ዳግም የተቃቃሩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ያመሩ ይሆን?

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለሥልጣናት የሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ የሚያደርጓቸው ንግግሮች ወደ ጦርነት ሊያስገቧቸው በሚችሉ የቃላት ልውውጦች የታጀቡ ናቸው።
የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ወደብ የማግኘት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ጦርነት በማንኛውም ጊዜ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት እየጨመረ መጥቷል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይፋ የባሕር በር ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው ያሉት ከሁለት ዓመታት በፊት በ2016 ዓ.ም. ነው።
በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ በየትኛውም መልኩ የባሕር በር ማግኘቷ እንደማይቀር ተናግረው ጦርነት ሊኖር እንደሚችል አመልክተዋል።
በኤርትራ ስር ከሚገኙ ወደቦች አንዱ የሆነው እና ለኢትዮጵያ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የአሰብ ወደብ ከኢትዮጵያ ድንበር 60 ኪሎ ሜትር ብቻ የሚርቅ ነው።
ኤርትራ ነጻነቷን ያወጀችው በ1985 ዓ.ም. ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና ቀርታለች።
በሁለቱ አገራት መካከል በድንበር ይገባኛል ውዝግብ ምክንያት 1990 አስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ ጦርነት ተካሂዶ ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል።
ሁለቱ አገራት ለረዥም ጊዜ ውጥረት ውስጥ ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ2010 እስከ 2016 ዓ.ም. ድረስ ወዳጆች ነበሩ።
አሰብ . . . "ማንኛውም ዋጋ ሊከፍሉለት የሚገባ"
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የኤርትራ ነጻ አገር መሆንን ተከትሎ ወደብ ያጣችበት "ስህተት"፤ "ነገ ይታረማል" ሲሉ ተናግረዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ጄነራል ባጫ ደበሌ አሰብ "የኢትዮጵያ ሀብት" መሆኑን ገልጸው "በኃይል ይመለሳል" ብለዋል።
"ጥያቄው አሁን አሰብ የእኛ ነው አይደለም የሚለው አይደለም፤ እንዴት እናስመልሰዋለን? የሚለው ነው" ሲሉ የመንግሥት ደጋፊ ለሆነው አዲስ ፓራዳይም የተባለ የዩቲዩብ ቻናል ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።
መስከረም 11/2018 ዓ.ም. የጦሩ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ኢትዮጵያን የባሕር በር ያሳጡ አገራትን እንደሚወጉ፣ ኤርትራን በተዘዋዋሪ በመጥቀስ ተናግረዋል።
"ሕዝባችን አሁን 130 ሚሊዮን ነው እና በሚቀጥሉት 25 ዓመታት 200 ሚሊዮን ይደርሳል። እንዴት ሆኖ የሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ፍላጎት [ኤርትራ] የ200 ሚሊዮን ሕዘብን ፍላጎትን ይደፈጥጣል" ሲሉ መስከረም 15 ተናግረዋል።
አክለውም "የመከላከያ ኃይላችንን እናጠናክራለን፣ ዕድገታችንን እናፋጥናለን እና የባሕር በር ማግኘታችንን እናረጋግጣለን" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ኃላፊ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ባለቤትነት ሲያስረዱ "ማንኛውም ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ" ሲሉ ገልጸውታል።
"አሰብ በቀይ ባሕር ላይ ነው የሚገኘው. . . ለኅልውናችን አስፈላጊ የሆነ ማንኛውም ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ ነገር ሆኗል" ነበር ያሉት ጄነራሉ።
