ባለፉት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ምን ላይ ደረሱ?

ባለፉት ዓመታት በ12ኛ ከፍል ብሔራዊ ፈተና በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ብሩክ ባልካቸው፣ ሰዓዳ ጀማል እና ሃናን ናጂ [ከግራ ወደ ቀኝ]

የፎቶው ባለመብት, Biruk/Seada/ Hanan

የምስሉ መግለጫ, ብሩክ ባልካቸው፣ ሰዓዳ ጀማል እና ሃናን ናጂ ባለፉት ዓመታት በተሰጡት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት ካስመዘገቡት ተማሪዎች መካከል ይገኙበታል።

እንደ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከ3 ሚሊዮን 950 ሺህ በላይ ተማሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ወስደዋል።

ከእነዚህ መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 545 ሺህ 340 የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ቁጥር የተመናመነ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ማስደነቃቸውንና ማስደመማቸውን ቀጥለዋል።

በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው በተለየ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት መሳብ ችለዋል።

ለመሆኑ በቀደሙት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያስመዘገቡት ተማሪዎች ምን ላይ ደረሱ? የጥረታቸው ውጤት ወዴት መራቸው? የትምህርት ሕይወት ጉዟቸውስ ምን ይመስላል?

ቢቢሲ የተወሰኑትን ተማሪዎች በማፈላለግ ፈቃደኛ የሆኑትን አነጋግሯል።

ከኮምፒዩተር ሳይንስ ጋር የተዋደደው ብሩክ ባልካቸው - ከጀርመን

ብሩክ ባልካቸው

የፎቶው ባለመብት, Biruk Balkachew

የምስሉ መግለጫ, ብሩክ የመማር ሒደት በራሱ ያስደስተኛል ይላል

የትምህርት ፍልስፍናው ከተለመደው ለየት ይላል።የመማር ሒደቱ በራሱ ደስታ ይሰጠዋል።

" የሆነ ነገር ከብዶኝ ሲገባኝ ደስ ይለኛል" ይላል ብሩክ።ቀድሞ ያስቀመጠው የትምህርት ግብ የለውም፤ ህልሙን ፈልጎ የሚያገኘው በትምህርት ሒደቱ ውስጥ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሚከብደው ትምህርት አለ ብሎም አያስብም።ሒሳብ የሚዝናናበት ትምህርቱ ነው።

ብሩክ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ያስመዘገበው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር።

በ2012 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ 350 ሺህ ተማሪዎች ነበሩ ፈተናውን የወሰዱት።

ከእነዚህ መካከል የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ብሩክ ከ700 ነጥብ 669 በማምጣት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ያኔ ከወላጆቹ ጋር ሆኖ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ በውጤቱም ሆነ በወደፊቱም ብዙም አልተገረመም ነበር።

ይልቁኑ በቀጣይ የሚማረው ዘርፍ ነበር ግራ የገባው።

"የሚከብደኝ ትምህርት አለ ብዬ አላስብም፤ ግን ምን እንደምማር ነው ግራ የገባኝ። አንድ ነገር ለመሆን አልፈለኩም።የሆነ ዘርፍ ላይ እንዳተኩር ያነሳሳኝ ነገር ደግሞ የለም መሰለኝ። ብቻ ገና ውሳኔ ላይ አልደረስኩም" ነበር ያለው።

አሁን ግን የኮምፒዩተር ሳይንስ ትኩረቱን ስቦታል።

ብሩክ ከ12ኛ ክፍል ውጤቱ በኋላ ማማተር የጀመረው ከአገር ውጭ የሚገኙ የትምህርት ዕድሎችን ነበር።

ሆኖም በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ፈተና ተራዝሞ ስለነበር እና ውጤቱም ይፋ የተደረገው በዓመቱ አጋማሽ ላይ ስለነበር ከአገር ውጭ በሚገኙ ኮሌጆች የትምህርት ዕድልን ለማግኘት አዳጋች ሆኖበት ነበር።

ከዚያ ግን አንድ ጓደኛው በሚማርበት የፈረንሳይ ኮሌጅ አመልክቶ የትምህርት ዕድል አገኘ።

በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የሚገኘውን ኢኮሌ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ተቀላቀለ።

በዚያም "ያዝናናኛል" የሚለውን ሒሳብን ጨምሮ ፊዚክስ እና ኢኮኖሚክስ ተማረ። በሒደት ግን 'የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ'ን ሲማር ኮምፒዩተር ሳይንስን እየወደደው መምጣቱን ይናገራል።

