ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ አረፉ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ ከዚህ ዓመት በሞት ተለዩ።

ፕሮፌሰር አንድርያስ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሐሙስ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም. ማረፋቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው ፕሮፌሰር አንድርያስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በሌሎች ዓለማት ፍልስፍና ያስተምሩ ነበር።

ፕሮፌሰር አንድርያስ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ እዚህ አዲስ አበባ የተማሩ ሲሆን ከዚያ በኋላም ወደ አሜሪካ በማቅናት በዊሊያምስ ኮሌጅ እና በየል ዩኒቨርስቲ ፍልስፍና ተምረዋል።

ከወላጅ እናታቸው መንበረ ገብረ ማርያም እና ከወላጅ አባታቸው ከእሸቴ ተሰማ የተወለዱት መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አንድርያስ ስለራሳቸው ሲናገሩ “እኔን ያሳደጉኝ ሦስት ቤተሰቦች ናቸው” የሚሉ ሲሆን እነዚህም ወላጆቻቸው፣ አጎታቸው እና የሪቻርድ ፓንክረስት ቤተሰብ ጋር ማደጋቸውን ይናገራሉ።

በዊልያምስ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከየል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመልሰው በመምህርነት እንዲሁም በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር አንድርያስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ብራውን፣ ዩሲኤልኤ፣ በርክሌይ እና ፔንሲልቬንያ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ ሲሆን በዩኔስኮ የሰብአዊ መብት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሊቀ-መንበር በመሆን አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ በሙያቸው ያገለገሉት ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንትነታቸው ከለቀቁ በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ በመሆን ሠርተዋል።

መምህሩ እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አንድርያስ በሞራል እና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች እንዲሁም ሥነ-ምግባር ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለሕትመት አብቅተዋል።

የአንድ ልጅ አባት የሆኑት ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ሌሎች ሁለት ልጆችንም እንደ አባት ተንከባክበው ማሳደጋቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።