ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዳሰነች ወረዳ ማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ እና ትራንስፖርት እንዲቆም ተወሰነ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው ዳሰነች ወረዳ በማርበርግ ቫይረስ ምክንያት የጣላቸውን እገዳዎች ባነሳ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ በድጋሚ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ ትምህርት እና ድግሶች እንዲቆሙ ወሰነ። የወረዳ አስተዳደሩ ክልከላዎቹን የጣለው "የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም በሰዎች ላይ እየተገኘ" መሆኑን መጥቀስ ነው።
የማርበርግ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበት አሪ ዞን አጎራባች በሆነው ደቡብ ኦሞ ዞን ሥር የሚገኘው ዳሰነች ወረዳ ክልከላውን ይፋ ያደረገው ትናንት አርብ ታኅሣሥ 3/2018 ዓ. ም. ምሽት ነው።
የወረዳ አስተዳደሩ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ያለመውን የመጀመሪያውን ክልከላ የጣለው ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ኅዳር 21 ነበር።
ይህ ክልከላ አንድ ሳምንት ከቆየ በኋላ በከፊል እንዲነሳ ተደርጎ ነበር። በትናትናው ዕለት ደግሞ እገዳዎቹ ሙሉ ለሙሉ እንደተነሱ ተገልጿል። እገዳው የተነሳው "የማርበርግ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለውጥ እያሳዩ በመምጣታቸው" እንደሆነም ወረዳው አስታውቋል።
ውሳኔው ይፋ ከተደረገ ከስምንት ሰዓታት ገደማ በኋላ ግን የመጀመሪያው ጥብቅ እገዳዎች በድጋሚ መጣላቸው ይፋ ተደርጓል።
በዚህም መሠረት "ትምህርት ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ" እንዲሆኑ ተወስኗል። "የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እንቅስቃሴም" እንዲቆም ተዕዛዝ ተላልፏል። ባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክሎች ደግሞ "ከአሽከርካሪው ውጪ ሁለተኛ ሰው" እንዳይጭኑ ተከልክለዋል።
ማኅበረሰቡ የሚያደርጋቸው የደስታ እና ሐዘን እንዲሁም "ሕዝብን ሊያሰባስቡ የሚችሉ" ሥነ ሥርዓቶችም "ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ" ተደርጓል። "መዝናኛ ተቋማት (የምሽት ዳንስ ቤቶች)፣ ፑል ቤቶች፣ ዲኤስ ቲቭ እና ቤቲንግ ቤቶች" እንዲሁም "ጫት ቤቶች" ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ተገልጿል።
"ማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮችም" እንዳይካሄዱ እገዳ ተጥሎባቸዋል። "ማኅበረሰቡ በተለምዶ በጋራ የሚመገባቸው እንደ ቦርዴ፣ ሾፎሮ እና መሰል መጠጦችን ንፅህናው በተጠበቀ ዕቃ በየግል መጠቀም" የሚለውም ከወረዳው አስተዳደር ውሳኔዎች መካከል ነው።
"አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመከላከያ ግብአትን አሟልተው እና አራርቀው" ለነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አሳስቧል። "ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ በሸቀጦች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ" እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።
የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ውሳኔውን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ እገዳዎቹ "ላልተወሰነ ጊዜ" እንደሚቆዩ አስታውቋል።
የወረዳ አስተዳደሩ እገዳዎቹን የጣለው፤ የጤና ሚኒስቴር አንድ ሰው በማርበርግ ቫይረስ መያዙ እንደተረጋገጠ በዕለታዊ የበሽታ ስርጭት መረጃው ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። ከትናንት አስቀድሞ በነበሩት ዘጠኝ ቀናት ለ821 ሰዎች በተደረገ ምርመራ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልተገኘም ነበር።
የዳሰነች ወረዳ ባወጣው መግለጫ ውሳኔውን ለማሳለፉ በምክንያትነት የጠቀሰው "የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም በሰዎች ላይ እየተገኘ መሆኑን" ነው። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሐቴ በበኩላቸው ውሳኔው የተላለፈው አንድ ተጨማሪ ሰው በቫይረሱ እንደተያዘ መረጋገጡን ተከትሎ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የትናንቱ ታማሚ የተገኘው በዳሰነች ወረዳ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ታደለ፤ "እርሱን አላውቅም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ መገኘቱ ይፋ ከተደረገ ነገ እሑድ ታኅሣሥ 5/2018 ዓ. ም. አንድ ወር የሚሞላው ማርበርግ ቫይረስ እስካሁን ድረስ በ14 ሰዎች ላይ ተገኝቷል። ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ያገገሙ ሲሆን ስምንቱ ሕይወታቸው አልፏል። ሁለት ሰዎች ደግሞ ሕክምና ላይ ናቸው።