በጅግጅጋ አየር ማረፊያ የምክር ቤት አባሏን የገደለው የፖሊስ አባል ሞት ተፈረደበት

ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑትን ወ/ሮ ጁዋሪያ መሐመድ ሱብእስ ጅግጅጋ አየር ማረፊያ ውስጥ ተኩሶ የገደለው የፌዴራል ፖሊስ አባል በሞት እንዲቀጣ ተፈረደበት።

ትናንት በጅግጅጋ ከተማ የጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩትን ጁዋሪያ መሐመድን በመግደል ተጠርጥሮ ክስ የተመሰረተብት የፌደራል ፖሊስ አባል በሞት እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን፣ ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ ይጋባኝ የማለት መብት እንዳለውም አመላክቷል።

ወ/ሮ ጁዋሪያ መሐመድ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላ ከመሆናቸው በተጨማሪ የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ።

በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ ውስጥ በሚገኘው ገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ ውስጥ የፖሊስ አባሉ በከፈተው ተኩስ ወይዘሮ ጁዋሪያ ወዲያው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ አህታቸውን ጨምሮ ሌሎች አራት ሰዎች ላይ መቁሰል ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው የሞት ቅጣት ውሳኔን ተከትሎ የሟች እህት የሆኑትን ፈሂማ መሐመድ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት የተሰጠው ፍርድ ተገቢ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

“መቼም በሰው ሞት የሚደሰት ያለ አይመስለኝም። ይሁንና እያንዳንዱ ሰው በሰራው ወንጀል በሕግ መቀጣት አለበት። እንደ ቤተሰብ ውሳኔው ብርታት ሆኖናል። ይህ ውሳኔ ደግሞ የሚያሳየው መንግሥት፣ ሕዝብ እና ሕጉ ከእኛ ጎን እንደሆኑ ነው።”

በጥቃቱ ከምክር ቤት አባሏ ግድያ በተጨማሪ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ከገቡት ሰዎች መካከል የክልሉ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መሐመድ አብዱረሺድ መሐመድ ኡመር ይገኙበት ነበር።

በአየር ማረፊያው በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የፖሊስ አባል ለፈጸመው ጥቃት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ግን ፖሊሱ ከሌሎች የአየር ማረፊያው የጥበቃ አባላት ጋር ሲነታረክ እንደነበር በወቅቱ ተናግረዋል።

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በምትገኘው የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ ውስጥ የሚገኘው የገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ለሰዓታት ሥራው ተቋርጦ ነበር።