ሃሪ ኬን ወደ ፒኤስጂ? የኪሊያን ምባፔና ሊዮኔል ሜሲ ዕጣ ፈንታስ?

የፓሪስ ሴይን-ዠርሜይን የእግር ኳስ አማካሪ ሉዊዝ ካምፖስ የ29 ዓመቱ ሃሪ ኬንን አግኝተው እንዳናገሩት የፈረንሳዩ ‘ፉት መርካቶ’ ጋዜጣ አስነብቧል።

ካምፖስ ተጫዋቹ እና ተወካዮቹን አግኝተው ኬን ወደ ፒኤስጂ እንዲመጣ ጎትጉተዋል ብሏል ጋዜጣው።

በሌላ በኩል ሪያል ማድሪድ ምባፔ፣ አልፎንሶ ዴቪስ እና ጁድ ቤሊንሃምን በሚመጣው ክረምት ሊያስፈርም እንደሚሻ ‘ስካይ ስፖርት’ ፅፏል።

የ24 ዓመቱን ፈረንሳዊ አጥቂ ምባፔ፣ ካናዳዊው የ22 ዓመቱ የባየርን ሙኒክ ተከላካይ ዴቪስ እና የ19 ዓመቱ እንግሊዛዊ የዶርትመንድ አማካይ ወደ ስፔኑ ክለብ ያቀኑ ይሆን ወይ የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል።

ቶተንሃም የፌይኖርዱን የ44 ዓመት አሠልጣኝ አርን ስሎትን ለማስፈረም ቢፈልግም ክለቡ ግን አዲስ ውል ሊያቀርብለት እንደሆነ ተሰምቷል።

‘ፉትቦል ትራንስፈር’ እንደፃፈው ከሆነ ደግሞ ባርሴሎና፤ ሊዮኔል ሜሲ እና ኔይማርን በክረምቱ መስኮት መልሶ ማስፈረም ይፈልጋል።

የ35 ዓመቱ ሜሲ እና የ31 ዓመቱ ኔይማር በቅርቡ ከፒኤስጂ ደጋፊዎች ተቃውሞ እንደገጠማቸው ይታወሳል።

በማንቸስተር ሲቲ ቤት ከአንድ ዓመት በላይ ውል እንዲራዘምለት የሚፈልገው ኢካይ ጉንዶዋን በአርሰናል እና በባርሴሎና ይፈለጋል።

የ32 ዓመቱ ጀርመናዊ አማካይ ከሲቲ ጋር ያለው ውል እየተገባደደ መሆኑን፣ ነገር ግን ውሉ ከአንድ ዓመት በላይ ሊራዘምለት እንደማይችል የፃፈው የጀርመኑ ‘ስፖርት ቢልድ’ ጋዜጣ ነው።

‘ታይምስ’ እንዳስነበበው ባየርን ሙኒክ የ31 ዓመቱ ሴኔጋላዊ አጥቂ ሳዲዮ ማኔን በሚመጣው ክረምት መሸጥ ይፈልጋል። አልፎም ከማንቸስተር ሲቲ በውሰት የሄደው የ28 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ጃዎ ካንሴሎን ወደ እንግሊዝ መመለስ እንደሚፈልግ ተሰምቷል።

የጀርመኑ ክለብ ባየር ሌቨርኩሰን የ30 ዓመቱን ስዊትዘርላንዳዊ የአርሰናል አማካይ ግራኒት ዣካን በ13 ሚሊዮን ፓውንድ የግላቸው ማድረግ ይፈልጋሉ ይላል የ‘ስታንዳርድ’ ዘገባ።

ወደ እንግሊዝ ስንመለስ ቶተንሃም የብሬንተፈርዱን ስፔናዊ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ ለማስመጣት ጥረት ላይ ነው። የ27 ዓመቱ ራያ የቶተንሃሙን አምበል ኡጎ ሎሪን እንዲተካ ነው ክለቡ ሊያስፈርመው የሚሻው።

የሮማው እንግሊዛዊ አጥቂ ታሚ አብራሃማ ወደ ቼልሲ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጮች ጠቁመዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድም ተጨዋቹን ማስፈረም ከሚፈልጉ ሌሎች ክለቦች መካከል ናቸው።

የ37 ዓመቱ የሊቨርፑሉ አማካይ ጄምስ ሚልነር በእንግሊዝ ክለቦች እየተፈለገ ነው። ሊድስ ዩናይትድ ከሊጉ ከመውረድ ከተረፈ ተጨዋቹን ሊያስፈርምት ይችላሉ። ብራይተንም ጉምቱውን አማካይ ለማስፈረም እንደሚፈልግ ተሰምቷል።

የበርንሊ አሠልጣኝ ቪንሴንት ኮምፓኒ የ23 ዓመቱን ቤልጂየማዊ አማካይ ሳምቢ ሎኮንጋን ማስፈረም እንደሚሻ ታውቋል። የአርሰናል ተጫዋች የሆነው ሳምቢ በውሰት ለክሪስታል ፓላስ እየተሰለፈ ይገኛል።