አሜሪካዊው ጋዜጠኛ የግድያ ወንጀል እየዘገበ ተገደለ

የፖሊስ ቢሮ

የፎቶው ባለመብት, CBS

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ በኦርላንዶ ፍሎሪዳ አቅራቢያ ከሰዓታት በፊት የተፈጸመን የግድያ ወንጀል እየዘገበ በነበረበት ወቅት በጥይት ተገደለ።

ጋዜጠኛው የተገደለው እየዘገበ በነበረው የግድያ ወንጀል ተጠርጣሪ ነው።

ግድያው የተፈጸመው ትናንት፣ የካቲት 15/ 2015 ሲሆን ከጋዜጠኛዋ በተጨማሪ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ በተተኮሰባት ጥይት ተገድላለች።

ሌላኛዋ ጋዜጠኛ እና የታዳጊዋ እናት በተመሳሳይ ታጣቂ ተመትተው ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገልጿል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ስፔክትረም ኒውስ ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሰሩ ሲሆን በአካባቢው የጣቢያው 13 ጋዜጠኞች የአንድ ሴትን ግድያ ሲዘግቡ ነበር።

ግለሰቡን የገደለውም ተጠርጣሪ ተመልሶ እንደተኮሰባቸው ፖሊስ ገልጿል።

ጋዜጠኞቹ ኢላማ ተደርጎባቸው ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት የጦር መሳሪያ ይዞ እንደነበርና ከፖሊስ ጋር ባለመተባበር እምቢተኝነቱን ማሳየቱን መርማሪዎች ተናግረዋል።

ረቡዕ እለት በኦርላንዶ በደረሱ ሁለት ጥቃቶች የተገደሉት ሶስት ግለሰቦች ማንነት አልተገለጸም።

የኦሬንጅ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ጆን ሚና ጋዜጠኞቹ በተሽካርካሪያቸው ወይም በአቅራቢያው እንደነበሩ ተናግረው መኪናው የቴሌቪዥን ጣቢያው አርማም አልነበረውም ብለዋል። ጥቃቱ የደረሰባቸው በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር አስር ሰዓት ላይ ነበር።

ጋዜጠኞቹ በዚያችው ዕለት አምስት ሰዓት አካባቢ የተፈጸመን ግድያ እየዘገቡ ነበር ተብሏል።

አንድ ታጣቂ በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝና መኪና ውስጥ በነበረች ግለሰብ ላይ በጥይት ተኩሶ ገድሏታል ተብሏል። ጋዜጠኞቹ ወንጀሉ የተፈጸመበት ስፍራ ላይ ደርሰው እየዘገቡ በነበረበት ወቅትም ተጠርጣሪው ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኩስ መክፈቱ ተሰምቷል።

ጋዜጠኞቹ ላይ ከተኮሰ በኋላ የ19 ዓመቱ ተጠርጣሪ ኬይዝ ሞሰስ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቤት ገብቶ አንዲት ህፃን እና እናቷ ላይ ተኩስ እንደከፈተባቸው ፖሊስ ተናግሯል።

እናትየው ሆስፒታል እንደምትገኝና በአስጊም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አክለዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ጋዜጠኞች ለተጎጂዎች የመጀመሪያ እርዳታ እንዳደረጉም የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል። ስፔክትረም ኒውስ የሪፖርተሯ ሞት ከተነገረም በኋላ የቀጥታ ዘገባውን አለማቆም ተገልጿል።