ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አገር አልባ ሆነው ለቆዩ የአንድ ጎሳ አባላት የኬንያ መንግሥት የዜግነት እውቅና ሰጠ
ከታንዛኒያዋ ደሴት በመፍለስ ለዘመናት ኬንያ ውስጥ አገር አልባ ሆነው ለቆዩት የፔምባ ማኅበረሰብ አባላት የኬንያ መንግሥት በይፋ እንደ አንዱ የአገሪቱ የጎሳ ቡድን አድርጎ በመቀበል ዜግነት ሰጠ።
በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኩል ይፋ የተደረገው የኬንያ መንግሥት ውሳኔ የተሰጠው የፔምባ ማኅበረሰብ አባላትን እንደ አገሪቱ ዜጎች እንዲቆጠሩ የተለያዩ ወገኖች ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
ፕሬዝዳንት ሩቶ እንዳሉት በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ኮሚቴዎች በኩል በተደረገው ግፊት ምክንያት መንግሥታቸው ለማኅረበረሰቡ አውቅናው ተሰጥቷል ብለዋል።
ይህ ለፔምባ ጎሳ አባላት የተሰጠው የኬንያ ዜግነት ማኅበረሰቡ ከሌላው የኬንያ የጎሳ ቡድኖች አንጻር እኩል እንዲታዩ በማድረግ፣ ዜጎች የሚያገኟቸውን የትምህርት፣ የጤና፣ የማኅበራዊ ጥበቃ፣ የገንዘብ እና የሥራ ዕድልን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።
ከዘመናት በፊት ቀደምቶቻቸው ከዛንዚባር በመምጣት በኬንያ የባሕር ጠረፍ አካባቢ ግዛቶች በሆኑት በክዋሌ፣ በኪሊፊ፣ በሞምባሳ እና በላሙ ውስጥ በመስፈር አገር አልባ ሆነው የቆዩት የፔምባ ማኅበረሰብ አባላት 8,000 በላይ ይሆናሉ።
እነዚህ የፔምባ ጎሳ አባላት በባሕር ዳርቻዎች አካባቢ በመስፈራቸው አብዛኞቹ ወደ ጥልቁ ውቅያኖስ በመቅዘፍ በዓሳ ማስገር እንዲሁም ለቀለባቸው በሚሆን ውስን የግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ ቆይተዋል።
የማኅበረሰቡ አባላት ለዘመናት በኬንያ ውስጥ የአገሪቱ ዜግነት መታወቂያ ሰነድ ስላልነበራቸው በፖሊሶች እና በባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች መንገላታት እንደሚፈጸምባቸው ሲያማርሩ ቆይተዋል።
የኬንያ መንግሥት ለማኅበረሰቡ አባላት የዜግነት እወቅና እንዲሰጥ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እና የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ቡድኖች ውሳኔውን አድንቀዋል።
እነዚህ የፔምባ ጎሳ አባላት በሱልጣን ቢን ኻሊፋ የሥልጣን ዘመን በ1800ዎቹ ገደማ ከዛንዚባር ደሴት ፈልሰው የመጡ ማኅበረሰቦች የልጅ. . .ልጆች መሆናቸውን ይናገራሉ።
የኬንያ መንግሥት በስደት እና በፍልሰት በአገሩ ውስጥ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የዜግነት እውቅናን ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከዚህ በፊትም ለረጅም ዘመናት በኬንያ ውስጥ በመኖራቸው የተነሳ አገር አልባ ሆነው የቆዩት ማኮንዴ፣ ሾና እና የደቡብ አስያ ማኅበረሰቦች እንደ አገሪቱ ጎሳ ተቆጥረው የዜግነት እውቅናን አግኝተዋል።