ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤታቸው በፖሊስ የተበረበረባቸው ትራምፕ በቀጣይ ምን ሊገጥማቸው ይችላል?
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፍሎሪዳ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በኤፍቢአይ አባላት ብርበራ ተካሂዶበታል።
ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ በትራምፕ መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራ መካሄዱን የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ወይም የአገሪቱ ፍትሕ ቢሮ ያሉት ነገር ባይኖሩም፤ ፍተሻውን ትከትሎ ትራምፕ ባወጡት መግለጫ ብዙ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባላት መኖሪያ ቤታቸውን መፈተሻቸውን ገልጸዋል።
ፍተሻው ከቀድሞ ፕሬዝዳንት የመንግሥታዊ ሰነዶች አያያዝ ጋር በተገናኘ ነው የተባለ ሲሆን፤ ትራምፕ ግን ባወጡት መግለጫ ፖሊስ ፍተሻውን ያካሄደው ለዋይት ሐውስ ደግም እንዳልወዳደር እንቅፋት ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ብርበራው ለትራምፕ ፖለቲካ ምን ማለት ነው?
ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ታሪክ በፕሬዝዳንት ላይ መሰል ብርበራዎች ተካሂደው እንደማያውቁ የሚናገሩት የፓልም ቢች ካውንቲ ስቴት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዴቭ አሮንበር ናቸው።
ምንም እንኳ በትራምፕ መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራ መካሄዱ በቀጣይ በወንጀል ያስከስሳቸዋል ማለት ባይሆንም፤ ኤፍቢአይ ባካሄደው ፍተሻ የሚያገኛቸው ሰነዶች ትራምፕ ዳግም ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ሊያግድ ይችላል ተብሏል።
ትራምፕ በእጃቸው አሉ ከተባሉ መንግሥታዊ ሰነዶች ጋር በተያያዘ ወንጀል ጥፋተኛ ከተባሉ ዳግም በምርጫ እንዳይወዳደሩ ሊታገዱ ይችላሉ።
የፌዴራል ፍተሻ ማዘዣ በዳኛ መፈረም አለበት። የሕግ አስከባሪ ተቋማት ፍተሻው ሕገ-ወጥነት ስለመፈጸሙ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል።
ኤፍቢአይ ፓልም ቢች የሚገኘው ማር-ኤ-ላጎ መኖሪያ ቤት ፍተሻ ካደረገ በኋላ በርካታ ሳጥኖችን ይዞ መውጣቱን ስማቸው ያልተጠቀሰ የፖሊስ ባልደረባ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
በትራምፕ መኖሪያ ቤት ብርበራ መደረጉን ተከትሎ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባወጡት መግለጫ፤ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ትብብር እያደረጉ መሆኑን አስታውሰው “በቤቴ ላይ የተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ አላስፈላጊ ወይም ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቶች ሥልጣናቸውን ሲለቁ ሰነዶችን ለአሜሪካ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት የማስረከብ ግዴታ አለባቸው።
ቤተ መዛግብቱ ትራምፕ ሥልጣናቸው ከለቀቁ ከወራት በኋላ ከማር-አ-ላጎ መኖሪያ ቤት 15 ሳጥኖችን ማውሰዱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ትራምፕ ኦፊሴላዊ ሰነዶችን ስለሚይዙበት መንገድ የፍትህ ክፍሉ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።
ትራምፕ ላይ የሚቀርቡ ሌሎች ክሶች
ዶናልድ ትራምፕ ከበርካታ ሕጋዊ ካልሆኑ ተግባራት ጋር ስማቸው ተያይዞ በተደጋጋሚ ይነሳል።
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን በኮሚቴነት የያዘ ቡድን፤ እአአ 2021 መጀመሪያ ላይ በካፒቶል ሂል በተቀሰቀሰው አመጽ የትራምፕ ተሳትፎ ምን ነበር የሚለውን እየመረመረ ይገኛል።
በዕለቱ ሕግ አውጪዎች የአሜሪካን የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉትን ጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት ሊያጸድቁ በተሰናዳበት ወቅት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትራምፕ ደጋፊዎች የካፒቶል ሂልን ሕጻን ጥሰው መግባታቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮም የቀድሞ ፕሬዝዳንት የምርጫ 2020 ውጤትን አልቀበልም ያሉበትን ምክንያቶችን እየመረመረ ነው።
በጆርጂያ ግዛት ያለ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ ትራምፕ እና አማካሪዎቻቸው በግዛቷ የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ላይ ጫና ለመፍጠር ሞክረው እንደሆነ በጥልቀት እየተመለከተ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ትራምፕ ከማጭበርበር፣ ሆነ ብሎ ንብረት ማውደም እና ከጾታዊ ትንኮሳዎች ጋር ተያይዘው ክሶች ይቀርቡባቸዋል። ትራምፕ ግን በየትኛውም ጥፋተኛ አይደለሁም ይላሉ።