ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የትግራይ ነዋሪዎች ሰቆቃ
ትግራይ ሰላም ከራቃት ድፍን ሁለት ዓመታት ተቆጠሩ።
ለሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፣ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ ለህሊና የሚከብዱ ፣ ለሰሚው የሚሰቀጥጡ ጭካኔዎች ተፈጽመዋል።
በፌዴራሉ መንግሥት እና በትግራይ ሃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ክልሏን ጨለማ ውስጥ ከቷታል።
ትግራይ ከመሰረታዊ አገልግሎቶች ጋር ተቆራርጣለች።
በክልሉ ሰላም ብቻ ሳይሆን ለዕለተ’ለት ኑሮ ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶች የሉም።
ትምህርት፣ የኤሌክትሪክና የነዳጅ አቅርቦት እንዲሁም የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት ተቋርጧል።
መሰረታዊ ልማቶች ወድመዋል፤ የግብርና ስራ ፣ የጤና ስርዓት፣ መንግስታዊ አገልግሎቶች ተስተጓጉለዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለረኃብ ተጋልጠዋል፤ በመድኃኒት እጦት ብዙዎች እየሞቱ ነው።
መሰረታዊ አገልግሎቶች በተዘጉባት ትግራይ ያሉ ነዋሪዎች በከፍተኛ ፈተናም ኑሯቸውን ለመግፋት ተገደዋል።
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
ከሁለት ዓመታት በፊት ጥቅምት 24 የተቀሰቀሰው ደም አፋሳሹን የርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ተፋላሚ ወገኖች በተለያየ ደረጃ “ለጆሮ የሚከብዱ” የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ተስምቷል።
ከሳምንታት በፊት የተባበሩት መንግስት ድርጀት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው እና በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው ኮሚሸን ይፋ ባደረገው ቀዳሚ ሪፖርት የተፈጸሙት መጠነሰፊ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም አመላክቷል።
ረሃብና የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ማደነቃቀፍ እንዲሁም መደፈር እንደጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ጠቁሟዋል።
በአስከፊ ሁኔታ የተፈጸመ መደፈርና ወሲባዊ ጥቃት መድረሱን ያተተው ሪፖርቱ ጦርነቱ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ሁሉ ተመሳሳይ ጥቃት የደረሰ ቢሆንም በትግራይ የተፈጸሙት ከሁሉም የከፋ እና በጭካኔ የተሞላ ነው ብሏል።
እነዚህ መደፈሮች እና ጥቃቶች የደረሱት ደግሞ መከላከያ ሰራዊት ትግራይን በተቆጣጠረበት ጊዜ መሆኑን አመላክቶ ጥሰቶቹን የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦር ሃይሎቸ እንዲሁም የፋኖ አባላት መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ በወጣበት ወቅት በምዕራብ ትግራይ መደፈርና ወሲባዊ ጥቃቶችም መቀጠሉንም ዝርዝሯል።
በተመሳሳይ የትግራይ ኃይሎችም መደፈርና ወሲባዊ ጥቃቶች በተቆጣጠሯቸው የአማራ እና አፋር አከባቢዎች መፈፀማቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ሪፖርት ውድቅ ያደረገው ሲሆን “በምርመራ ሪፖርት ስም ፖለቲካዊ መግለጫ ነው” ሲል አጣጥሎታል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ከስድስት ወራት በኃላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹን በተመለከተ “ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ አለ” ቢሉም በትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸሙን አምነዋል።
"እኛ ወታደሩን የላክነው ወንጀለኞችን እንዲቆጣጠር እንጂ እንዲደፍር አይደለም። በዚህ ወንጀል የተሰማራ ወታደር ካለ በሕግ ተጠያቂ ይደረጋል" ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እና አጋሮቻቸው መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ምግብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ አውድመዋል ሲል በተመድ ሰብአዊ ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚሽን በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት አመላክቷል።
