ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምርጫ ለመሳተፍ በቅድመ ሁኔታ እና ሕጋዊነትን በማጣት መካከል የተወጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች
አስር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን እና "ከአጃቢነት ያለፈ ተሳትፎ" እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ቅድመ ሁኔታዎችን አቀረቡ።
ራሳቸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት መድረክ (መድረክ) ሲሉ የሚጠሩት 10 የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ኅዳር 3/2018 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ "ሕጋዊነትን ለመላበስ የሚደረጉ የፖለቲካ ትወናዎች" ሲሉ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎችን በመኮነን፤ ምርጫዎቹ "ነፃ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ፤ በውጤታቸውም ተዓማኒ እና በሕዝብ ተቀባይነት አላገኙም" ሲሉ ተችተዋል።
የኢህአፓ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አብርሃም ሃይማኖት ከወራት በኋላ የሚደረገው አገራዊ ምርጫ "አስቻይ ሁኔታ ካልተፈጠረ እኛም ከአጃቢነት የተለየ ተሳትፎ አይኖረንም፤ ምርጫውም ትርጉም የለሽ፣ የይስሙላ ከመሆን [አያልፍም]" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት መድረክ በጋራ ባወጣው መግለጫ ላይ "ሕጋዊነትን ለመላበስ የሚደረጉ የፖለቲካ ትወናዎች" ሲሉ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎችን በመኮነን፤ ምርጫዎቹ "ነፃ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ፤ በውጤታቸውም ተዓማኒ እና በሕዝብ ተቀባይነት አላገኙም" ሲል ተችቷል።
ኢህአፓ፣ ኦነግ እና ኦፌኮን ጨምሮ 10 አገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎች ሰባተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰባት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ "መሠረታዊ ማሻሻያዎች" እንዲካሄዱ የጠየቁ ሲሆን፤ "አስቻይ ሁኔታ" ይፈጠር ብለዋል።
ፓርቲዎቹ ካቀረቧቸው ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር፣ ግጭቶችን ማቆም እና የሰላም ዋስትና፣ የተቋማት ማሻሻያ እና ገለልተኝነትን እንዲሁም የፕሬስ ነፃነትን ማስፈን ይገኙበታል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢህአፓው ፕሬዝዳንት "የአገሪቱ ሰላም እና ፀጥታ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ይሄ ደግሞ ከምርጫው በፊት ወደ ድርድር፤ ወደ ሰላም መምጣት ነው ያለበት። ሌላኛው የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የፓርላማ አባላት ሳይቀሩ በየእስር ቤቱ ነው የሚገኙት።...ስለዚህ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበናል" ብለዋል።
"መንግሥት ምህዳሩን አጥብቦብናል፤ ታጣቂዎች ደግሞ ሰላማዊ ታጋዮችን እንደ ጠላት ማየት አለ። በሁለት ኃይሎች መካከል ሆነን እንዴት ነው ምርጫ ልንሳተፍ የምንችለው?" ሲሉ የፀጥታ ችግሩን እና ተሳትፏቸውን ጉዳይ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. ለማካሄድ አቅዷል።
የድምጽ መስጫ ዕለትን እና ሌሎችንም የምርጫ ሂደቶች የያዘ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ምርጫ ቦርድ አዘጋጅቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሌሎችም አካላት ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን እስካሁን ግን አልፀደቀም።
የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ "የኃይል ምንጭ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ከተባበረ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ከቆሙ እነዚህን ጥያቄዎች ሥርዓቱ እንዲመልስ ማድረግ እንችላለን የሚል እምነት አለን" ብለዋል።
የምርጫ ቦርድ "ገለልተኛነት" እና "ብቁነት" ላይ ጥያቄ ያነሱት ፓርቲዎቹ፤ ያቀረቧቸው "መሠረታዊ" ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ላይ "የመንግሥት ቁርጠኝነትን" ቢጠራጠሩም የኢህአፓው ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ምርጫ ከተካሄደ "የጨረባ...ነው የሚሆነው" ብለዋል።
ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ምርጫው ከተካሄደ ፓርቲያቸው አይሳተፍ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ አብርሃም፤ "ብንሳተፍ እንኳ ላለመፍረስ [ላለመሰረዝ] ነው" ሲሉ የተሳትፏቸው ጉዳይ በቀጣይ የሚወሰን መሆኑን አመልክተዋል።
"ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ብልፅግና ፓርቲ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእኛ ጋር መነጋገር፤ መደራደር [አለበት]" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ቅድመ ሁኔታዎቹ ባልተሟሉበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ "ዋጋ የለውም" ብለዋል።
መጪው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት፤ በስደት እና በትጥቅ ትግል የሚገኙትን ጨምሮ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና ባለድርሻ አካላት መካከል ሁሉን አቀፍ ውይይት በማድረግ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እና እርቅ ማውረድ አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።
አቶ አማኑኤል ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎቹ ካልተሟሉ "ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" በማለት "እጅ አንሰጥም" ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ በግፍ ታስረው የሚገኙ ያሏቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት እና የፖለቲካ እስረኞችን መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ መልቀቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በተቃዋሚዎች ላይ ይደርሳል ያሉት ማዋከብ እና ማስፈራራት፣ ሙሉ በሙሉ መቆም እንዳለበትም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
ቅድመ ሁኔታዎቹ ሰፊ እና ማሻሻያ የሚጠይቁ በመሆናቸው ከምርጫው በፊት ለማሟላት፤ "መንግሥት ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ" ነው ሲሉ "በቂ ጊዜ አለ" ብለዋል።
ቀጣዩን ምርጫ "ወሳኝ" ሲሉ የገለፁት አቶ አብርሃም፤ ምርጫው የይስሙላ ከሆነ "ሰላማዊ ትግል ላይ ያለን ጭላንጭል ተስፋን ጭምር የምንቆርጥበት፤ አገሪቱ ከሰላማዊ ትግል ውጪ ሌሎችን አማራጮች የምታማትርበት፤ አሁን ካለው ጦርነት በላይ ከፍተኛ እልቂት የሚከሰትበት ነው የሚሆነው" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ይደረጋል ከተባለው ምርጫ በፊት በቀዳሚነት ሊደረጉ ይገባል የሚሏቸውን ቅድም ሁኔታዎችን በመዘርዘር በጋራ መግለጫ ካወጡት ፓርቲዎች መካከል አንዳንዶቹ "አመቺ ሁኔታ የለም በሚል በቀደመው ምርጫ ያልተሳተፉ ይገኙበታል።
እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ የማይሳተፉ ከሆነ ሕጋዊነታቸውን የሚያጡ በመሆናቸው ሊሟሉ ይገባሉ ባሏቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና በኅልውናቸው መካከል ሆነው ምርጫው ወራት ቀርተውታል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት ሰባተኛውን ዙር አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ባወጣው መረሃ ግብር መሠረት የሚያስፈልጉ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን አስቻይ ሁኔታ ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫን ለማካሄድ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ የቀደመው ምርጫ ጦርነት በነበረበት ጊዜ መካሄዱን ጭምር በመጥቀስ የምርጫው መካሄድን አይቀሬነት አረጋግጠዋል።