ገላችንን መታጠብ ያለብን ጠዋት ወይስ ማታ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ገላችንን መታጠብ ያለብን ጠዋት ነው ወይስ ማታ የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው።
ብዙዎች ጠዋት እንቅልፍ የተጫጫነው ሰውነታቸውን ለማነቃቃት ሰውነታቸውን ይታጠባሉ። ቢያንስ ለአሥር ደቂቃ መታጠብ አካልን እንደሚያነቃቃ የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም።
ቀናቸውን ሻወር ወስደው መጀመር ከሚፈልጉ ሰዎች በተቃራኒው ያሉት ደግሞ የቀን ድካምን ለማስወገድ ማታ ሰውነታቸውን የሚታጠቡ ናቸው።
ቆንጆ እንቅልፍ ለመተኛትና በድካም የዛለ አካልን ዘና ለማድረግ ምሽት ላይ ሰውነታቸውን ይታጠባሉ።
ለመሆኑ በጉዳዩ ላይ ሳይንስ ምን ይላል? ለጤናስ የሚጠቅመው ጠዋት መታጠብ ነው ማታ?
ሰውነትን መታጠብ አቧራ፣ ላብና ሌላም ከቆዳችን ያስወግዳል። ቀኑን ሙሉ ሰውነታችን አቧራን ጨምሮ ለተለያዩ በካይ ነገሮች ይጋለጣል።
ከመኝታ በፊት ሰውነታችንን ካልታጠብን እነዚህን ሁሉ በካዮች ወደ አልጋችን ይዘን እንገባለን።
በቆዳችን ላይ አንድ ስኩዌር ሴንቲሜትር ወስደን በማጉያ መነጽር ብንመለከተው ከ10ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ባክቴሪያዎች እናገኛለን።
ላብ ከሚያመነጨው የሰውነት ክፍል ቅባት በማግኘት ሕይወታቸውን ይገፋሉ። ጠረን ያለው ከሰውነት የሚመነጭ ላብ ሳይሆን እንደ ስታፊሎሎከስ ያሉ ባክቴሪያዎች ሲከማቹ የሚፈጥሩት ሽታ ነው።
ይህንን እውነታ ከግምት በማስገባት ምሽት ላይ ሰውነትን መታጠብ ጥሩ አማራጭ ቢመስልም ነገሩ ያን ያህል ቀላል አይደለም።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሌስተር ማይክሮባዮሎጂስት የሆኑት ፕሪምሮዝ ፍሪስቶን "ማታ ሰውነታችንን ታጥበን ስንተኛ አካላችን እንደታደሰ ቢሰማንም ሌሊት ላይ ያልበናል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀዝቃዛ አየር ቢኖርም እንኳን ከሰውነት ላብ መመንጨቱ አይቀርም። ከሰውነት ከሚወጣው ወደ 50ሺህ የሚጠጋ የቆዳ ሕዋስ ጋር ላብ ሲደባለቅ ለባክቴሪያ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
"በቆዳ ላይ ያለው ባክቴሪያ ሊመገበው የሚችለው ይሄንን ነው። ስለዚህ ማታ ሻወር ወስደን ብንተኛም ጠዋት ስንነሳ አልቦን ነው የምንነቃው" ይላሉ ባለሙያዋ።
ምሽት ላይ መታጠብ ጠቀሜታው የሚጎላው አንሶላችንን አዘውትረን የምናጥበው ከሆነ ነው። ባክቴሪያ አንሶላ፣ አልጋ ልብስና የትራስ ልብስ ላይ ለሳምንታት መኖር ይችላል።
የትራስ ልብስ ላይ ፈንጋይን የመሰሉ ነፍሳት ዘለግ ላለ ጊዜ መቆየት ይችላሉ።
ብዙኃኑ በእነዚህ ነፍሳት ጉዳት ላይደርስባቸው ይችላል። ሆኖም ግን 76% የሚሆኑ ብርቱ የአስም ሕመም ያለባቸው ሰዎች የፈንጋይ አለርጂ አለባቸው።
አስፔርጊለስ ፉሚጋቱስ የተባለው የፈንገስ ዓይነት በተለይም የሳምባ ነቀርሳ እና ከማጤስ ጋር የተያያዘ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ለሳምባ ሕመም ያጋልጣል።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሁል የሚያስተምሩት ሆሊ ዊልክሰን እንደሚሉት አዘውትሮ ምሽት ላይ ሰውነትን ከመታጠብ ይልቅ አንሶላን ንጹህ ማድረግ የተሻለ ጠቀሜታ አለው።
"ማታ ሰውነታችንን ታጥበን አንሶላችንን አንድ ወር የምንተኛበት ከሆነ ባክቴሪያ መሰብሰቡ አይቀርም" ይላሉ።
የፖለን አለርጂ ያለባቸው ሰዎች አንሶላቸውን የማያጥቡ ከሆነ ሕመማቸው ይባባሳል።
ቆሻሻ ልብስ ለብሶ መተኛትም የቆዳ ኢንፌክሽን ያስከትላል።
ማታ ሰውነታቸውን የሚታጠቡ ሰዎች የተሻለ እንቅልፍ እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
13 ጥናቶች ላይ የተደረገ ዳሰሳ እንደሚያሳየው ለ10 ደቂቃ ሻወር መውሰድ በቶሎ ለመተኛት ይረዳል። ሰውነትን አሙቆ ከዚያም ማቀዝቀዝ የእንቅልፍ ሰዓት መድረሱን ለሰውነት መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ ነው።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሌስተር ማይክሮባዮሎጂስት የሆኑት ፕሪምሮዝ ፍሪስቶን ጠዋት መታጠብ የተሻለ ነው ብለው ያምናሉ።
ጠዋት ሻወር በመውሰድ ሌሊት ላይ ከሰውነት የወጣውን ላብና ጥቃቅን ባክቴሪያዎችን ያስወግዳል። ቀኑን በጥሩ መንፈስ ለመጀመር ጠዋት ሰውነትን መታጠብ ይረዳል።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሁል የሚያስተምሩት ሆሊ ዊልክሰን በበኩላቸው "በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ሰውነታችንን የምንታጠብ ከሆነ ጠዋትም ብንታጠብ ማታም ብንታጠብ ለውጥ አይኖረውም" ይላሉ።
ጠዋት ወይም ማታ ሻወር መውሰድ ከጤና ጋር በተያያዘ የጎላ ልዩነት የለውም። ቀኑን ተነቃቅቶ መጀመር ይሻላል ወይስ ምሽት ላይ ድካምን በሻወር አራግፎ መተኛት የሚለውን መምረጥ ይቻላል።
በየቀኑ ሰውነትን መታጠብ ንጽህናንና ጤናን ለመጠበቅ ሁነኛ መንገድ ነው።
"የምንሠራው ሥራ ይወስነዋል። ለምሳሌ አርሶ አደር ምሽት ላይ መታጠብ ሊመርጥ ይችላል። ዋናው ነገር የሰውነትን ጤና መጠበቅ ነው" ሲሉ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።















