ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ አጋሮቿ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን ለዩክሬን እንዲልኩ ፈቀደች
ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ የዩክሬን አብራሪዎች ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ አሜሪካ ሰራሹን ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን ለኪዬቭ እንዲልኩ አሜሪካ ፈቀደች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት ይህንን አዲስ አቅሟን መጠቀም ትችላለች ብሏል።
ዩክሬን በበኩሏ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እንዲፈፀምላት ስትጠይቅ የነበረው ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ውሳኔውን አድንቃለች።
ይሁን እንጂ ኪዬቭ ኤፍ 16 ተዋጊ ጀቶችን ተጠቅማ የሩሲያን የአየር የበላይነት ለመመከት ወራት ሊወስድባት እንደሚችል ይጠበቃል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ ቀደም ብሎ ኒውክሌር ከታጠቀችው ሩሲያ ጋር ያለውን ጦርነት ሊያባብስ ይችላል በሚል ስጋት ለዩክሬን ኤፍ -16 ተዋጊ ጄቶች እንዳይሰጡ ከልክለው ነበር።
ሩሲያ ግን እስካሁን በዚህ ላይ የሰጠችው አስተያየት የለም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ፣ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ ሁለ ገብ የሆኑ ኤፍ 16 ተዋጊ አውሮፕላኖችን ለዩክሬን እንዲያስተላልፉ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ገልጸው፣ይህም የመጀመሪያዎቹ አብራሪዎች ሥልጣናቸውን እንዳጠናቀቁ የሚፈፀም ይሆናል ብለዋል።
የኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዎፕኬ ሆክስታርም ይህ ዩክሬን አገሯን እና ሕዝቧን ከጥቃት ለመከላከል ትልቅ ዕድል ነው በማለት የአሜሪካን ውሳኔ ተቀብለዋል።
“ አሁን ጉዳዩን ከሌሎች የአውሮፓ አጋሮቻችን ጋር እንነጋገርበታለን“ ሲሉም በቀድሞ ስሙ ትዊተር በሚባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ኤክስ ላይ አስፍረዋል።
የዴንማርክ መከላከያ ሚኒስትር ጃኮብ ኢሌማን ጀንሰንም "መንግሥት ብዙ ጊዜ እንደተናገረው የጦር መሣሪያ ድጋፉ ከሥልጠና በኋላ የሚመጣ ሒደት ነው።ከቅርብ አጋሮቻችን ጋር እየተነጋገርንበት ነው" ሲሉ ለዴንማርክ ሪትዛው የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ የአሜሪካን ውሳኔ "አስደሳች ዜና" ሲሉ ገልጸውታል።
“ ጦራችን በፈጣን ተማሪዎች የተሞላ ነው። በቅርብ ጊዜ ዩክሬን ድል ማድረጓ የማይቀር መሆኑን እናሳያለን። በአሜሪካ ፣ በኔዘርላንድስ እና ዴንማርክ የሚገኙ አጋሮቻችንና ወዳጆቻችን ሁሉ እናመሰግናለን። ወደ ድል! “ ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
በምዕራቡ የዩክሬን አጋር የሆኑ አስራ አንድ አባል አገራት ያሉት ጥምረት የዩክሬን አብራሪዎችን በዚህ ወር መጨረሻ ማሰልጠን የሚጀምሩ ሲሆን ለሚቀጥለው ዓመት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዩክሬን አየር ኃይል ቃል አቀባይ ዩሪይ ኢህናት ኪዬቭ በመጭዎቹ ወራት ኤፍ 16 ጄቶችን ማንቀሳቀስ እንደማትችል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተናግረው ነበር ።
ኤፍ 16 ተዋጊ ጄት በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አስተማማኝ ተዋጊ ጀቶች አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።
እንደ አሜሪካ አየር ኃይል ከሆነ ጄቶቹ ሚሳይሎችንና ቦምቦችን በመታጠቅ በሰዓት 2 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር መብረር ይችላሉ።
የኤፍ -16 ተዋጊ ጀቶች ኢላማ የማድረግ ብቃታቸውም ዩክሬን በየትኛውም አየር ጠባይ እና በምሽት የሩሲያን ኃይሎች በብቃት ለማጥቃት ያስችላታል።
ዩክሬን በርካታ ተዋጊ አውሮፕላኖች እንዳሏት የሚታመን ሲሆን አብዛኞቹ በሶቭየት ዘመን የተሰሩ ጊዜ ያለፈባቸው ሚጎች ናቸው።
በመሆኑም ኪዬቭ ከሩሲያ አስከፊ ሚሳይል እና የሰው አልባ አውሮፕላን [ድሮን] ጥቃት የአየር ክልሏን ለመጠበቅ እንዲሁም በደቡብ እና በምስራቅ ዩክሬን እየፈፀመች ያለውን የአጻፋ ጥቃት ለመደገፍ ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ትፈልጋለች።