በሌላ በኩል በምዕራብ ትግራይ በሰብአዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ መፈጸሙን ሁለት ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በጣምራ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጡት በዚህ ሪፖርት ላይ ከአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚነሱ የጸጥታ ኃይሎችና ባለስልጣናት በትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት እየፈጸሙ መሆኑን አመላክተዋል።
እነዚህ ጥቃቶች በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የጦር ወንጀሎችን ናቸው ብሏል ሪፖርቱ።
ሆኖም የፌዴራሉ እና የአማራ ክልል መንግስታት ሪፖርቱን አንቀበለውም ብለዋል።
አምንስቲ ኢንተርናሽናል በ2013 አጋማሽ በተናጠል ባወጣው ሌላ ሪፖርት ደግሞ ከተለያዩ የጤና ተቋማት ያሰባሰበውን መረጃ መሠረት በማድረግ በሶስት ወራት ብቻ በትግራይ1 ሺህ 2 መቶ 88 የመድፈር ጥቃቶች የተፈጸመባቸው ተጠቂዎች ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ሄደው ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልጿል።
ይህ አሃዝ ወደ ጤና ተቋማት የሄዱትን ብቻ የሚመለከት በመሆኑ በዚያ ወቅት በትግራይ ከተደፈሩ ትክክለኛ የሴቶችን ቁጥር የማያንጸባርቅ ነው።
በተጨማሪም ሪፖርቱ በትግራይ ሴቶች በደቦ እንደተደፈሩ፣ ለወሲብ ባርነት እንተዳረጉና ባዕድ ቁሶች አካላቸው ውስጥ የተከተተባቸውና በኤችአይቪ የተያዙ ሴቶችም እንዳሉ አትቷል። ይህንን ጥቃት የፈጸሙት የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የአማራ ኃይሎችና የፋኖ አባላት መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ይህንን ሪፖርት ተከትሎ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ አግነስ ካላማርድ በሰነዘሩት አስተያየት “በትግራይ ሴቶች ላይ ዘላቂ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ለማድረስ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸው ግልጽ ነው” ብለዋል።
የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በትግራይ ክልል ብቻ አልተገታም።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኃላ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የትግራይ ተወላጆች ማንነትን መሰረት ላደረገ እስር እንደተዳረጉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና ዓለም አቀፍ የመብት ተቋማት አረጋግጠዋል። አውግዘዋል። በአስቸኳይ እንዲቆምም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የትግራይ ተወላጆችን በዘፈቀደ ማሰር፣ መሰወር እንዲሁም ሌሎች በደሎች መፈጸማቸውን የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ያስረዳል።
የትግራይ ሃይሎች የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ወደ ዋና ከተማዋ እያመሩ በነበረበት ወቅት የፌዴራሉ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ብሄርን መሰረት ያደረገ እስር ይፈጸም እንደነበር ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ አስቸኳይ አዋጁ በስራ ላይ በዋለበት ወቅት ከህዳር እስከ የካቲት ወር ብቻ ከ15 ሺህ በላይ የሚገመቱ የትግራይ ተወላጆች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል። ሮይተርስ በበኩሉ ታስረው የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን በማናገር እና የሳተላይት ምስሎችን በመገምገም የታሰሩ ሰዎች ተመድ ካወጣው ቢያንስ በ3 ሺህ እንደሚበልጥም አስነብቧል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ሰዎች ከሥራ ቦታቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም ከመንገድ ላይ ጭምር ተይዘው በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ኢሰመኮ በወቅቱ ገልጾ ነበር።
