሲስ ምርምር በማቀዝቀዣው ምክንያት እክል እንደገጠመው የኢንስቲቲዩቱ ጠበቃ ገልጸዋል።

ፍሪጁ የሚያስፈልገው ጥገና እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ የሚያገኘው ኃይል እንዳይቋረጥ የሚያሳስብ ማስታወቂያ በበሩ ላይ ተለጥፎለት የነበረ ቢሆንም የጽዳት ሠራተኛው መመሪያውን ሳይከተል ቀርቷል።

“ይህ ማቀዝቀዣ ድምጽ የሚያሰማው በጥገና ላይ ስለሆነ ነው። እባክዎ ማቀዝቀዣውን አያንቀሳቅሱት ወይም ሶኬቱን አይንቀሉት።በእዚህ አካባቢ ምንም አይነት የጽዳት ሥራ ማከናወን አያስፈልግም።

የሚያሰማውን ድምጽ ለማስቆም የደወል ቁልፉን ከ5 እስከ 10 ሰከንዶች በመጫን ድምጹን ማጥፋት ይችላሉ” የሚል የጽሑፍ ማሳሰቢያ ተጽፎ ነበር።

ነገር ግን ማቀዝቀዣው ድምጽ ማሰማት ከጀመረ ከቀናት በኋላ፣ የጽዳት ሠራተኛው በምን ምክንያት እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ የተቀመጠውን መመሪያ ከመከተል ይልቅ ፍሪጁ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኝበትን መስመር በማጥፋት እንዲቋረጥ አድርጎታል።

በዚህ ምክንያትም በፍሪጁ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ተጠብቀው የቆዩ እና ከዜሮ በታች በ80 ሴለሊሺየስ ወይም 112 ፋራናይት ቅዝቃዜ ውስጥ የተቀመጡ ናሙናዎች “ለብልሽት ተጋልጠዋል፣ ተበላሽተዋል እንዲሁም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል” በማለት ተቋሙ ክስ አቅርቧል።

ተመራማሪዎች ማቀዝቀዣው የሚያገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ባወቁበት ጊዜ የፍሪጁ የሙቀት መጠን ከዜሮ በላይ ወደ 50 ሴሊሺየስ (122 ፋራናይት) ደርሶ ነበር። ይህም በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ስፍራ ላይ መቀመጥ የነበረባቸው ናሙናዎች ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ጉዳዩን የያዙት ጠበቃ ሚካኤል ጊንስበርግ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት፣ “የሚረብሸውን ድምጽ” ሰምቶ የኤሌክትሪክ ኃይሉን ያቋረጠው የጽዳት ሠራተኛ “ድምጹን ማስቆሙን እንጂ ምንም ጉዳት የሚያደርስ ነገር አለመፈጸሙን እንደሚያምን” ባናገሩት ጊዜ ገልጾላቸዋል።

የሬንሴለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲቲዩት የሕግ ቡድን አባላት የጽዳት ሠራተኛውን የቀጠረው የጽዳት አገልግሎት ሰጪው ድርጅት ሠራተኞቹን በተገቢው ሁኔታ ሥልጠና አልሰጠም በማለት ከሰዋል።

የጽዳት አገልግሎት ሰጪው ድርጅቱ ስለደረሰው ጉዳት እና ስለቀረበበት ክስ እስካሁን ያለው ነገር የለም።