አቶ ጌታቸው እና ጄኔራል ጻድቃን ስለስምምነቱ በሰጡት መግለጫ ምን አሉ?

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተካሄደው ድርድር ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲያበቃ ተስፋ የሰነቀ ይመስላል።

ስምምነቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሲዋጉ የቆዩት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመታት ተቋርጠው የቆዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እና ሰብአዊ እርዳታ ያአለገደብ እንዲገባ የሚሉ መሠረታዊ ነጥቦች ይገኙበታል።

ይህንን ተከትሎ በቅርቡ የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ አዛዦች ኬንያ ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።

በትግራይ በኩል ተደራዳሪዎቹ እና የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ የቆዩ ሲሆን ከክልሉ ተወላጆች የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።

ይህንን ተከትሎም ከተደራዳሪዎቹ ዋነኞቹ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና አቶ ጌታቸው ረዳ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ ዕለት ኅዳር 11/2015 ዓ.ም. ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ምን ምን አነሱ?

በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተደረጉት ውይይቶች በተከታታይ ተደርገው በስምምነት ቢጠናቀቅም መጀመሪያው ከተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ በላይ ጊዜ ወስደዋል።

ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ድርድሩ የተለመደውን ዓለም አቀፍ የሰላም ድርድር መስፈርት የሳተ እንደነበረና የኢትዮጵያ መንግሥት መቀለ ከተማን በመቆጣጠር የውይይት ውጤቱን ለመቀየር ያልተሳካ ጥረት አድርጓል ብለዋል።

“በፕሪቶሪያ በቆየንባቸው አስር ቀናት መቀሌን በፍጥነት ለመቆጣጠር፣ መሬት ላይ አንድ ሀቅ ለመፍጠር እና የንግግሩን ከንቱ ለማድረግ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም። ከባድ የመጨፋጨፍ ጦርነት ተደርጓል። በሌላ በኩል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከመቀለ ከወጣን፣ የድርድሩ መንፈስ እንደሚቀይር እየነገረን ነበር። ሠራዊቱም ይህንን ያውቅ ነበር። በእነዚያ አስር ቀናት ውስጥ ከባድ የመከላከል ውጊያ ተደርጓል።”

እናም ተደራዳሪዎቹ ከስምምነት ላይ ሊደርሱ የቻሉት በጠንካራ “[የትግራይ ኃይሎች] የመከላከያል ጠንካራ አቋም እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት" መሆኑ ተናግረዋል።

“በጦርነቱ በርካታ ሰዎች እንደገና ተፈናቅለዋል። ሕዝባችንን መከላከል የማንችልበት ጦርነት ሊሆን ተቃርቧል” ያሉት ጄኔራል ጻድቃን፤ ሕዝቡን ለመታደግ የማዕከላዊ ዕእዝ ጦርነቱን በአስቸኳይ ለማስቆም ወስኗል።

በዚህም መሠረት ሁሉም ፍላጎቶቻቸው ባይሟሉም መሠረታዊ የተኩስ አቁም አላማቸውን ማሳካት መቻላቸው ተናግረዋል።

“አንደኛ ነገር ተኩስ ቆሟል። ተኩስ ማስቆም የፈለግንበት ዋናው ምክንያት ሕዝባችን ለመታደግ እና ወደ ውይይት ለመግባት ነው። እንዲሁም እርዳታ እንዲገባ፣ ተዘግተው የነበሩት አገልግሎቶች እንዲከፈቱ ነው። ስለዚህ በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የተኩስ ማቆም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተናል።”

ጄኔራል ጻድቃን በተጨማሪም የተከሰተው ችግር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለመፍታት የተደረገው ስምምነት ሌላ የንግግሩ መልካም ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የድርድሩ ተስፋዎች

አቶ ጌታቸው ረዳ የተኩስ አቁም ስምምነት በትግራይ ለተከሰቱ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት ይረዳል ብለዋል።