ይህም ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች ምግብ፥ ልብስን እና መሠረታዊ ቁሳቁሶችን ለታሰሩ ሰዎች ለማቀበል ብሎም የታሰሩ የቤተሰብ አባላትን ለመጠየቅ እንዳልቻሉ ካመላከተ በኃላ ህጻናት ልጆች ያሏቸው እናቶች፥ የህክምና ክትትል የሚፈልጉ እና ለተለያዩ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ጭምር መታሰራቸው ተገልጾ ነበር።
በሌላ በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የትግራይ እና የአፋር የድንበር ከተማ ከሆነችው አብአላ ታፍሰው ወደ ሰመራ ከተወሰዱ በኃላ በቂ የጤና አገልግሎት እና እርዳታ በሌለበት ማቆያ ውስጥ መስፈራቸው ተዘገቦ ነበር።
በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በማቆያው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በማቆያው ላይ የሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል።
በክልሉ የተከሰተው የጤና ቀውስ
ጦርነቱ እና ተከትሎት የመጣው የትግራይ ከመሰረታዊ አግልገሎት መነጠል የጤና ስርዓቱን ክፉኛ ጎድቶታል።
እገዳ ላይ ባለችው ትግራይ መሰረታዊ የመድኃኒት እጥረት ህሙማንን እየገደለ ነው።
በባለፈው ሳምንት አርብ በክልሉ የነበረው ውስን ክትባት፣ ህመም ማስታገሻ እና ኢንሱሊን የመሳሳሉ መድኃኒቶች ተሟጦ ማለቁን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
በህክምና መዳን በሚችሉና መከላከል በሚችሉ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምርም እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በክልሉ በተጣለው እገዳ መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች ማስገባት እንዳልቻለ ከዚህ ቀደም ያስታወቀው ተቋሙ ለወራት ከዘለቀው ከተኩስ አቁሙ ጋር ተያይዞ የተወሰነ እርዳታና መድኃኒትም መግባት ችሎ ነበር።
በትግራይ ከሚገኙ የጤና ማዕከላት ውስጥ 9 በመቶው ብቻ እየሰራ እንደሆነና እነዚህም በነዳጅ እጥረት ችግር ውስጥ መሆናቸውን የተቋሙ ኃላፊዎች በባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጄኔቫ ላይ በነበረ መግለጫ ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቡድን መሪ ኢልሀም አብደልሃይ ኑር በትግራይ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ህፃናት “አስደንጋጭ” ያሉት ሲሆን ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ህጻናት መካከል አንዱ በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃይም ገልጸዋል።
በክልሉ ያለውን የጤና ቀውስን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚናገሩት የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም “የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ ቀውስ የሚገባውን ትኩረት እንዲሰጠው እጠይቃለሁ። በአሁኑ ወቅት የዘር ማጥፋትን ለመከላከል ጠባብ እድል አለ “ ብለዋል
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ወይም ኤምኤስኤፍ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በትግራይ ክልል በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ላይ ሆን ተብሎ መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸሙን በ2013 አጋማሽ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
ኤም ኤስ ኤፍ በትግራይ 106 የሕክምና ተቋማት ላይ ምልከታ ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ላይ ዘረፋ እንደተፈፀመባቸው ገልጿል። አንዳንዶቹ ዘረፋዎች የተፈፀሙት በወታደሮች ጭምር ነው ብሏል።
ምልከታ ካደረገባቸው ውስጥ 13 በመቶ የሚሆኑት የጤና ተቋማት ብቻ የሚጠበቅባቸውን ማከናወን ይችላሉ ሲል ገልጿል።