የመጀመሪያ ዲግሪውን ካጠናቀቀ በኋላም ወደ ሥራው ዓለም ከመግባት ይልቅ ትምህርቱን መቀጠል ነበር የመረጠው።

በጀርመን ብሪመን በሚገኘው ኮንስትራክተር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል አግኝቶ በኮምፒዩተር ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪውን እየተከታተለ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል።

በዚያው ትምህርት ቤት የተማሩ ጓደኞቹ ስለነበሩ እርሱም መሞከሩንና ዕድሉን ማግኘቱን ገልጿል ብሩክ።

" ምንም የተወሳሰበ ነገር አልነበረውም" ብሏል የነበረውን ሒደትም ሲገልጽ።

ብሩክ ኮምፒዩተር ሳይንስን ለማጥናት የመራው የትምህርት ፍልስፍናው ነው - በትምህርት ሒደት ውስጥ የሚወደውን መከተል።

ህልሙ በወላጆቹ የተቀመጠለት አይደለም።ህልሙን ራሱ ነው የሚፈልገው፤ራሱ ነው የሚከተለው።በዚህ ነጻነት ውስጥ ነው ያደገው።

ብሩክ እንደሚለውም የራሱን ፍላጎት መከተሉ እና ቤተሰቦቹም ያስቀመጡለት መንገድ ባለመኖሩ የሚወደውን ለመከተል እና የሚወደውን ለመፈለግ እንደረዳው ይናገራል።

" ወላጆቼ ሁለቱም ሐኪሞች ናቸው፤ እነሱን ብከተል ሐኪም ነው ልሆን የምችለው።ግን እነሱ ያስቀመጡልኝ የሕይወት ግብ የለም። የራሴን ነው የምከተለው" ይላል። ይህ ማለት ግን የወላጆቹን ድጋፍ እና ምክር ወደ ጎን ይላል ማለት አይደለም።

"መማሩ ለራሴ ሲሆን ደስ ብሎኝ ነው የምማረው" የሚለው ብሩክ፣ ወደ ኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ያዘነበለው የወደደውን ተከትሎ እንደሆነም ይገልጻል።

ብሩክ አሁን ሁለተኛ ዲግሪውን እየሰራበት ባለው የኮምፒዩተር ሳይንስ ዘርፍ የማደግ ሃሳብ አለው። ትላልቅ ካምፓኒዎች ውስጥ በመስራት ልምዱን ካካበተ በኋላ የራሱን የሶፍትዌር ካምፓኒ አቋቁሞ መስራት ነው ዓላማው።

"በኢንደስትሪው ላይ አሉ ከሚባሉ ሰዎች መካከል አንዱ መሆን ነው የምፈልገው" የሚለው ብሩክ፣ ወደ ሥራው ዓለም ከተቀላቀለ በኋላ ሦስተኛ ዲግሪውን የመማር ዕቅድ እንዳለውም ለቢቢሲ ገልጿል።

". . . የራሴ ሆስፒታል ይኖረኛል" ሰዓዳ ጀማል

ፈተና ወረቀት እና ሰዓዳ አንዲት ሴትን ስትመረምር የሚያሳይ ምስል ጎን ለጎን

የፎቶው ባለመብት, Seada Jemal

ከሕፃንነቷ ጀምሮ ሕልሟ ሐኪም መሆን ነበር። ከእቃቃዎቿ ውስጥ የሕክምና ቁሳቁሶች አይጠፉም።

በጨዋታዎቿ ሐኪም ሆና ሌሎችን ማከምን ነበር የምታዘወትረው።

ከፍ እያለች ስትሄድ ደግሞ እናቷ በጨጓራ ህመም ሲሰቃዩ ትመለከት ነበር።ሐኪም ቤት ሄደው ሲመለሱ እናቷ በጎ እንደሚሆኑ የምታስታውሰው ሰዓዳ፣ ይህም ሐኪም የመሆን ፍላጎቷን ሳይጨምረው እንዳልቀረ ትገምታለች።

"ዶክተር ሆኖ ህሙማንን በደንብ ማከም ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል" የሚል ግንዛቤ የያዘችውም ገና በታዳጊነቷ ነው።

ሰዓዳ ጀማል በ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ ከ350 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከ700/ 650 ነጥብ በማምጣት ነበር ከሴቶች ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው።

ውጤቷ ወላጆቿን፣ ወዳጅ ዘመዶቿን፣ ትምህርት ቤቷን እንዲሁም አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ያኮራ ነበር።

ሰዓዳ፣ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧ ይፋ በሆነበት ወቅት ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ላይም ፍላጎቷ ሕክምና ሳይንስ ማጥናት እንደሆነ ገልጻ ነበር።

በስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ የሚገኘው ሃይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያፈራት ሰዓዳ፣ አሁን ላይ የልጅነት ህልሟን ለማሳካት ጉዞ ላይ ናት።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅን ተቀላቅላ የሕክምና ሳይንስ ትምህርቷን እየተከታተለች 5ኛ ዓመት ላይ ደርሳለች።

ብዙ ሰዓት በትምህርት ላይ ማሳለፍ፣ ከበፊቱ በተለየ ብዙ ማጥናት እና ድካሙን ጨምሮ የሕክምና ሳይንስን ማጥናት የሚኖሩትን ተግዳሮቶች ቀድማ ባትገምትም፣ ይህንን ሁሉ በትጋት እየተወጣች እንደሆነ ገልጻለች።

በአገር ውስጥ ብዙ ፈተናዎችን እያስተናገደ የሚገኘውን የሕክምና ዘርፍ መቀላቀልም ቀላል አይደለም።

በቅርቡም የሕክምና ባለሙያዎች የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ በማንሳት አድማ እስከ መምታት ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።

ሰዓዳ በተለይ ሙያውን ማጥናት እና ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በቅርብ መገናኘት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የሕክምና ባለሙያዎች እየገጠማቸው ያለውን ተግዳሮት ይበልጥ ተረድታለች። ሆኖም ይህ ከሕልሟ እንደማያደናቅፋት ትናገራለች።

"እንደ አገር ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች አሉ።ተምሮ ሥራ አለማግኘት፣ ካገኙም በኋላ የሚያገኙት ከልፋታቸው ጋር አለመመጣጠን ብዙ ሰዎችን ተስፋ ያስቆርጣል፤ ነገር ግን በመማር የምናገኘውን እውቀት እና ክህሎት በራሳችን መንገድ ብንጠቀመው ሽልማት ነው የሚሆነው" የምትለው ሰዓዳ፣ እውቀት እስከሆነ ድረስ መቼም እንደማይጎዳ እና ንግድ ላይም ቢሰማሩ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ታስረዳለች።

"ባለመማር አዲስ የምንፈጥረው ነገር አይኖርም" ትላለች ሰዓዳ።

" እዚህ በቅርበት እናያቸዋለን።ከእኛ ሲኒየር የሆኑ፣ ብዙ ደረጃ አልፈው ሕይታቸው የማያረካ ይሆናል። አንዳንዴ አያበረታታም ።ይህ እንደ አገር ቢስተካከል ለትውልድ ተስፋ ይሆናል" ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።

ሰዓዳ የሕክምና ትምህርቷን ስፔሻላይዝ ማድረግ ትፈልጋለች።የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ወይም የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስት ሆና የግል ሆስፒታል እንደሚኖራት ታልማለች።

ለዚህ ግን የውጭ የትምህርት ዕድል ብታገኝ የተሻለ እውቀት ይዛ መምጣት እንደምትችል እና የበለጠ ህልሟን ማሳካት እንደምትችል ገልጻለች።የዚህን በር የሚከፍትላት ብታገኝም ደስታዋ ወደር አይኖረውም።

የሰዓዳ ዓላማ ይህ ብቻ አይደለም።በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ሕብረተሰቡ ላይ ለመስራትም ታስባለች።

የሊደርሽፕ ሥልጠናዎችን ጎን ለጎን በመውሰድም ለወደፊት ህልሟ ራሷን እያዘጋጀች ትገኛለች።በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትሰጣለች።

እርሷ እየተከተለችው ያለው የስኬት መንገድ ለታናናሾቿም መነሳሳትን እንደፈጠረ ሰዓዳ ትናገራለች።

"ታናናሾቼ በትምህርትም፣ በሃይማኖትም የተሻለ ለመሆን ያቅዳሉ፤ይጥራሉም" ብላለች።

"የናሳ ተመራማሪነት ህልሙን የሚያሳካበት መንገድ ላይ ነው" የሚክያስ አባት

ሚክያስ አዳነ እና የሚማርበት ሃሊፋ ዩኒቨርሲቲ ሕንፃ

የፎቶው ባለመብት, Mikias/ Khalifa University

የምስሉ መግለጫ, ሚክያስ ከዚህ ቀደም ስፔስ ኤክስ ወይም ናሳ የመግባት ህልም እንዳለው ለቢቢሲ ገልጿል

ሚክያስ አዳነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቀው በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ ነው።

