ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ሲቲ፤ ሪያል ማድሪድን ‘ረምርሞ’ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ደረሰ
ማንቸስተር ሲቲ የአምና የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድን በሰፊ ውጤት በመርታት ለፍፃሜ ደርሷል።
ምሕረት የለሽ ሆኖ ብቅ ያለው ሲቲ በሜዳው የስፔኑን ኃያል ክለብ ከውድድሩ ውጭ በማድረግ በፍፃሜው ከኢንተር ጋር እንደሚገናኝ አረጋግጧል።
ሲቲ ከዚህ ቀደም ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በግማሽ ፍፃሜው በማድሪድ ተረትቶ ከውድድሩ ቢሰናበትም ዘንድሮ ግን ኃያል ሆኖ ቀርቧል።
ጠጠር መጣያ ባልነበረበት የኤቲሃድ ስታድየም ሪያል ማድሪድን የገጠመው የፔፕ ቡድን የአውሮፓ ዋንጫ ለማንሳት 90 ደቂቃዎች ብቻ ይቀሩታል።
የአውሮፓ ዋንጫ ልሂቃን የሚባሉት ሪያል ማድሪድ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በጨዋታ ተበልጠው ነበር።
ሲቲ፤ በሚቀጥለው ቅዳሜ ከቼልሲ ጋር ያላቸውን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ግጥሚያ ካሸነፉ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።
በአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ከኢንተር ሚላን የሚገናኘው ሲቲ፤ ሃገር ቤት በኤፍ ኤ ዋንጫ ማንቸስተር ዩናይትድን ይገጥማል።
ማንቸስተር ሲቲ ሶስቱንም ዋንጫ ማንሳት ከቻለ ከማንቸስተር ዩናይትድ ቀጥሎ ሁለተኛው የእንግሊዝ ክለብ ይሆናል።
በረቡዕ ምሽቱ ፍልሚያ የማድሪዱ ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮርቱዋ በመጀመሪያው አጋማሽ የሃላንድን ሁለት የጭንቅላት ኳሶች በማዳን መረቡን ቢያስጠብቅም ከቆይታ በኋላ በርናንዶ ሲልቫ የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ስታድየሙን በደስታ ነቅንቋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ስምንት ደቂቃዎች ሲቀሩት በርናንዶ ሲልቫ ከሙከራ ተሸራርፎ የተመለሰ ኳስ በግንባሩ ጎል በማድረግ የሲቲን መሪነት አጠናክሯል።
ከእረፍት በኋላ ሪያል ማድሪድ ተሻሽሎ ቢመለስም የማድረድ ተጫዋቾች ያደረጓቸው ሙከራዎች በሲቲው ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ተመልሰዋል።
ከደቂቃዎች በኋላ የሲቲ ተከላካይ ኢማኑዔል አካንጂ ከቅጣት ምት የተሻገረ ኳስ በግንባሩ ወደ መረብ ሲሰድ የማድሪዱ ተከላካይ ኤደር ሚሊታዎን ጨርፎ ጎል መሆን ችሏል።
በመገባደጃው ደቂቃ አርጀንቲናዊው አጥቂ ጁሊያን አልቫሬዝ የማሳረጊያውን ጎል በማስቆጠር ሲቲ 4 ለምንም እንዲረታ አስችሏል።
ማንቸስተር ሲቲ ከኢንተር ሚላን ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ከምሽቱ አራት ሰዓት በኢስታንቡል የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲቲዎች ሶስቱን ዋንጫዎች ካነሱ ጎረቤቶቻቸው ዩናይትድ በፈረንጆቹ 1999 ያደረጉትን ታሪክ መድገም ይችላሉ።
ከእንግሊዝ ክለቦች ማንቸስተር ዩናይትድ ብቻ ነው በአንድ የውድድር ዘመን የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚዬር ሊግ እና ኤፍ ኤ ዋንቻ ማንሳት የቻለው።
የአርሰናልን ቅስም በመስበር የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት የተቃረቡት ሲቲዎች ይህን ታሪክ ለመድገም ኢንተር ሚላን እና ማንቸስተር ዩናይትድን መርታት ይጠበቅባቸዋል።