ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬኗ መዲና ከባድ የሚሳኤል ጥቃት ደረሰባት
የዩክሬኗ መዲና ኪዬቭ ከባድ የሚሳኤል ጥቃት የደረሰባት ሲሆን እስካሁን ከታየው ሁሉ "እጅግ መጠነ ሰፊ" እንደሆነም ነው አንድ ባለሥልጣን የገለጹት።
ከሚሳኤሎች በተጨማሪ በድሮኖችም ጥቃት የተፈጸሙ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ሰዎችም መቁሰላቸው ተነግሯል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የዩክሬን የአየር መከላከያም በሚሳኤይሎቹ ላይ አጸፋዊ ምላሽ ተኩሰዋል።
ሩሲያ ባለፉት ሳምንታት የአየር ጥቃት ዘመቻዋን ያጠናከረች ሲሆን በቅርቡም በደቡብ ዩክሬን በኩል ወታደራዊ ዘመቻ እንደምትጀምር ይጠበቃል።
የአየር ጥቃት ማስጠንቂቂያ ሰኞ ሌሊት 8፡30 ጀምሮ የተሰማ ሲሆን ከሁለት ሰዓት በኋላም እንዲቆም ተደርጓል። ሩሲያ በመዲናዋ ላይ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ስምንተኛዋ ጊዜ ነው።
የዩክሬን ጦር ኃይሎች ኃላፈ ቫለሪ ዛሉጂያ ሩሲያ ከሰሜን፣ ደቡብ እና ምሥራቅ በኩል በመዲናዋ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቀዋል። በዚህም ጥቃት ከአየር፣ ባሕር እና መሬት ላይ የተነሱ 18 የሚሳኤል ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብለዋል።
ሁሉም ሚሳኤሎች በዩክሬን ተመትተው መውደቃቸውንም ተናግረዋል።
የዩክሬን የኪዬቭ ወታደራዊ ኃላፊ ሰርሂ ፖፕኮ ጥቃቱን “በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሚሳኤሎች ጥቃት የተፈጸመበት” ሲሉ ገልጸውታል።
“በደረሰው ቅድመ መረጃ ምክንያት በኪዬቭ አየር ክልል ውስጥ የተገኙት አብዛኛዎቹ የጠላት ሚሳኤሎች ተገኝተዋል እንዲሁም ወድመዋል” ሲሉም አክለዋል።
የሚሳኤል ቁርጥራጮች ከአየር ላይ ሲወድቁም የኪዬቭ ነዋሪዎች ከመስኮቶች እንዲርቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ የሮኬት ቁርጥራጮች መካነ አራዊትን ጨምሮ በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራዎች ወድቋል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የሶሎሚያንስኪ ግዛት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተነግሯል።
በግዛቲቷ የተቀሰቀሰው የእሳት አደጋ መጥፋቱንም ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በአውሮፓ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ ከምዕራባውያን አጋሮች በርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ቃል ተገብቶላቸዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመችበት ጊዜ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች እና ተዋጊዎች ተገድለዋል እንዲሁም ቆስለዋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ ከተሞች ወድመዋል፣ ወደ 8.2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዩክሬናውያን ለስደት የተዳረጉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 2.8 ሚሊዮን የሚሆኑት ሩሲያን መጠጊያቸው አድርገዋል።