ፖላንድ ተዋጊ ጄቶችን ለዩክሬን በማስታጠቅ የመጀመሪያዋ አገር ልትሆን ነው

ፖላንድ ከሩሲያ ወረራ በኋላ ለዩክሬን ተዋጊ ጄት በመላክ የመጀመሪያዋ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገር ልትሆን ነው።

የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንዴዝ ዱዳ የሶቪዬት ኅብረት ዘመን ስሪት የሆኑት አራት ተዋጊ ጄቶች በቀጣይ ቀናት ወደ ዩክሬን ይላካሉ ብለዋል።

ዩክሬን የጎረቤት አገር ፖላንድን ውሳኔ በደስታ የምቀበለው ነው ብትልም፣ ሚግ ጄቶቹ በጦርነቱ ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ አይጠበቅም።

የዩክሬን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ኦሌና ኮንደራትዩክ “ሌሎች አገራት የፖላንድን ምሳሌ ይከታላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

የዩክሬን ምክር ቤት አባል የሆኑት ኪራ ሩዲክ በበኩላቸው የጦር ጄቶቹ የአየር መከላከል አቅምን ክፍ እንደሚያደርጉ እና ለመልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖራቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዩሪያ ሳክ ደግሞ የአገሪቱ አየር ኃይል የፖላንድ ጄቶችን በአግባቡ ይጠቀምባቸዋል ብለዋል።

እንደ አማካሪው ከሆነ ባለፉት 24 ሰዓታት የዩክሬን አየር ኃይል በሩሲያ ሰው ኃይል እና ንብረት ላይ 16 ጊዜ የአየር ጥቃት ፈጽሟል። ይሁን እንጂ አማካሪው ዩክሬን አሁን ላይ የሚያስፈልጋት ዘመናዊዎቹ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች ናቸው ብለዋል።

ከፖላንድ በተጨማሪ ሌሎች የኔቶ አባል አገራት የዩክሬን አብራሪዎች የሠለጠኑባቸውን የሶቪዬት ኅብረት ዘመን የሆኑ የጦር ጄቶችን ለመላክ እያሰቡበት ነው።

ከዚህ ቀደም ዩክሬን ምዕራባውያን አገራት ዘመናዊ የሆኑትን እንደ ኤፍ-16 የጦር ጄቶች እንዲሰጧት በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ዩናይትድ ኪንግደም የኔቶ ደረጃ የሆኑ የጦር ጄቶችን የማብረር ሥልጠና ለዩክሬን አብራሪዎች ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፣ ሥልጠናው የሚወስደውን ረዥም ጊዜን ከግምት በማስገባት ዘመናዊ የጦር ጄቶች ለዩክሬን የመስጠቱ ጉዳይ በረዥም ጊዜ ዕቅድ የሚታይ ነው ብላ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ከአሜሪካ ወደ ዩክሬን የጦር ጄቶችን የመላክ ዕቅድን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሩሲያ ወረራ በተጀመረበት ወቅት ዩክሬን በእድሜ የገፉ ሚግ 29 እና ሱ-27 የተባሉ ወደ 120 የጦር ጄቶች እንዳላት ይገመታል።

ፕሬዝዳንት ዱዳ አገራቸው ፖላንድ ወደ አስራ ሁለት የሚጠጉ የሶቪዬት ዘመን የሆኑ ሚግ 29 ጄቶች እንዳላት ተናግረዋል።

ፖላንድ ጠንካራ የዩክሬን አጋር ከመሆኗ በተጨማሪ፣ ለዩክሬን ከፍተኛ የጦር ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት ተርታ ትሰለፋለች።

ፖላንድ ሶቪዬት ሰራሽ የጦር ጄቶቿን በአሜሪካ እና በኮሪያ ሰራሽ ጄቶች እየቀየረች ትገኛለች።

ከፖላንድ በላይ ለዩክሬን ከፍተኛ የጦር ድጋፍ ያደረጉት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት ናቸው።