“ተኩሱ ቆሟል ማለት ብዙ መፈናቀልንና መከራን በመጠኑም ቢሆን እናስቆማለን። ይህን ማድረግ በራሱ አንድ ነገር ነው። . . . . በረሃብ እና በመድኃኒት እጦት ሊሞቱ ይችሉ የነበሩ ወገኖቻችን በመጠኑም ቢሆን መፍትሔ የሚያገኙበት ዕድል ይሰጣል። ከምንም በላይ ልንገባበት የወሰንነው የፖለቲካ ሂደት በታማኝነት ከተተገበረ፣ የችግሩን መንስኤዎች በሙሉ ወይም አብዛኛው ለማስወገድ እድሉ አለ።”

ጄኔራል ጻድቃን በበኩላቸው ስምምነቱ አገሪቱ ካለችበት አጣብቂኝ ውስጥ እንድትወጣ የሚረዳ ነው መሆኑን በመጥቀስ “ኢትዮጵያን ካለችበት ቀውስ የማዳን አቅም አለው። ይህ ትልቅ በረከት ነው። አገሪቱ ላይ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ እኛንም የሚጎዳ ትልቅ ችግር ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ላይ “ተነስተውብናል” ያሏቸውን ኃይሎች ለማስቀረት ዕድል እንዳለው በማመልከት፣ ንግግሩ የሚፈጥረው “ዕድል ከችግሮቻቸው በላይ ነው የምናየው” ብለው እንደሚያምኑ አንጸባርቀዋል።

ስጋቶች እና ጥርጣሬዎች

የትግራይ ከፍተኛ ተደራዳሪዎች ይህንን ተስፋ ሊያበላሹ የሚችሉ ስጋቶች ግን አሉ ብለዋል።

ሁለቱም ተወካዮች እዚህ ላይ ዋናው ፈተና የኤርትራ ጦር እና የአጎራባች ክልል ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደሆነም አስረድተዋል።

በናይሮቢው ስምምነት መሰረት የውጭ ኃይሎች እና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ታጣቂዎች ከትግራይ መውጣት የትግራይን ጦር ትጥቅ ሲፈታ በተመሳሳይ ጊዜ መሆን እንዳለበት ያትታል።

ነገር ግን የትግራይ ባለሥልጣናት የኤርትራን ሠራዊት ግድያ፣ አፈና እና ዘረፋን ጨምሮ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየፈጸሙ እንደሆነ ይከሳሉ።

ይህንን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ መንግሥታት በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።

“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደ ትልቅ ችግር የሚያየው የኤርትራን ጦር ነው። በትግራይም ሆነ በሌላ ቦታ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ስምምነቱን የማደናቀፍ ሚና ይኖረዋል። በአፋር ክልል ሚሊሻዎችን እና በአማራ ልዩ ኃይል ለማሰልጠን ላይ ነው። ለኢትዮጵያ ሰላም ደንታ የለውም” ሲሉ አቶ ጌታቸው ይከሳሉ።

ጄኔራል ጻድቃን በተመሳሳይ “[የኤርትራ መንግሥት] በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ ተጠቅሟል። ሌላውን ሁሉ አጥቷል” በማለት ለሰላም ድርድሩ ትልቁ ፈተና ሊሆን የሚችለው የኤርትራ መንግሥት እንደሆነ አመልክተዋል።

ለሁለት ዓመታት በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የቆዩት የሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ጥልቅ ጥርጣሬ ሌላው ፈተና መሆኑን ሁለቱም የትግራይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

“አንድ ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር ከሁለት ዓመታት ከባድ ውጊያ በኋላ ወደ ሰላም ሲገባ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም አይመጣም። የሽግግር ወቅት ያስፈልጋል፣ የሽግግሩ ጊዜ ደግሞ አዝጋሚ ነው” ሲሉ ሂደቱ ጊዜ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

ሰላም ዘላቂ ምርጫቸው እንደሆነ ያመለከቱት ጄኔራል ጻድቃን እና አቶ ጌታቸው፣ “ሰላም ስትራተጂካዊ ምርጫችን ነው ወይንስ ጊዜ የምንግዛበት ታክቲክ ነው?” በማለት ጥያቄ ያነሱት አቶ ጌታቸው፤ “ይህ ጉዳይ ‘ታክቲካል ነው’ ብለን ከተነሳን፣ ለእኛም ሆነ ለጠላት ከሚያመጣው አደጋ በስተቀር ምንም ጥቅም ሊኖር አይችልም” ብለዋል።