ጨው ለጤናችን ጠቃሚ እንዲሁም አደገኛ ሊሆን የሚችለውን ምን ያህል ስንመገብ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ጨው ያነሰው ምግብ መመገብ ልክ ከፍተኛ ጨው የገባበትን ምግብ እንደ መመገብ አደገኛ ነው ብለው ይከራከራሉ። ግን እውነታው ምንድን ነው?
በጨው ፍቅር ወድቀናል። የሕክምና ባለሙያዎች ቢያስጠነቅቁም በመላው ዓለም የሚገኝ ሕዝብ መጠቀም ካለበት ሁለት እጥፍ በላይ ጨው ይመገባል። ይህም በሂደት የጤና መታወክን ያስከትላል።
ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው የቆሙ ክርክሮች የአድማጮችን ቀልብ እየሳቡ ነው። ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተደረጉ ምርምሮች ላይ ጥርጣሬን በመፍጠር እና ስለ ተወዳጁ ቅመም ያልተመለሱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥያቄን አጭረዋል።
በጨው ውስጥ የሚገኘው ቁልፍ ንጥረ ነገር ሶዲየም የሰውነታችን አጠቃላይ የፈሳሽ ሚዛንን ለመጠበቅ፣ ኦክሲጅን እና ንጥረ ነገሮችን ለማጓጓዝ አስፈላጊ ነው። የነርቭ ሥርዓታችን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሸከም ያደርገዋል።
ነገር ግን አብዛኛው ሰው ከሚመከረው በላይ ጨው በመመገቡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የምንመገበውን የጨው መጠን እንድንቀንስ ለማድረግ ተቸግረዋል።
በየቀኑ ምን ያህል ጨው መውሰድ አለብን?
የዓለም የጤና ድርጅት እያንዳንዱ ሰው በየቀኑ መጠኑ ከአምስት ግራም የማይበልጥ ጨው መመገብ እንዳለበት ይመክራል።
በተጨማሪም ከተቻለ በቀን ከሁለት ግራም ያነሰ ሶዲየም መጠቀም ላይ ብንገድብ መልካም ነው ይላል።
በአሜሪካ አዋቂ ሰዎች በቀን ከ2.3 ግራም ያነሰ ሶዲየም እንዲወስዱ፤ ያም ማለት አንድ የሻይ ማንኪያ ጨው ያህል ይመከራሉ።
ይህ አንድ የሻይ ማንኪያ ያህል የሚሆነው ከአምስት ግራም ያልበለጠ ጨው በአጠቃላይ በአንድ ቀን ውስጥ በተለያዩ ሁቤታዎች በምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ ተሠራጭተው የሚገኙ ናቸው።
በ2022 ተመራማሪዎች በቀን ከ3 እና 6 ግራም ጨው መውሰድ የልብ ሕመምን ለመቀነስ ፍቱን አማራጭ ነው ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት በበኩሉ አዋቂ ሰዎች በቀን ከስድስት ግራም በላይ ጨው መውሰድ እንደሌለባቸው ይመክራል።
ይህ ደግሞ በቤት ውስጥ በምናዘጋጃቸው ምግቦች ብቻ ሳይሆን ከውጭ አዘን የምንመገባቸውን ምግቦችንም ያካትታል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) አማካኝ የጨው ፍጆታ በቀን 8.4 ግራም ሲሆን፣ በአሜሪካ ደግሞ 8.5 ግራም ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጨው ፍጆታ በቀን ወደ 10.8 ግራም ማደጉን በመግለጽ ስጋቱን በመግለጽ እያስጠነቀቀ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን ራሳችን በምናበስላቸው ምግቦች ውስጥ የምንጨምረው ጨው ከምንመገበው አንድ አራተኛውን ብቻ ነው።
ሌላው በምንገዛቸው ምግቦች ውስጥ ተደብቆ ያለ ነው።
ዳቦ፣ ስጎ፣ ሾርባ እና አንዳንዴም ጥራጥሬዎች ውስጥ ጨው ተደባልቆ ይሸጣል።
በፋብሪካ ታሽገው የሚሸጡ ምግቦች ጨው አለባቸው ከሚል መግለጫ ይልቅ አደናጋሪ በሆነ መልኩ ሶዲየም ተብሎ ይጻፍባቸዋል።
ይህ ደግሞ መውሰድ ከሚገባን ዝቅተኛ የጨው መጠን እንደወሰድን እንዲሰማን ያደርጋል።
ጨው የሶዲየም እና የክሎራይድ አየኖች ውህድ ነው።
በ2.5 ግራም ጨው ውስጥ 1 ግራም ሶዲያም አለ።