የመከላከያ ምህንድስና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጄነራል ደስታ አብቼ ከፍተኛ የወታደራዊ መኮንኖች በተሰበሰቡበት የቀይ ባሕር በር ለማግኘት "በየዕለቱ እየተቃረብን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"ይህንን ማድረግ [የባሕር በር ማግኘት] ተልዕኮውን የሚሸከም አስተማማኝ ኃይል መገንባት አለብን፤ እና ለዚህም ነው ዕለት በዕለት ወደዚያ እየተቃረብን ያለነው" ብለዋል።
የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያን ማስጠንቀቅ
ከኢትዮጵያ ወገን በቀይ ባሕር የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት በተደጋጋሚ ቢሰማም የኤርትራ መንግሥት ምላሽ ግን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ላይ በሚለጥፉት አጭር መልዕክት የተወሰነ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታቀርበውን ጥያቄ "አደገኛ" ነው በማለት ውድቅ ያደረጉት ሚኒስትሩ "የድንበር መንጠቅ መርዛማ አጀንዳ" ሲሉ ኮንነውታል።
መስከረም 6/2018 ዓ.ም. ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን እርምጃ "ግልጽ የሆነ ጥቃት" በማለት ለኢትዮጵያ እና ለጎረቤቶቿ ጦስ እንደሚኖረው አስጠንቅቀው "ሊታለፍ የማይገባው ቀይ መስመር" መሆኑን ገልጸዋል።
ብዙም ሲናገር የማይደመጠው የኤርትራ መከላከያ ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዯጵያ መሪዎች ሕዝቡን ወደ ጦርነት አዘቅት መጎተት እንዲያቆሙ አስጠንቅቋል።
ጦሩ አክሎም "ቀይ መስመሩን የሚያልፍ ማንኛውም አካል ለመማር ዳግም ዕድል የማይሰጥ አዘቅት ውስጥ ራሱን እየከተተ ነው" ሲል አስጠንቅቋል።
ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች
ሁለቱን አገራት በሚያዋስኑ አካባቢዎች ግዙፍ የሆኑ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው ምንም የተዘገበ ነገር የለም።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵይ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ኢቲቪ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ አዲስ ምልምል ወታደሮች ሲመረቁ በተደጋጋሚ ያሳያል።
የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ሰው ኃይል ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ በቅርቡ በሰጡት ቃለምልልሰ ላይ ጦሩ "በአስተማማኝ ቁመና" ላይ እንደሚገኝ ተናግረው "በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች" እየተቀላቀሉት መሆኑን እና ይህም "ለጠላት መልዕከት" መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ያቀረቧቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተለያዩ ከፍተኛ የማዕረግ ዕድገት ተሰጥቷቸዋል።
ቅዳሜ መስከረም 10/2018 ዓ.ም. ወታደራዊ ሹመት ያገኙ ስድሳ ስድስት ከፍተኛ የወታደራዊ መኮንኖች ሲሆኑ፣ አራቱ የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።
ጦሩ በተጨማሪም አዲስ የተገኙ ወታደራዊ መሣሪያዎችን፣ ተተኳሾችን ጨምሮ ታንኮችን እንዲሁም የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን በብሔራዊ በዓላት ወቅት ለዕይታ አቅርቧል።
እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ትርዒት ወይንም ምላሽ ከኤርትራ ወገን አልተሰማም።
ይሁን አንጂ በኤርትራ አሁንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የሚሠለጥኑበት የብሔራዊ አገልግሎት እንደቀጠለ ነው።
ጥቅምት 5/2018 ዓ.ም. የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ የሆነው አሰና ቲቪ የኤርትራ መንግሥት በሠራዊቱ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል ባሉበት ምድብ እንዲቆዩ መታዘዛቸውን ዘግቧል።
"የኤርትራ ምንጮች ለአገሪቱ መከላከያ ኃይል አባላት፣ በምድባቸው ውስጥ እንዲቆዩ ጥብቅ መመሪያ መተላለፉን ነግረውናል" ብሏል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዘመቻ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባት ኢትዮጵያ የባሕር በር "ያጣችው" "ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ" መሆኑን እና መመለሱ የጊዜ ጉዳይ መሆኑን እየዘገቡ ነው።
