ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን የምርጫ ውጤትን አልቀበልም ማለት “ወደ ትርምስ” ሊወስድ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ሚድ-ተርም ወይም የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የዕጩዎች “ሽንፈትን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን” አገሪቷን ወደ ትርምስ ጎዳና ሊወስድ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንት ባይደን፣ ባለፈው ዓመት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የ2020 ምርጫን ውጤት ለመቀልበስ ጥቃት ካደረሱበት ካፒቶል ሂል አቅራቢያ በሚገኘው በዋሽንግተን ዲሲ ዩኒየን ስቴሽን ሆነው ረቡዕ ምሽት በሰጡትና በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው፣ ከአምስት ቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ አሜሪካውያን ፖለቲካዊ ግጭቶችን ለመቃወም በጋራ እንዲቆሙም አሳስበዋል።
ዲሞክራት የሆኑት ባይደን የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና ደጋፊዎቻቸው “የሴራ እና የክፋት መረጃዎችን እያሰራጩ ነው” ብለዋል።
ሪፐብሊካኖች በበኩላቸው ባይደን “ለመከፋፈል እና አቅጣጫ ለማስለወጥ እየፈለጉ ነው" ሲሉ ክሱን አጣጥለውታል።
የሁለቱ የኮንግረስ ምክር ቤቶች እና ቁልፍ የግዛት አስተዳደሮች ማን ይቆጣጠራል የሚለው በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ምርጫ ይወሰናል።
በርካታ ትንበያዎች ሪፐብሊካኖች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለመቆጣጠር እንደሚያሸንፉ አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው በስም ያልጠቀሷቸውን ነገር ግን የተሸነፉት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሲሉ የጠሯቸውን [ዶናልድ ትራምፕ] የተወሰኑ የሪፐብሊካን ዕጩዎችን በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ምርጫ ከተሸነፉ ውጤቱን እንዳይቀበሉ እያነሳሱ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋል።
“ይህ ደግሞ ወደ ትርምስ የሚወስድ ነው። ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ፣ ሕገ ወጥ እና የአሜሪካውያን መገለጫ ያልሆነ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የትራምፕን የምርጫ ንግግር፣ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ላይ ከደረሰው የመዶሻ ጥቃት ጋር አገናኝተውታል።
የትራምፕ የ2020ው ምርጫ ተሰርቋል የሚል ትልቅ ውሸት፣ በ82 ዓመቱ ፓል ፔሎሲ ላይ ለደረሰው ጥቃት እና በካፒቶል ሂል ለተፈጠረው ግርግር መንስኤ እንደሆነም ፕሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።
“ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የታየውን ፖለቲካዊ አመጽ እና መራጮች የማስፈራራት ድርጊትን ያባባሰው ውሸት ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን።
በመሆኑም በምርጫ ሣጥኖች አቅራቢያ መራጮችን በማንገላታት በተከሰሱትና አንዳንድ ጊዜ የታጠቁ ወይም የስፖርት ልብስ የለበሱ የትራምፕ ደጋፊዎች ላይ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጡ ፕሬዝዳንቱ ከአሪዞና የፌደራል ዳኛ ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ያሰራጨውና ለሕግ አስከባሪ ተቋማት በአገር ውስጥ የሚታይ ጽንፈኝነት “የተጠናከረ ስጋት” እንዳለ የሚያስጠነቅቅ ማስታወቂያ፣ ዕጩዎች እና የምርጫ ሠራተኞች “የርዕዮተ ዓለም ቁጣ ባላቸው ግለሰቦች ሊጠቁ ይችላሉ” ብሏል።
የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ ሪፐብሊካኖች “ባይደን ካላቸው አነስተኛ የሕዝብ ተቀባይነትና በአሜሪካ ካለው የዋጋ ግሽበት አሜሪካውያንን ለማዘናጋት የተደረገ ሙከራ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
ቁንጮ ከሆኑ ሪፐብሊካኖች መካከል አንዱ የሆኑት ኬቪን ማካርቲ ምርጫውን ካሸነፉ የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንደሚሆኑ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
“ፕሬዚደንት ባይደን አሜሪካውያን አንድ ለመሆን በሚፈልጉበት ወቅት ለመከፋፈል እና ለማጋጨት እየሞከረ ነው። ምክንያቱም የኑሮ ውድነቱን ሊያሻሽል ስለሚችለው ፖሊሲያቸው አያወሩም። አሜሪካውያንም ይህንን አይቀበሉትም” ብለዋል።
ሮይተርስ በዚህ ሳምንት በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት፣ ግማሽ የሚሆኑ አሜሪካውያን ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ክስተቶች እምብዛም ቢሆኑም የምርጫ መጭበርበር ሰፊ ችግር እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
እንደ ቢቢሲ የአሜሪካው አጋር ሲቢኤስ ከሆነ ደግሞ፣ ግዛት ለማስተዳደር ከሚወዳደሩት 595 ሪፐብሊካኖች ከግማሽ በላይ ማለትም 306 የሚሆኑት በ2020ው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ጥርጣሬ አላቸው።