ኤም ኤስ ኤፍ በትግራይ ምልከታ ከደረገባቸው የጤና ተቋማት 65 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ እና ባለሙያዎች የሌሉባቸው ናቸው።
የኤምኤስኤፍ ዋና ዳይሬክተር ኦሊቨር ቤን ይህንን በዚህ መግለጫ በተካተተ አስተያየታቸው "በትግራይ የጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው" ብለዋል።
በትግራይ በከፋ የምግብ እጥረት ምክንያት በየቀኑ ህጻናት እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ደርጅት ይፋ አድርጓል።
በትግራይ የጤና ተቋማት ላይ በደረሰ ውድመት፣ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር እንዲሁም ለህይወት አስጊ የሆኑ በሽታዎችን ለማከም የሚውሉ መሃኒቶች አቅርቦት በመቋረጡ በርካቶች ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል።
በመቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታልም በዚህ ችግር እየተፈተነ ሲሆን መሰረታዊ የህክምና አግልግሎቶችን ለማቆም ተገዷል።
ለአብነት የስኳር በሽታን እንመልከት።
በትግራይ ውስጥ 27 ሺህ የሚጠጉ ህሙማን በአፍ በሚወሰድ እንክብል ወይም በመርፌ በሚሰጥ መድሃኒት ህይወታቸውን እንደሚያስቀጥሉ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ገብረስላሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች ነው።
አይደር በክልሉ ትልቅ የሚባለው ሆስፒታል ነው። ሆስፒታሉ ለእነዚህ ታካሚዎች ከማዘን በስተቀር ማድረግ የሚችለው ነገር አለመኖሩን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
በዚህም በየሳምንቱ እስከ 12 ሰው ሕይወቱ ያልፋል።
በትግራይ የጤና ስርዓቱ መቃወስ ክፉኛ ከጎዳቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ህጻናት ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ከትግራይ ጤና ቢሮ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት በክልሉ ክትባቶችን የሚያገኙ ልጆች ቁጥር ከ10 በመቶ በታች ማሽቆልቆሉን ባለፈው ሳምንት ገልጿል።
“ጨቅላ ሕጻናት እና የልጆች ክትባትን ጨምሮ ሕይወት አድን የሆኑ መድኃኒቶች እና የሕክምና አቅርቦቶች እንዳያገኙ በመደረጋቸው” ለተለያዩ በሽታዎች መጋለጣቸውን አስረድቷል።
ይህም የኩፍኝ፣ የተቅማጥ፣ የማጅራት ገትር፣ የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮ እና የመሳሰሉ ወረርሽኞች በክልሉ ማስከተሉንም ጠቁሟል።
የኩፍኝ ወረርሽኝ በትግራይ የተለያዩ አከባቢዎች መከሰቱን የገለጸው ቢሮው ከአራት ዓመታት በፊት በጨቅላ ሕጻናት ላይ የሚከሰት ‘ቲታነስ’ የተባለ በሸታ ዜሮ ደርሶ የነበረ ሲሆን አሁን 25 ህጻናት ላይ መከሰቱን አስታውቋል።
በሌላ በኩል ቢቢሲ ከትግራይ ጤና ቢሮ ያገኘው መረጃ ባለፉት ሁለት ዓመታት በምግብ እጥረት ምክንያት የሞቱ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ጨቅላዎች ጦርነቱ ከመጀመሩ አራት ወራት በፊት ከነበረው ሁኔታ በ1 ሺህ 533 በመቶ እንደጨመሩ ያሳያሉ።
ከሐምሌ 2013 ሐምሌ 2014 ዓ.ም ድረስ 2 ሺህ 450 ሕጻናት በሆስፒታል ውስጥ መሞታቸው ታውቋል።
በትራንስፖርት ችግር እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለመኖርን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች መረጃን ማሰባሰብ ለክልሉ ከባድ ሆኗል። በዚህም ሳቢያ ይህ አሃዝ በመሬት ካለው እውነታ እጅግ እርቆ እንደሚገኝ ይታመናል።
በሌላ በኩል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኃላ በአማራ እና አፋር ክልሎች ከ 1 ሺህ 500 በላይ የጤና ተቋማት በትግራይ ሃይሎች ስለመዘረፉ እና መውደሙ ጤና ሚኒስቴር አሳውቋል።
ረሃብና የምግብ እጥረት በትግራይ
በትግራይ ጦርነቱ እና የተጣለው እገዳ የከፋ የምግብ እጥረት እንዲሁም ርሃብ አስከትሏል። በዚህም ምክንያት ምግብ እስከመለመን የደረሱ ዶክተሮች እና ነርሶችን ቢቢሲ አነጋግሯል።
ይህ አንድም በክልሉ የእርሻ ስራ በመስተጓጎሉ ሌላም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ እገዳ ተጥሎ በመቆየቱ ሳቢያ የተከሰተ ነው።