የኢቲቪ የዜና ሽፋኖች ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ወደብ "ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ማጣቷን" በሚገልጹ እና ዳግም መልሶ የማግኘት ጉዳይ ላይ በሚሰጡ አስተያየቶች የታጀበ ነው።
ኢቲቪ አዳዲስ የሚመረቁ ወታደሮች ከማሳየት ባሻገር "ከግድቡ ወደ ወደቡ"፤ "አሰብ የእኛ ነው" ወይንም "አሰብ የኢትዮጵያ ነው" የሚል መፈክር የያዙ ሰልፈኞችንም ሲያቀርብ ነበር።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በባሕር በር ጉዳይ ያለውን አቋም የሚያሠራጩ አክቲቪስቶችን በባይነ መረብ ላይ ማሰማራቱን ይገልጻሉ።
የእነዚህ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ የተሰማሩ 'ዲጂታል አርሚ' ተብለው የሚጠሩ አክቲቪስቶች ቁጥር "60 ሺህ" እንደሚደርስ ተዘግቧል።
የኤርትራ መገናኛ ብዙኃን
የኤርትራ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በተለይ፣ ኤሪ ቲቪ ኢትዮጵያን "ከአስርት ዓመታት በፊት የተፈታን ጉዳይ ዳግም በማንሳት ዓለምን እያሳሳተች ነው" በማለት የሚወነጅሉ ርዕሰ አንቀጾችን እና አስተያየቶችን ያቀርባል።
ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም. የቀረበ ርዕሰ አንቀጽ የኢትዮጵያ መንግሥት "ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሕጋዊ በሆነ መልኩ የተፈታን ጉዳይ በመቀስቀስ" በሁለት አገራት መካከል ጦርነት ለመጫር እየሞከረ ነው ሲል ወንጅሏል።
የማስታወቂያ ሚኒስቴር ርዕሰ አንቀጽ ቦርድ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ተጠያቂ አትሆንም ሲል ጽፏል።
ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ባለቤትነት ጥያቄ ማንሳቷን ተከትሎ ከዚህ በፊት የኤርትራ መንግሥትን በመቃወም የሚታወቁ መገናኛ ብዙኃን ድምጸታቸውን እንዲቀይሩ አድርጓል።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው አሰና ቲቪ አጠቃላይ ተመልካቾቹን እና ኤርትራውያንን የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ከኤርትራ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።
መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው እና በተቃውሞ የሚታወቀው ሬዲዮ አረና በበኩሉ የኢትዮጵያን ጠብ አጫሪ መግለጫዎች ኮንኖ አቅርቧል።
ጦርነት ሊቀሰቀስበት የሚችልበት ዕድል
በ2016 ዓ.ም. የትግራይ ጦርነት ማብቃት አገሪቱ ከአውዳሚ ጦርነት እፎይታ ያገኘች ቢያስመስላትም መንግሥት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ከታጣቂዎች ጋር የሚያደርገው ውጊያ አሁንም ዋጋ እያስከፈለው ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ አሁንም በትግራይ በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ አልተተገበረም በሚል ውጥረት ነግሷል።
ኅዳር 5/2018 ዓ.ም. የአፋር ክልል የትግራይ ኃይሎች በወረዳው ቶንሳ ቀበሌ ላይ "በከፈቱት ጥቃት"፤ "ወደ 15 ኪሎ ሜትር ዘልቀው" መግባታቸውን እና "ስድስት መንደሮችን" መቆጣጠራቸውን በመግለጽ ከስሷል።
የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ "የከፈትነው ጥቃትም ሆነ የተቆጣጠርነው መሬት የለም" ሲል ውንጀላውን አስተባብሏል።
ኅዳር 7/2018 ዓ.ም. ደግሞ ህወሓት የፌደራል መንግሥቱ በአፋር ድንበር አካባቢ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መሰንዘሩን በመግለጽ ተዋጊዎቹ እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት የመቀስቀስ ዕድሉ የሰፋ ነው።
አዲስ አበባ፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግሥትን ተቃውመው ነፍጥ ያነሱ ኃይሎችን ትደግፋለች ሲል ይከስሳል።















