ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሉሴጉን ኦቦሳንጆ የተመራው የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች ከህወሓት አመራሮች ጋር ተወያዩ
በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦቦሳንጆ የተመራው የአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ሐሙስ ኅዳር 15/2015 ዓ.ም. ባደረጉት የመቀለ ጉብኝት ከህወሓት አመራሮች ጋር ተነጋገሩ።
የፕሪቶሪያውን ግጭት በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀለን የጎበኘው የልዑካኑ ቡድን፣ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እና የኅብረቱ የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዮን አካቷል።
የትግራይ ቴሌቪዥን በእንግሊዝኛ ባወጣው ዜና የህወሓት መሪ የሆኑት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በመቀለ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ልዑካኑን መቀበላቸውን አሳይቷል።
ዘገባው በተጨማሪም ዶክተር ደብረጽዮን በትግራይ በኩል የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ የትግራይ አመራሮች መሬት ላይ እያከናወኑት ያለውን ተግባር አስረድተዋል።
ከዚህም ውስጥ የሰላም ስምምነቱ ትልቅና ውስብስብ እንደመሆኑ መጠን የማኅበረሰቡም ስምምነት ስለሚያስፈልገው ሕዝቡን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የትግራይ ኃይል አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ለልዑካኑ ማስረዳታቸውን አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በኦባሳንጆ የሚመራው የልዑካን ቡድን ወደ ትግራይ መግባቱን ዘግቧል።
የኅብረቱ ተወካዮች በአዲስ አበባ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን አምባሳደር ወንድሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ የሰላም ስምምነት ዋነኛ እክል የኤርትራ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች ላይ በትግራይ ተወላጆች ላይ እየፈጸሙት ያለው መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት መሆኑንም ለልዐካኑ አስረድተናል ብለዋል።
“የኤርትራ ጦር ሕዝባችንን እየጨፈጨፈ ነው። መንደሮችን እየተቃጠሉ ነው። ንብረት እየተዘረፉ ነው። አላማውም እኛን ወደ ሌላ ጦርነት ለማስገባት ትንኮሳ እየፈጸመች ነው” ብለዋል።
የዚህ ስምምነት ተግባራዊ መሆን ዋነኛ ችግርም የኤርትራ ጦር መሆኑን እንዳስረዱ ገልጸው፣ ይህንንም ኃላፊነት መወጣት የኢትዮጵያ መንግሥትና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፣ በፕሪቶሪያም ይሁን በናይሮቢ በተደረጉ ውይይቶች የውጭ አገር ወታደሮችን ጨምሮ ሌሎችንም ጉዳዮች መወያየታቸውን ጠቅሰው “የትኛውም አገር የውጭ አገር በመሬቱ ላይ መኖሩን መቀበል የለበትም” ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭት የማቆም ስምምነት ኤርትራን በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን፣ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል።
ከሰሞኑም ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ የማታስወጣ ከሆነ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ጦር በተጨማሪ የአማራ ልዩ ኃይል እና የአፋር ሚሊሻ በትግራይ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት የሰላም ስምምነት ኃይሎቹ እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።
አምባሳደር ወንድሙ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከፌደራሉ መከላከያ ስምምነቱን ለመፈጸም ችግር የለውም ብለዋል።
ሆኖም ሰብዓዊ እርዳታ በተፈለገው መጠን እየገባ እንዳልሆነና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳልተመለሱ ጠቅሰው በቅርቡም እንደሚስተካከል ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የትግራይ ኃይሎች ተሰልፈውባቸው ከቆዩባቸው ግንባሮች የማስወጣት ሂደት (disengagement) በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንደሚጀመር የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።
ከናይሮቢው የትግበራ ዝርዝር ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫ የሰጡት ጄኔራል ታደሰ የሰላም ስምምነት ለታጣቂዎቻቸው የማስረዳት ሥራዎች እየተገባደዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይሄንን ተከትሎ አሁን ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች መውጣት እንደሚጀምሩ አመልክተዋል።
“ስምምነት ተደርጓል፤ ከዚያ በኋላ ‘ዲስኢንጌጅ’ ማድረግ፣ ሠራዊቱ ተጓጉዞ ወደ ትክክለኛው ቦታ እንዲገባ የማድረግ ሥራዎች በሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ይጀመራል” ብለዋል።
የትግራይን ወገን በመወከል በደቡብ አፍሪካውና በኬንያው ንግግር ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ባሳለፍነው እሁድ በሰጡት መግለጫ፣ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ነገር ግን የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች በትግራይ ውስጥ “አሰቃቂ ግፍ እየፈጸሙ ነው” ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፣ ለቀረበው ውንጀላ ከኤርትራም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ምላሽ የለም።
የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ታጣቂዎች በትግራይ ክልል ውስጥ መሆናቸው ለሰላም ስጋት ነው ያሉት ጄኔራል ጻድቃን ባስቸኳይ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
“ሁለቱም ኃይሎች በትግራይ መሬት ላይ ናቸው፤ ስምምነቱን የፈጸምነው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆኑ የተቀሩት ኃይሎች ከዚህ መውጣት አለባቸው” ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ባለፈው ወር መደረሱ ይታወቃል።
በዚህም የሰላም ስምምነት መሰረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሰረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ህገ መንግሥታዊ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።