የበሽር አል አሳድ ሚስት የፍቺ ጥያቄ አቅርበዋል መባሉን ክሬምሊን አስተባበለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብሪታኒያ የተወለዱት የሶሪያው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ሚስት የፍቺ ጥያቄ አላቀረቡም ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ተናገሩ።
አስማ አል-አሳድ ፍቺ ፈጽመው እሳቸው እና ባላቸው አማጽያን ደማስቆን ከተቆጣጠሩ በኋላ ጥገኝነት የጠየቁባት ሩስያን ለቀው መውጣት እንደሚፈልጉ የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር።
ዲሚትሪ ፔስኮቭ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለ ሪፖርቶቹ ሲጠየቁ "ትክክል አይደለም። ከእውነታው ጋር አይሄዱም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሳድ በሞስኮ ብቻ ተወስነው እንደሚቆዩ እና ንብረታቸውም ታግዷል የሚለውንም ዘገባ አስተባብለዋል።
ሩስያ የአሳድ መንግስት ጠንካራ አጋር የነበረች ሲሆን በሶሪያ እርስ በርስ ጦርነት ወቅትም ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥታለች።
የቱርክ መገናኛ ብዙኃን እሑድ እንደዘገቡት ከሆነ ግን አሳድ እና ባለቤታቸው በሩሲያ ዋና ከተማ ከባድ እገዳ ውስጥ እየኖሩ ከመሆናቸውም ባለፈ የቀድሞዋ የሶሪያ ቀዳማዊት እመቤት ፍቺ ጠይቀው ወደ ለንደን መመለስ ይፈልጋሉ።
አስማ የሶሪያ-ብሪታንያ ጥምር ዜግነት ያላቸው ቢሆንም ወደ ብሪታንያ እንዲመለሱ እንደማይፈቀድላቸው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቀደም ሲል አስታውቀዋል።
ከሳምንታት በፊት በፓርላማ ንግግር ያደረጉት ሚንስትሩ ዴቪድ ላሚ "እሳቸው ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰብ መሆናቸውን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ዩናይትድ ኪንግደም እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም" ብለዋል።
አንድም የአሳድ ቤተሰብ አባል "በእንግሊዝ ውስጥ ቦታ እንዳያገኝ" ለማድረግ "አቅሜ የሚችለውን ሁሉ አደርጋለሁ" ሲሉ አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት የበሽር አል አሳድ እንደሆነ በተገለጸ መግለጫ ከሶሪያ ለመሸሽ አስበው ሳይሆን፤ ነገር ግን በሞስኮ ጥያቄ ከሩሲያ ጦር ሰፈር ወደ ሞስኮ ወሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ49 ዓመቷ አስማ አል አሳድ እአአ በ1975 ከሶሪያዊያን ወላጆች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተወልደው ምዕራብ ለንደን በምተገኘው አክተን አደጉ።
በ25 ዓመታቸው ወደ ሶሪያ አቅንተው አሳድ አባታቸውን ተክተው ፕሬዝዳንት ከሆኑ ከጥቂት ወራት በኋላ ትዳር መሠረቱ።
የሶሪያ ቀዳማዊት እመቤት በነበሩበት 24 ዓመታት ውስጥም የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ስለእሳቸው ለመዘገብ ፍላጎት ነበረው።
አወዛጋቢ የሆነው የ2011 ቮግ መጽሔት "በበረሃ ውስጥ ያለች ጽጌረዳ" ብሎ ጠርቷቸዋል። "ከቀዳማዊት እመቤቶች ሁሉ ትኩስ እና መግነጢሳዊ ኃይል ያላት" ሲልም ገልጿቸዋል። በኋላ ላይ ግን ጽሑፉ ከቮግ ድህረ ገጽ ተወግዷል።
አስማ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት መጀመሪያ ላይ ባለቤታቸው የዲሞክራሲ ደጋፊዎችን በኃይል ሲጨፈልቁ ዝምታን መርጠዋል በሚል ከአንድ ወር በኋላ ተተችተዋል።
ግጭቱ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ባለቤታቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል በሚል ይከሰሳሉ።
እአአ በ2016 አሳም በሩሲያ መንግስት የሚደገፈውን የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከባለቤታቸው ጎን ለመቆም በመወሰናቸው በጦርነት ከምታመሰው አገር ለመውጣት የቀረበላቸውን ዕድል ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
እአአ በ2018 ለጡት ካንሰር ህክምና ማግኘታቸውን አስታውቀው ከአንድ ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማገገማቸውን ተናግረዋል።
ከወራት በፊት ደግሞ ሉኬሚያ ተገኝቶባቸው ህክምና መጀመራቸውን የወቅቱ የፕሬዝዳንት አሳድ ቢሮ አስታውቋል።
በዚህ ምክንያትም ከህዝባዊ ሥራዎች "ለጊዜው ትገለላች" ብሏል መግለጫው።