"ሰፊው ሕዝብ ይህንን አይረዳም፤ እናም ሶዲየም እና ጨው አንድ መሆናቸውን ልብ አይልም። ማንም ደግሞ ይህንን አይነግረንም" ያሉት የኒውትሪሽን ባለሙያው ማይ ሲምፕኪን ናቸው።
እንደ አሜሪካ በሽታ መከለከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) መረጃ ከሆነ በአሜሪካ ፍጆታ ላይ የሚውለው 40 በመቶ የሚሆነው ሶዲየም የሚመጣው ከፒዛ፣ ቦሪቶ፣ ታኮ፣ ጣፋጮች፣ የዶሮ ምግቦች፣ በርገሮች እና ከአሳማ፣ ዶሮ እና የበሬ ሥጋ በፋብሪካ ከሚዘጋጁ ምርቶች ነው።
ብዙ ጨው በመመገብ የሚመጡ የጤና አደጋዎች
ተመራማሪዎች ከፍተኛ የጨው መጠን መመገብ ለደም ግፊት እንደሚያጋልጥ፣ ይህም ወደ ልብ ሕመም እና ስትሮክ እንደሚያመራ ደርሰውበታል።
ባለሙያዎች ከጨው በተቃርኖ የተገኙ የምርምር ውጤቶች አሳማኝ መሆናቸው ላይ ጥርጣሬ የላቸውም።
ጨው በምንመገብበት ወቅት ሰውነታችን ውሃ ይይዛል፣ የደም ግፊትን በመጨመር ኩላሊታችን እስኪያስወግደው ድረስ የደም ግፊታችን ይጨምራል።
ለረዥም ጊዜ የሚወሰድ ከፍ ያለ መጠን ያለው ጨው የደም ስራችን ላይ መስተጓጎል በመፍጠር ወደ ደም ግፊት በማምራት 62 በመቶ ስትሮክ፣ 49 በመቶ ለልብ ሕመም እንደሚያጋልጥ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ሶዲየም መውሰድ በየዓመቱ በዓለም ላይ ለሚደርሱ ከ1.89 ሚሊዮን ሞቶች ጋር ተያያዥ ነው።
ባለፉት 35 ዓመታት የታተሙ 13 ጥናቶችን የፈተሸው ትንተና እንዳስቀመጠው ከሆነ በቀን ከ5 ግራም በላይ ጨው መመገብ ለልብ ሕመም የመጋለጥን ዕድል 17 በመቶ እንዲሁም በስትሮክ የመጠቃት ዕድልን ደግሞ 23 በመቶ ይጨምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምንወስደውን የጨው መጠን መቀነስ
የምንወስደውን የጨው መጠን መቀነስ አሉታዊ ጎኖችን በማስወገድ ረገድ ትልቅ አበርክቶ አለው።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተሠራ አንድ ጥናት በቀን የምንወስደውን የጨው መጠን በ1.4 ግራም ስንቀንስ በደም ግፊት የመያዝ ዕድላችን ይቀንሳል። 42 በመቶ ስትሮክ፣ 40 በመቶ ከልብ ሕመም ጋር የተያያዙ ሞቶችም ይቀንሳሉ።
በ2023 የታተመ ጥናት ደግሞ የደም ግፊት ላለባቸው ሕሙማን ከሚሰጠው መድኃኒት በበለጠ ለአንድ ሳምንት ዝቅተኛ የሶዲየም መጠን ያለው ምግብ መመገብ የደም ግፊትን በመቀነስ ረገድ ያለው ለውጥ ከፍተኛ ነው።
የጃፓን መንግሥት በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ዜጎቹ የሚወስዱትን የጨው መጠን እንዲቀንሱ ዘመቻ ካካሄደ በኋላ በቀን 13.5 ግራም ይወስዱ የነበሩት ወደ 12 ግራም ዝቅ ማድረግ ችለዋል።
በዚሁ ጊዜ ውስጥ የደም ግፊት የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እንዲሁም በስትሮክ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 80 በመቶ ቀንሷል።
በ1970ዎቹ እንዲሁ በፊንላንድ በቀን 12 ግራም ይወስዱ የነበሩ ዜጎች በአውሮፓውያኑ 2002 ወደ ዘጠኝ ግራም ዝቅ ማድረግ ችለዋል።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በስትሮክ እና በልብ ሕመም የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከ75 እስከ 80 በመቶ ቀንሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጨው በተለያዩ ሰዎች ላይ ያለው ተጽዕኖ
የበዛ የጨው አጠቃቀም በሰዎች ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ የጤና ጉዳት ከሰው ወደ ሰው ይለያያል።
ጥናቶች ሰውነታችን ለጨው አጠቃቀማችን የሚሰጠው ምላሽ የተለያየ መሆኑን ደርሰውበታል።
