ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ኃይሎች ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች መውጣት ይጀምራሉ - ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የትግራይ ኃይሎች ተሰልፈውባቸው ከቆዩባቸው ግንባሮች የማስወጣት ሂደት (disengagement) በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንደሚጀመር የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ በተደረጉ ድርድሮች በዘላቂነት ግጭትን ለማቆምና የትግራይ ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ለማድረግ መስማማታቸው ይታወሳል።
ጄኔራል ታደሰ ወረደ ማክሰኞ ኅዳር 13/2015 ዓ.ም. ለትግራይ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ባለፉት ሳምንታት ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ለታጣቂዎቻቸው የማስረዳት ሥራዎች እየተገባደዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይሄንን ተከትሎ አሁን ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች መውጣት እንደሚጀምሩ አመልክተዋል።
“ስምምነት ተደርጓል፤ ከዚያ በኋላ ‘ዲስኢንጌጅ’ ማድረግ፣ ሠራዊቱ ተጓጉዞ ወደ ትክክለኛው ቦታ እንዲገባ የማድረግ ሥራዎች በሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ይጀመራል።” ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካውን አጠቃላይ ስምምነት ተከትሎ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ናይሮቢ ላይ ባደረጉት ንግግር ትጥቅ በማስፈታት ዙሪያ ሊኖር ስለሚገባው አፈጻጸም ዝርዝር ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
በዚህም የጦር አዛዦቹ በስምንት ቀናት ውስጥ የትግራይ አመራሮች ለታጣቂዎቻቸው ማብራሪያ ለመስጠት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ሲደረግ ጎን ለጎን በክልሉ ያሉ ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች እንዲወጡ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በዚህም መሠረት የትግራይ ኃይሎች የሚጠበቅባቸውን እየፈጸሙ ነው ያሉት ጄኔራሉ “በእኛ በኩል መደረግ ያለበት ይከናወናል፤ በመንግሥት በኩልም ተመሳሳይ ነገር እየተደረገ ይሆናል” ብለዋል።
በተጨማሪም በሁለቱ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ የተኩስ አቁም መደረጉን አረጋግጠው፣ በዚህም የትግራይ ሕዝብ እና የትግራይ ኃይሎች ደስተኛ ናቸው ብለዋል።
“አንድ ተጨባጭ ለውጥ የተኩስ ልውውጥ መቆሙ ነው። በዚህ ደግሞ ሕዝቡ ደስተኛ ነው . . . ሠራዊቱም ደስተኛ ነው። ሲታኮስ የነበረው ሠራዊት በአንዳንድ አካባቢዎች በአካል ተገናኝቶ ሀሳብ የሚለዋወጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉም ጄኔራሉ ተናግረዋል።
የትግራይን ወገን በመወከል በደቡብ አፍሪካውና በኬንያው ንግግር ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ባሳለፍነው እሁድ በሰጡት መግለጫ፣ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ነገር ግን የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች በትግራይ ውስጥ “አሰቃቂ ግፍ እየፈጸሙ ነው” ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፣ ለቀረበው ውንጀላ ከኤርትራም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ምላሽ የለም።
የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ታጣቂዎች በትግራይ ክልል ውስጥ መሆናቸው ለሰላም ስጋት ነው ያሉት ጄኔራል ጻድቃን ባስቸኳይ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
“ሁለቱም ኃይሎች በትግራይ መሬት ላይ ናቸው፤ ስምምነቱን የፈጸምነው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆኑ የተቀሩት ኃይሎች ከዚህ መውጣት አለባቸው” ብለዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መሞታቸው ይነገራል።
ጦርነቱ ባስከተለው ቀውስ የተነሳ በትግራይ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ የሚጠብቁ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ባገረሸው ጦርነት ሰበብ ተቋርጦ የነበረው የእርዳታ አቅርቦት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መልሶ መጀመሩን የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች ገልጸዋል።