በጋዛ የአንድ ዶክተር ዘጠኝ ልጆች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸው ተገለፀ

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በካን ዩኒስ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል የምትሰራ ዶክተር ቤትን መትቶ ከ10 ልጆቿ መካከል ዘጠኙን ገደለ።

ናስር ሆስፒታል እንዳስታወቀው የዶ/ር አል ናጃር አንድ ልጅ እና ባለቤቷ ጉዳት ቢደርስባቸውም ተርፈዋል።

በሆስፒታሉ የሚሰራው እና በሕይወት የተረፈውን የ11 ዓመት ልጅ ቀዶ ሕክምና ያደረገለት ብሪታንያዊ ዶክተር፣ ግራይሜ ግሩም ለቢቢሲ ለዓመታት የሕጻናት ሐኪም ሆና ልጆችን ስትንከባከብ ለቆየችው እናታቸው "ሊቋቋሙት የማይችሉት ጭካኔ ነው" ብሏል።

በአንድ የሚሳዔል ጥቃት ሙሉ ቤተሰቧን ልታጣ ትችል እንደነበርም ጨምሮ ተናግሯል።

የእስራኤል መከላከያ አርብ ዕለት በካን ዮኒስ በፈጸመው የአየር ጥቃት "በርካታ ተጠርጣሪዎችን" መምታቱን አስታውቆ "ተሳትፎ የሌላቸውን ሠላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት በተመለከተ የቀረበው ውንጀላ እየተገመገመ ነው" ብሏል።

በሃማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር ዳይሬክተር ያጋሩት እና ቢቢሲ እውነተኛነቱን ባረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ትንንሽ በእሳት የተቃጠሉ አስከሬኖች በካን ዮኒስ ጥቃቱ ካደረሰው ፍርስራሽ ውስጥ ሲወጡ ያሳያል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል "በካን ዮኒስ ከእስራኤል ወታደሮች አጠገብ በሚገኝ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የተለዩ በርካታ ተጠርጣሪዎችን መትተናል" ብሏል።

"ካን ዮኒስ አደገኛ የጦር ቀጠና ነው። በስፍራው የእስራኤል ወታደሮች መንቀሳቀስ ከመጀመራቸው በፊት ሰላማዊ ዜጎች ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርገዋል" ሲል ተናግሯል።

ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ባወጣው መግለጫ ላይ ባለፉት ቀናት በጋዛ ከ100 በላይ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ባለው 24 ሰዓት ውስጥ ብቻ በእስራኤል ጥቃት 74 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ሙኒር አልቦርሽ በኤክስ ገጻቸው፣ የአል ናጃር ባለቤት ሀሚድ፣ እሷን ስራ ቦታዋ አድርሶ ቤት በደረሰ በደቂቃዎች ውስጥ ነው የተመታው ብለዋል።

ዶ/ር አልቦርሽ እንዳሉት የዶ/ር አል ናጃር ትልቁ ልጅ ዕድሜው 12 ነበር።

ብሪታንያዊ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ግሩም የልጆቹ አባት "በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ደርሶበታል" ብሏል።

አባትየው "ጭንቅላቱን ዘልቆ የገባ ጉዳት አጋጥሞታል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ስለ አባትየው መጠየቁን የተናገረው የቀዶ ሕክምና ባለሙያው፣ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሰራ ዶክተር መሆኑን መስማቱን እና "ምንም ዓይነት የፖለቲካ፣ ወታደራዊ ተሳትፎ የለውም። እንደሁም በማኅበራዊ ሚዲያም ላይ ቢሆን ንቁ አይደለም" ብሏል።

ዶ/ር አላ አል ናጃር ያገጠማት "የማይታሰብ" ነው ሲል ስሜቱን አጋርቷል።

በሕይወት የተረፈው የ11 ዓመቱ አዳምም ቢሆን ለዕድሜው "በጣም ትንሽ ነው" ብሏል ዶ/ር ግሩም።

"የግራ እጁ ተንጠልጥሎ ነበር። ሰውነቱ በሌሎች ጉዳቶች ተሸፍኖ፣ እንዲሁም በርካታ ቦታዎች ከፍ ያሉ መቆረጦች አጋጥሞት ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ሁለቱም ቤተሰቦቹ ዶክተሮች በመሆናቸው፣ በጋዛ ከሚኖሩት ሁሉ ዕድለኛ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፤ ነገር ግን በቀዶ ጥገና ጠረጴዛው ላይ ስናስተኛው ዕድሜው 11 አይመስልም ነበር" ብሏል።

"ትንሹ ልጃችን ይድናል፤ ነገር ግን ስለ አባቱ እርግጠኛ መሆን አንችልም" ሲል አክሏል።

በጋዛ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ማሃሙድ ባሳል አርብ ከሰአት በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ቡድናቸው በካን ዮኒስ ነዳጅ ማደያ አቅራብያ ከሚገኘው ከአል ናጃር ቤት ስምንት አስከሬኖችን እና በርካታ የተጎዱ ሰዎችን ማውጣቱን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ አስቀድሞ ስምንት ሕጻናት መገደላቸውን በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋርቶ የነበረ ሲሆን ከሁለት ሰዓት በኋላ የሟቾቹ ቁጥር ዘጠኝ መድረሱን በመጥቀስ አሻሽሎታል።

ዘጠኝ ልጆቿን ያጣችው የሕክምና ባለሙያ ዘመድ የሆነው ዶክተር ዩሱፍ አቡ አል-ሪሽ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በለጠፈው መግለጫ ላይ ዶክተር አል ነጃርን በሕይወት ስላተረፈው ልጇ መረጃ እየጠበቀች ሳለ ለማግኘት ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል መሄዱን እና ሊያጽናናት መሞከሩን ተናግሯል።

ዶ/ር ዩሱፍ ለኤኤፍፒ "በቃን! ምህረትን አድርጉልን! ሁሉም አገራት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ሕዝቡ፣ ሃማስ እና ሁሉም አንጃዎች ምህረትን እንዲያደርጉልን እንማጸናለን።

"መፈናቀሉና ረሃቡ ደክሞናል በቃን!" ብሏል።

አርብ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ፣ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጋዛ የሚኖሩ የጦርነቱ "ጨካኝ ደረጃ" ተጋፍጠው እንደሚገኙ ገልጸው፣ እስራኤል በመጋቢት ወር የጣለችውን የሰብዓዊ ርዳታ እገዳ አውግዘዋል።

እስራኤል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እገዳውን በከፊል አንስታለች።

የእስራኤል ወታደራዊ ክንፍ የሆነው ኮጋት በበኩሉ 83 ተጨማሪ የጭነት መኪናዎች ዱቄት፣ምግብ እና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች የጫኑ መኪኖች አርብ ዕለት ጋዛ መግባታቸውን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀን ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ የጭነት መኪኖች እንደሚያስፈልጉ በመግለጽ፣ በጋዛ ለሚገኘው 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ አሁን የሚገባው የእርዳታ መጠን በቂ አለመሆኑን አስታውቆ፣ እስራኤል በቂ እርዳታ እንዲገባ እንትፈቅድ ጠይቋል።

እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የጀመረቸው መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሃማስ ጥቃት ሰንዝሮ 1,200 እስራኤላውያን መግደሉን እና 251 ማገቱን ተከትሎ ነው።

እስራኤል ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረች ጀምሮ 16,500 ሕጻናትን ጨምሮ፣ 53,901 ፍልስጤማውያን መገደላቸው የግዛቲቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።