ይህ ደግሞ በዘር ግንዳችን፣ በዕድሜ፣ የሰውነት ክብደታችን እና ያለን የስብ መጠን፣ አጠቃላይ ጤና እና በዘር ያለ የደም ግፊት ታሪክ የተነሳ ነው።
ለጨው ከፍተኛ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ከጨው ጋር በተያያዘ ለደም ግፊት የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው።
አሁን አሁን ተመራማሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ጨው መመገብ ብቻ ሳይሆን አነስተኛ መጠን መውሰድም ለደም ግፊት የማጋለጥ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው በማለት ይከራከራሉ።
ከሌሎች ብዙ ጥናቶች ጋር ተዳምሮ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በጣም ትንሽ ጨው መመገብ ከልብ ችግሮች እና ከሞት ጋር ግንኙነት አለው።
ተመራማሪዎቹ በቀን ከ5.6 ግራም በታች እንዲሁም ከ12.5 ግራም በላይ መመገብ ከአሉታዊ የጤና ሁኔታዎች ጋር ተያያዥነት አለው ብለዋል።
በ2020 ይፋ የሆነ ጥናት ደግሞ የጨው አመጋገባችን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ በተለይ በወጣቶች እና ነጭ ባልሆኑ ግለሰቦች ዘንድ ለልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድልን ያሰፋል ብሏል።
170 ሺህ የተሳተፉበት ሌላ ጥናትም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
በማክ ካስተር ዩኒቨርስቲ የሥነ ምግብ ተመራማሪ የሆኑት አንድሪው ሜንቴ ከከፍተኛ የጨው መጠን ወደ መካከለኛ መቀነስ (ከ1.5 እስከ 2.5 የሻይ ማንኪያ ጨው መጠቀም) የደም ግፊትን ይቀንሳል።
ነገር ግን ከዚያ ያለፈ የጤና ጥቅም የለውም። ከዝቅተኛ ወደ መደበኛ ከፍ ማድረግ ደግሞ ሊያግዝ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የብሪታኒያ የሥነ ምግብ ፋውንዴሽን ባልደረባ የሆነችው ሳራ ስታነር የጨው መጠንን መቀነስ የደም ግፊትን እንዲሁም የልብ ሕመምን እንደሚቀንስ ምንም ጥርጥር የለውም ትላለች።
አክላም በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ በቀን 3 ግራም ጨው የሚመገቡ ሲሆን፣ አንዳንድ ጥናቶች ይህንን እጅግ በጣም ዝቅተኛ ሲሉ ይገልጹታል።
ወደ ሰውነታችን የምናስገባው ጨው ከተለያዩ ምግቦች የሚመጣ በመሆኑ ያንን ለመቆጣጠር ልንቸገር አንችላለን።
በአጠቃላይ በሰዎች ምግብ ውስጥ የሚገኘውን የጨው መጠን ለመቀነስ በዩኬ እንደተደረገው ኩባንያዎች በምርቶቻቸው ላይ የሚያስገቡትን የጨው መጠን እንዲቀንሱ ማድረግ መፍትሄ ነው።
ስታነር አክላም ጨው በደም ግፊት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በፖታሲየም የበለፀጉ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶችን እንዲሁም ለውዝ እና የወተት ተዋፅኦዎችን መመገብ ጠቃሚ ነው።
የላንካስተር ዩኒቨርስቲ ምሁሯ ሲዩ ማቴያስ በበኩሉ ጨውን ሙሉ በሙሉ ከማስወገድ ይልቅ በምግባችን ውስጥ የተደበቁትን ማስተዋል ተገቢ ነው። ጨው ሲበዛም ሲያንስም አደጋ አለው የምትለው ማቴያስ በርካታ ጥናቶች ሊሠሩ እንደሚገባ ትናገራለች።
ለአሁን ግን ጤናማ ሰዎች ጥቂት ጨውን ቢወስዱ መልካም መሆኑን፤ ነገር ግን ከፍ ያለ መጠን መጠቀም ወይንም ሙሉ በሙሉ መተው ግን አደጋ እንዳለው መገንዘብ አስፈላጊ ነው።
በ2022 ይፋ የሆነ ጥናት በቀን ከ3 እስከ 6 ግራም የሆነ መካከለኛ የሆነ የሶዲየም አጠቃቀም የልብ ሕመምን ለመቀነስ ጠቃሚ ነው።