የኮቪድ ወረርሽኝ እንዲሁም የሰሜኑ ጦርነት በእርሱም ላይ ተፅዕኗቸውን አሳርፈዋል።ብሔራዊ ፈተናውም በመሰናክል የተሞላ ነበር።ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከመሰጠቱ ጋር በተያያዘ ሒደቱ ቀላል አልነበረም - ሚክያስ አልተበገረም እንጂ።

ሚክያስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኘው ወገል ጤና ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ቤተሰቦቹ ከሚኖሩበት 200 ኪሎሜትር ገደማ በሚርቀው ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው።

በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፎ ነው ሚክያስ በ2014 ዓ.ም. በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 666 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው።

ጦርነቱ ብዙ መስተጓጎል እንደፈጠረ የገለጹት አባቱ አቶ አዳነ እውነቱም "ጦርነቱ ባይኖር ከዚህም በላይ ውጤት ይጠበቅ ነበር" ብለዋል በወቅቱ።

የ2014 ዓ. ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የወሰዱት ከ900 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሲሆኑ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ከ30 ሺህ በታች የሚሆኑት ነበሩ።

ሚክያስ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ካገኘ አስትሮፊዚክስ ማጥናት እንደሚፈልግ እና የትምህርት ዕድሎችን እያፈላለገ እንደሆነ በወቅቱ ተናግሮ ነበር።

"ራሴን ማየት የምፈልገው ስፔስ ኤክስ ወይም ናሳ ገብቼ ነው" ሲልም ነበር የወደፊት ሕልሙን ለቢቢሲ ያጋራው።

ሚክያስ ይህን ካለ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል።በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሚክያስ ምን ላይ ደርሶ ይሆን?

ሚክያስ ባለበት የጊዜ ጥበት ምክንያት ለጥያቄያችን ምላሽ መስጠት አልቻለም።ሆኖም አባቱን አቶ አዳነ እውነቱን ጠይቀናቸዋል።

እርሳቸው እንደገለጹልን ሚክያስ ውጤቱን ካመጣ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪነግ ትምህርት ክፍል ትምህርቱን መከታተል ጀምሮ ነበር።

ሆኖም መንግሥት ባመቻቸው የትምህርት ዕድል ምክንያት ጀምሮት የነበረውን ትምህርት አቁሞ ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ተጉዟል።

አሁን ላይ በሃሊፋ ዩኒቨርሲቲ የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል።

ሚክያስ ህልሙ አስትሮፊዚክስ ማጥናት ቢሆንም የመረጠውን የትምህርት ዓይነት ባለማግኘቱ ለጊዜው ያገኘውን ትምህርት እየተከታተለ እንደሆነ የገለጹት አባቱ፤ ነገር ግን ይህን ሲጨርስ "ህልሙን መከተሉን" እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አሁን ላይ እየተማረ ባለው የትምህርት ዘርፍም የራሱን ሥራ ለመፍጠር እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።

" የዚህን ውጤት ህልሙን የማሳኪያ መንገድ አድርጎ ነው እየተጠቀመበት ያለው" ብለዋል።

"የሚክያስ ውጤት ቤተሰብን ጨምሮ በሁሉም ዘንድ ተነሳሽነትን ፈጥሯል። ወላጆችም ሚክያስን እንደ አርአያ በመውሰድ ልጆቻቸው እንዲበረቱ ድጋፋቸውን አጠናክረዋል" ብለዋል አቶ አዳነ።

ሚክያስን በሳይንስ ዘርፍ ለአገሩም ሆነ ለዓለም ጥሩ የሚያበረክት ሰው ሆኖ እንደሚያዩትም ተስፋ አላቸው። በቴክኖሎጂው ረገድም የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለውም ያምናሉ - አቶ አዳነ።

". . . በጤናው ዘርፍ ግንባር ቀደም ተመራማሪ መሆን ነው ህልሜ" ሃናን

ሃናን ናጂ

የፎቶው ባለመብት, Fana/Naji

ጉብዝና እና እርጋታ የሃናን መለያዋ ነው ይላሉ ወላጆቿ። ትምህርት እና ጥናት መዝናኛዎቿ ናቸው።

በርካታ ወጣቶችን "የስልክ ሱስ" ውስጥ የዘፈቁት ማኅበራዊ ሚዲያዎች የእርሷን ቀልብ አይገዙትም።ትኩረቷ ንባብ እና ትምህርት ላይ ነው - ሃናን ናጂ።

ከአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ ጀምሮ ከፍተኛ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው የመጣችው።ለዚህም ስኬቷ ከእናቷ በርካታ ሰዓቶች ተበርክተውላታል።

