በጣሊያን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማውገዝ በአስር ሺዎች ወደ አደባባይ ወጡ

በጣሊያን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማውገዝ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን በአደባባይ አሰሙ።

ለዚህ የአደባባይ ተቃውሞ መነሻ የሆነው ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንዲት የዩኒቨርስቲ ተማሪ መገደሏ ነው።

ጁሊያ ሴቸቲን ልትመረቅ ቀናት ሲቀራት በቀድሞ ፍቅረኛዋ መገደሏ ተነግሯል።

በጣሊያን ከተሞች ሚላን እና ኔፕልስ በርካታ ሕዝብ የተሰበሰበ ሲሆን በተለይም በመዲናዋ ሮም ከፍተኛ መጨናነቅ ተፈጥሮ መተላለፊያ አልነበረም ተብሏል።

የጣሊያን ፕሬዚዳንት የሴቶችን ግድያ በዝምታ ሊታለፍ አይገባም ብለዋል።

“እንዲህ አይነት አስደንጋጭ ዜናዎች የሕዝቡን ህሊና አንቀጥቅጠውታል” ሲሉም ሰርጂዮ ማታሬላ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምትታሰበው ዕለት ተናግረዋል።

“ስልጣኔን የሚሻ ሕዝብ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ተከታታይ ጥቃቶችን እና ግድያዎች ሊቀበል አይችልም። ዝም ብሎ ሊያይ አይገባም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የማኅበረሰቡ ውድቀት ማሳያ ነው ብለዋል።

የጣሊያን የአገር ውስጥ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት እስካሁን 106 ሴቶች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 55ቱ በትዳር አጋር ወይም በቀድሞ የፍቅር አጋር የተፈጸሙ ናቸው።

በተለይም ከፖዱዋ ዩኒቨርስቲ ልትመረቅ ቀናት ሲቀራት የተገደለችው የ22 ዓመቷ የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ጁሊያ በርካቶችን አስቆጥቷል።

የጁሊያ አባት ጂኖ ሴቸቲን በፓዱዋ ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ለተማሪዎች ንግግር ያደረጉ ሲሆን ልጃቸውን ለማሰብ እንዲሁም በጥቃቶች ሰለባ ለሆኑ ሴቶች በዩኒቨርስቲው ግቢ የተሰራውን የመታሰቢያ ቀይ አግዳሚ ወንበርም መርቀዋል።

“ጂሊያን የሚመልሳት ምንም ነገር የለም፤ ነገር ግን ሞቷ መነሳሳቶችን እንዲያመጣ እፈልጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።

ጁሊያ ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር የጠፋችው።ፍሊፖ ቱሬታ ከተባለው የቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋርም የመመረቂያ ጋወን ሊገዙም ሄደው ነበር ተብሏል።

ጥንዶቹ መጥፋታቸው ከተነገረ ከቀናት በኋላም ፍሊፖ የቀድሞ ፍቅረኛውን በቤቷ አቅራቢያ በመኪና ውስጥ ሲደበድባት የሚያሳይ ቪዲዮ መገኘቱንም መርማሪው ዳኛ ተናግረዋል።

አስከሬኗም በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ነው የተገኘው።