የእስራኤል ወታደሮች ጋዛን ለሁለት ከከፈለው ኮሪደር ለቀው ወጡ

እስራኤል የጋዛ ሰርጥን ለሁለት በመክፈል የጦር ቀጣና በማለት ከፈረጀችው ኮሪደር ጦሯን አስወጣች።

ኔትዛሪም የተሰኘው ኮሪደር ሰሜናዊ ጋዛን ከቀሪው የጋዛ ሰርጥ የለየ እና ያቆራረጠ ኮሪደር ነው።

ጦሩ ከስፍራው መልቀቁን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በመኪኖች እንዲሁም በጋሪዎች ፍራሻቸውን እና የቤት እቃዎቻቸውን ጭነው እስራኤል ወደ ፍርስራሽነት ወደቀየረችው ሰሜናዊ ጋዛ እየተመለሱ ይገኛሉ።

ጦሩ ከስፍራው የወጣው የጋዛው የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እሁድ፣ ጥር 11/ 2017 ዓ.ም ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

እስካሁን ድረስ ሐማስ 16 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ደግሞ በእስር ቤቷ የነበሩ 566 ፍልስጤማውያንን ለቃለች።

ለሶስት ሳምንታት በሚቆየው የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም 33 እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲሁም 1 ሺህ 900 ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል ከ33ቱ ውስጥ ስምንቱ መሞታቸውን አስታውቃለች።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48,189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሶስተኛው የጋዛ ህንጻዎች መውደማቸውን የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

እሁድ እለት በርካታ ፍልስጤማውያን የኔትዛሪም ኮሪደርን ተሻግረው በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኙ ቤቶቻቸው ላይ የደረሰውን ውድመት መመልከት ችለዋል።

"የተመለከትነው ጥፋት፣ አሰቃቂ ውድመት ነው። ወራሪው ኃይል [እስራኤል] ሁሉንም መኖሪያ ቤቶች፣ ሱቆች፣ መስጊዶች፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ፍርድ ቤቶችን አውድወሟል" ሲሉ ከኔትዛሪም በስተሜን በምትገኘው አል ማግህራቃ ነዋሪ የሆኑት ኦሳማ አቡ ካሚል ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በደቡባዊ ጋዛ ከተማ ኻን ዩኒስ ከአንድ ዓመር በላይ ለመኖር የተገደዱ የ57 ዓመት ነዋሪ በበኩላቸው "አሁን ከፈረሰው ቤታችን አጠገብ ድንኳን እንተክላለን። ምንም አማራጭ የለንም" ሲሉ አክለዋል።

መሃመድ አል ሳርሂ የተሰኘ ፍልስጤማዊ በበኩሉ "መላው ከተማ ወደ ፍርስራሽ ተቀይሯል" ብሏል።

የእስራኤል ጦር የመሬት ላይ ወረራ በጋዛ ከማካሄዱ በፊት ፍልስጤማውያን እንዲወጡ አስገዳጅ ትዕዛዝ መውጣቷን ተከትሎ 700 ሺህ ነዋሪዎች ሰሜን ጋዛን ለቀው ወደ ደቡባዊ ጋዛ ተሰደው ነበር።

ጦሩ ወደ ደቡባዊ ጋዛ ላይ ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ ነዋሪዎች ለተደጋጋሚ ጊዜ ለመፈናቀል ተገደዋል።

ተፈናቃዮች በኔትዛሪም ኮሪደር በኩል ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳይመለሱ ክልከላ ተጥሎባቸው ቆይቷል።

የእስራኤል ጦር ከጥቂት ሳምንት በፊት በኮሪደሩ ምዕራብ በኩል በተወሰነ መልኩ ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ፍልስጤማውያን እግረኞች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ለመመለስ በባህር ዳርቻው ራሺድ ጎዳና በኩል እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር።

በተሽከርካሪዎች የመጡት ደግሞ ሳላህ አል ዲን በተሰኘው ጎዳና ለመጠቀም የአሜሪካ እና የግብጽ የጸጥታ ኃይሎችን ፍተሻ ማለፍ ነበረባቸው።

በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ነዋሪዎች "ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ለደህንነታቸው ሲሉ የወጡ የእንቀስቃሴ መመሪያዎችን እንዲያከብሩ" ማሳሰቡን የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ አስነብቧል።