ምዕራባውያንን ያሳሰቡት በቻይና የሚደረጉ የሰው የዘረ-መል ማሻሻያ ሙከራዎች

ምዕራባውያን ተመራማሪዎች በቻይና የሚደረጉ የሰው ልጆች ላይ የዘረ-መል ማሻሻያዎች ለማድረግ የሚደረጉ ጥናቶች ግልጽነት ስለሚጎድላቸው አሳሳቢ ናቸው አሉ።

የቻይና መንግሥት የዘረ-መል ማሻሻያ ምርምርን በተመለከተ ያለው ሕግ በተለይ በግል ኩባንያዎች ሊጣሱ የሚችሉ ናቸው ሲሉ ምዕራባውያን ተመራማሪዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ቻይና ግን በቅርቡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተፈጻሚ ያደረገችው መመሪያ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የተከተለ መሆኑን አመልክተው፤ ሙያዊ ሥነ-ምግባር ማረጋገጥ፣ ቁጥር እና ፍተሻ ማድረግ የሚያስችል ነው ስትል የምዕራባውያን ተመራማሪዎችን ስጋት ታጣጥለለች።

የሰው ልጆች ላይ የዘረ-መል ለውጥ በማድረግ ወደ ልጆች ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ለይቶ ማውጣት እንደሚቻል ተመራማሪዎች ያምናሉ።

ይሁን እንጂ የዘረ-መል ማሻሻያ ማድረግ አግባብነት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የለውም። አንዳንዶች ይህ ቴክኒክ ከልጅ ልጅ የሚተላለፍ ቋሚ የዘረ-መል ለውጥ በማምጣት የአንድን ሰው ልዩ መለያ ሊያሳጣ ይችላል ሲሉም ይከራከራሉ።

የዘረ-መል ማሻሻያ ጥናት በስፋት መነጋጋሪያ መሆን የጀመረው አንድ ቻይናዊ ተመራማሪ የዘረ-መል ለውጥ ያደረገባቸው መንትያ ልጆች መወለዳቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

ዶ/ር ሂ ጂንኩይ የተባሉት ተመራማሪ ከአምስት ዓመታት በፊት በዓለም የመጀመሪያ የሆኑ ሉሉ እና ናና ሲሉ የሰየሟቸው መንትዮች ላይ የዘረ-መል ለውጥ በማድረግ መወለዳቸውን ይፋ ሲያደርጉ የዘርፉን ባለሙያዎች አስደንግጠው ነበር።

እንደ ዶ/ር ሂ ከሆነ መንትዮቹ ገና ጽንስ ሳሉ በዘረ-መላቸው ላይ ማሻሻያ እንደተደረገባቸው እና የኤችአይቪ ኢንፌክሽንን መቋቋም እንደሚችሉ ጨምር ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ሂ ይህን በማድረጋቸው የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን፣ ሦስት ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉም ተደርገዋል።

ተመራማሪው ላይ ቅጣቱ እንዲተላለፍባቸው ምክንያት የሆነው ፍቃድ የሌላቸውን ምርምሮች በሰው ልጆች ላይ ማከናወናቸው፣ እንዲሁም ምርምራቸው በይፋ አለመከናወኑ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

ግለሰቡ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ወደ ሆንግ ኮንግ አቅንተው ልጆች የጡንቻ በሽታ ከወላጆቻቸው እንዳይወርሱ ለማድረግ የዘረ-መል ማሻሻያ ላይ ጥናት ለማድረግ ክሊኒክ እንደሚከፍቱ ገልጸው ነበር።

ይህ ከተሰማ በኋላ ሆንግ ኮንግ ግለሰቡ የወንጀል ሬኮርድ አላቸው በሚል ምክንያት ለግለሰቡ የሥራ ፍቃድ ከልክላለች።

ታዲያ የበርካታ ምዕራባውያን ተመራማሪዎች ስጋት የቻይና ሕጎች ክፍተት ስላላቸው ምርምሮች በሰው ልጆች ላይ እንዲደረጉ ዕድል ይሰጣሉ በማለት የዶ/ር ሂ የምርምር ሥራን እንደ ምሳሌ ያቀርባሉ።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ክሪክ ኢንስቲትዩት የተባለው ባዮሜዲካል ምርምር ተቋም፣ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሮቢን ሎቬል-ባጅ በቻይና የምርምር ሥራዎች ግልጽ የማይደረጉ ነገሮች ስላሉ ነገሩ አሳሳቢ ነው ይላሉ።

“ቻይና በቴክሎጂው ቀዳሚ መሆን ለምን እንደምትፈልግ ይገባኛል፤ ነገር ግን አንዳንድ ዘርፎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ የዘረ-መል ለውጥ ምርምር ነው” ብለዋል።

“ይህ ሙከራ አግባብ በሆነ አስተዳደር እና ክትትል ስር መካሄድ አለበት። ይህን እያደረጉ ስላልሆነ ስጋት አለኝ” ብለዋል።

በካናዳ ዳልሆስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ፍንኮስ ባይሊስ በቻይና የሚደረጉ የዘረ-መል ለውጥ ምርምሮች ክትትል ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎቹ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የተላበሱ መሆን አለባቸው ይላሉ።

ተመራማሪዋ በቻይና ብቻ ሳይሆን በሰሜን አሜሪካ ያሉ የግል ኩባንያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ትልቅ ፈተና መሆኑን ይናገራሉ።

ከቻይና አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ የተወከሉት ዶ/ር ያንጊን ፔንግ ግን መንግሥታቸው የዘረ-መል ምርምር መመሪያዎችን እና ሕጎችን ጥብቅ ማድረጉን ይገልጻሉ።