በትግራይ በርሃብ ምክንያት ሰዎች እና እንስሳት እየሞቱ እንደሆነ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኋላፊ ዶ/ር አትንኩት መዝገቦ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከ8 ወራት ገደማ በኃላ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የተመድ የህጻናት አድን ድርጅቱ ዩኒሴፍ ባወጡት መግለጫ ነው በትግራይ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዋሪ በአፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አመላክተው ነበር።
የመንግስታቱ ድርጅት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታንም አስመልክቶ "በአስርት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ አስከፊው የረሃብ ሁኔታ" እንዲቀለበስ ከተፈለገ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ እርዳታ ሊቀርብላቸው እንደሚገባም አሳስቧል።
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ "ትግራይ ውስጥ ረሃብ መከስቱን ይፋ አድርገው ነበር።
አስተባባሪው በንግግራቸው ትግራይ ውስጥ ወደ 353,000 የሚጠጉ ሰዎች ደረጃ አምስት የሚባለው (catastrophe) ማለትም የከፋ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙና፤ ተጨማሪ 1.769 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ደረጃ አራት የሚባለው (emergency) ማለትም አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያሻቸው ጠቁመዋል።
የፌዴራል እና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም አጋሮቻቸው በትግራይ ከብቶችን እንደገደሉ እና ምግብ እንደወደሙ ተመድ የቋቋመው የሰብአዊ መብት ጥሰት አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት አመላክቷል።
በሌላ በኩል በ2013 በሰኔ ወር ላይ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ትግራይ በተመለከተ ባደረገው ዝግ ስብሰባ ላይ ማርክ ሎውኮክ ያደረጉት እና ቢቢሲ የደረሰው ንግግር በትግራይ ርሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ውሏል ብለዋል።
ሃላፊው "ሴቶችንና ታዳጊዎችን በተቀናጀ ሁኔታ በመድፈር ለማሸበርና ለማሰቃየት እየተጠቀሙበት ነው። የኤርትራ ወታደሮች ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው። የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ይከበባሉ፣ ይደበደባሉ እንዲሁም ማስፈራሪያዎች ይደርሳቸዋል" ብለዋል።
በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት ነሃሴ ላይ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል በህብረቱ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በትግራይ ያለውን ጦርነት የተዘነጋ ነው ብለውታል።
ሃላፊው ለሁለት ዓመታት ያህል የትግራይ ክልል ረሃብ እና ወሲባዊ ጥቃት "ምግብ፣ መድኃኒት፣ መብራት፣ ቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት መንፈግ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው" ብለዋል።
ሆኖም የፌዴራሉ መንግስት ይህንን አይቀበልም። በ2013 ምርጫ ወቅት በበሻሻ ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “በትግራይ ርሃብ የለም” ብለዋል።
ምንም እንኳን ባለፈው ነሃሴ ዳግም ባገረሸው ጦርነት የሰብአዊ እርዳታ ቢቋረጥም ከዚያ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ውስን መሻሻሎች ታይተውበት ነበር።
በትግራይ ይህንን ሁሉ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሁለት ዓመታት ደፍኗል። በነዚህ ዓመታት ንጹሃን ተገድለዋል፣ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተሰምተዋል፣ በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ የክልሉ የጤና ስርሃት ክፉኛ ተቃውሷል፣ ወሳኝ አገልግሎቶችም ተቋርጧል። ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል ወይም መቼ እንደሚያበቃ የማያውቁ ንጹሃን ደግሞ መከራቸው እንደቀጠለ ነው።