የተወካዮች ምክር ቤት ሥራቸውን በለቀቁት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ምትክ አዲሶችን ሾመ

የፎቶው ባለመብት, HOPR
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፍቃዳቸው ሥራ የለቀቁ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንትን የሚተኩ ሁለት ዕጩዎችን ተቀብሎ ሹመታቸውን አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 26/2015 ዓ.ም. ባደረገው 13ኛ መደበኛ ጉባኤው ከዚህ ቀደም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሌሊሴ ደሳለኝ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በምክትል ፕሬዝዳንትነት ደግሞ በሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተለያየ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉትን ዘሃራ ኡመርን ሾሟል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋጋሪ እንዲሁም ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ተናኘ ጥላሁን በፍቃዳቸው የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል መባሉን ተከትሎ ነው ሁለቱ ተተኪዎች ለምክር ቤቱ የቀረቡት።
አዲሷ ተሿሚ ሌሊሴ ደሳለኝ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ ለሁለት አስርት ዓመታት ማገልገላቸው ተገልጿል።
የሌሊሴ ትምህርትን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአመራር እና ለውጥ ትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ማግኘታቸው ተገልጿል።
በሥራ ልምዳቸው በኩልም በዳኝነት የካበተ ልምድ አላቸው የተባሉት ሌሊሴ፣ ሥራቸውን የጀመሩት በ1994 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኛ በመሆን ነው።
ከ1995 እስከ 1999 ዓ.ም ባሉት ዓመታት በምሥራቅ ወለጋ ዞን እንዲሁም በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በዳኝነት አገልግለዋል።
በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንትነት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ማገልገላቸው ተጠቅሷል።
ወደ ፌደራሉም በመዛወር በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለሦስት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት እያገለገሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, HOPR
በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተሾሙት ዘሃራ ኡመር በሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ዘሃራ ኡመር የሲቪል ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሩቅ ሲሆኑ፣ በሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወንጀል ችሎት፣ በፍትሐ ብሔር እና በሰበር ሰሚ ችሎት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በዳኝነት ማገልገላቸው ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በጥብቅና ሙያ ለአምስት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑም ወቅት በክልሉ የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው እየሰሩ እንደነበር ተገልጿል።
በዛሬው የፓርላማ ውሎ በተመሳሳይ መልኩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው በፈቃዳቸው ከሥራ የመልቀቅ ጉዳይ ጥያቄ ተነስቷል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ በፍቃዳቸው ከሥራ በመልቀቃቸው ምክንያት ተተኪዎቻቸው የተሾሙት ከሁለት ወራት በፊት መሆኑ ይታወሳል።
ይህንንም አስመልክቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (እብን) ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሁለቱ ፍርድ ቤቶች ኃላፊዎች መልቀቂያ ማስገባታቸው ሊመረመር ይገባል ብለዋል።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሕግ አስፈጻሚው አካል ወይም ፖሊስ በዳኝነት ጣልቃ በመግባት እና ፍርድ ቤቶች የሚወስኑትን ለማስፈጸም ካለ ዳተኝነት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችል እንደሆነ ሊፈተሽ እንደሚገባም ጠቁመዋል።