እናቷ ሹክሪያ ሺፋ ልጃቸው ሃናን አንደኛ በወጣች ቁጥር ሰዓት መሸለማቸው ያለምክንያት አይደለም።

" ሁሉም ነገር በሰዓቱ መደረግ እንዳለበት እና ያለፈን ነገር መመለስ እንደማይቻል ለማስረዳት ነው። . . . ዛሬ ላይ አላምዱሊላሂ ያንን ምክር ተጠቅማበታለች ብዬ አስባለሁ" ብለዋል እናቷ ሹክሪያ ለቢቢሲ በተናገሩበት ወቅት።

በዚህ የወላጆች ምክር እና ድጋፍ ያለፈችው ሃናን በ2016 ዓ.ም አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ700/649 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግባለች።

በዚህ ፈተና 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ፈተና ላይ የተቀመጡ ሲሆን የማለፊያ ነጥብ ማምጣት የቻሉት 36 ሺህ 409 የሚሆኑት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ።

በአዲስ አበባ የክሩዝ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረችው ሃናን ናጂ ውጤቷ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት እንደሆነ ገልጻ ነበር በወቅቱ ለቢቢሲ ስትናገር።

"ለራሴ ጥረት ዋጋ እሰጣለሁ።ምክንያቱም በጣም ጥሬበታለሁ ማለት ነው። ያለኝ ጥሩ ጎን ብዬ የማስበው ጊዜ አጠቃቀሜን ነው። የሚሻለው ነገር ላይ ነው ሰዓቴን ማጥፋት የምመርጠው።አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ የሚሻለው ነገር ማንበብ ነው" ነበር ያለችው።

ሃናን አሁን በቱርክ ከፍተኛ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።

ፈተና ላይ ስለነበረች በድምጽ ቃለ ምልልስ ለመስጠት ባትችልም ስለ ህልሟ እና አሁን ስላለችበት ሁኔታ ለቢቢሲ የጽሑፍ መልዕክት ልካለች።

ሃናን ከፍተኛ ውጤት ካመጣች በኋላ የተቀላቀለችው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ነበር። ነገር ግን ዓላማዋ ውጭ አገር ሄዶ መማር ስለነበር አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው ለውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች በማመልከትና ለፈተናዎች በመዘጋጀት ነበር።

"በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረኝ ቆይታ ብዙም ጥሩ የሚባል አልነበረም" የምትለው ሃናን፣ የተመቻቸ ማደሪያ ባለመኖሩ እና መኖሪያ ቤቷም ከተመደበችበት ካምፓስ ስለሚርቅ ተቸግራ እንደነበር ገልጻለች።

"ትምህርቱንም በጠበቅኩት ደረጃ አላገኘሁትም ነበር። ከዚያ እዚያ መማር እንደማልቀጥል ወሰንኩ" ትላለች።

ከዚያም በውጭ አገር ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ማመልከቻዎችን ማስገባቷን ተያያዘች።በአሜሪካ እና በአውሮፓ የትምህርት ዕድሎችን ብታገኝም የምትፈልገው የትምህርት ዘርፍ ስላልነበር አልተቀበለችም።

ከበርካታ የትምህርት ማመልከቻዎች በኋላ ግን በቱርክ አንካራ ዩኒቨርሲቲ ያስገባችው ማመልከቻ ሰመረላት።

አሁን ላይ በአንካራ ዩኒቨርሲቲ ሙሉ የትምህርት ዕድል አግኝታ የፋርማሲ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።

" የዓለምን የጤና ችግር ለመፍታት ግንባር ቀደም ተመራማሪ መሆን ነው የምፈልገው" የምትለው ሃናን፣ ይህንን ለማሳካትም መንገዷን ጀምራለች።

ሃናን ገንዘብ እና ሌላ ነገር ሳይሆን እውቀት እና ምርምር ማድረግ ነው ፍላጎቷ የሚሉት አባቷ አቶ ናጂም፣ እነርሱም በራሷ ፍላጎት እንድትሄድ እንደፈቀዱላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

" መጪውን ነገር ፈጣሪ ቢያውቅም፣ ህልሟን ታሳካለች ብዬ አስባለሁ" ብለዋል አቶ ናጂ።

"ልጆችን በግድ መግፋት አያስፈልግም።ግን የሚያዩት ነገር ያበረታቸዋል። በመሆኑም ከሃናን የሚያዩት እያበረታታቸው ጥናት ላይ ትኩረት እያደረጉ ነው" ብለዋል።