ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሰሜን ኮሪያ የውጭ አገር ፊልሞች አይተዋል የተባሉ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ
የተባበሩት መንግሥታት የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ዜጎቹ የውጭ አገር ፊልሞችን እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን በማየታቸው የሞት ቅጣት እንደምትፈጽም በሪፖርቱ አመለከተ።
ከተቀረው ዓለም የተገለለችው እና በአምባገነን መንግሥት የምትተዳደረዋ ሰሜን ኮሪያ የዜጎቿን ነጻነት ከመገደብ ባለፈ በግዳጅ ሥራ ላይ እንደሚያሰማሩ ሪፖርቱ ጠቅሷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ባለፉት አስር ዓመታት የሰሜን ኮሪያ መንግሥት "በዜጎቹ ሕይወት ላይ በሁሉም መስክ" የሚያደርገውን ቁጥጥር ማጥበቁን ገልጿል።
"በአሁኑ ዓለም ሌላ ሕዝብ በእንዲህ ዓይነት ገደብ ውስጥ አይኖርም" ሲል የገለፀው ሪፖርቱ የሚደረገው ቁጥጥር "የበለጠ እየሰፋ የመጣ" እና በቴክኖሎጂ ጭምር የተደገፈ ነው ብሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ ይህ ድርጊት የሚቀጥል ከሆነ ሰሜን ኮሪያውያን "ለበለጠ ስቃይ፣ ጭካኔ ለተሞላበት ጭቆና እንዲሁም ለረዥም ጊዜ አብሯቸው ለሚቆይ ፍርሃት ይጋለጣሉ" ብለዋል።
ሪፖርቱ የተዘጋጀው ባለፈው 10 ዓመት ውስጥ ከሰሜን ኮሪያ አምልጠው የወጡ 300 ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሲሆን፣ የሞት ቅጣት በአብዛኛው ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ እንዲሆን የሚፈቅዱ ቢያንስ ስድስት አዲስ ሕጎች ተግባራዊ ሆነዋል።
በሞት ከሚያስቀጡ ወንጀሎች መካከል አንዱ የውጭ አገር ፊልሞችን እና የቴሌቪዥን ድራማዎችን መመልከት፣ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ሥርጭቶች ለሌሎች ማጋራት ይገኝበታል።
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ዜጎች መረጃ እንዳያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው።
ከአገሪቱ አምልጠው የወጡ ሰዎች ለመንግሥታቱ ድርጅት ተመራማሪዎች እንደተናገሩት ከሆነ ከ2020 ወዲህ የውጭ አገር ፕሮግራሞችን በማሠራጨት ብቻ በርካታ ሰዎች የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።
የሞት ቅጣቱ የሚፈጸመው በሌሎች ላይ ፍርሃትን ለመንዛት እና ሕግን አንዳይተላለፉ ለማድረግ በሚል በአደባባይ ሰዎች ተሰብሰብበው እየተመለከቱ ጥይት በመተኮስ መሆኑንም ተናግረዋል።
ካንግ ጊዩሪ በ2023 ከሰሜን ኮሪያ ያመለጠች ሲሆን፣ ሦስት ጓደኞቿ የደቡብ ኮሪያ ፊልሞችን ሲመለከቱ በመገኘታቸው የሞት ቅጣት እንደተፈፀመባቸው ለቢቢሲ ተናግራለች።
አንድ ጓደኛዋ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔ ሲሰጥ ፍርድ ቤት መገኘቷንም አክላ ተናግራለች።
"የፍርድ ውሳኔው የተሰጠው ከአደንዛዥ ዕጽ ወንጀለኞች ጋር ነው። እነዚህ ወንጀሎች አሁን የሚታዩት በተመሳሳይ መልኩ ነው" በማለት ከ2020 ወዲህ ሰዎች የበለጠ እየፈሩ መሆኑን አስረድታለች።
ይህ የመንግሥት እርምጃ ሰሜን ኮሪያውያን ተስፋ አድርገውት ከነበረው በተቃራኒ የቆመ ነው።
ኪም ጆንግ ኡን በአውሮፓውያኑ 2011 ወደ ሥልጣን ሲመጡ ምግብ በበቂ ሁኔታ ስለሚኖር ከእንግዲህ "ቀበቷችሁን ማጥበቅ አያስፈልጋችሁም" በማለት በመናገራቸው ሕይወት የተሻለ ይሆናል ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር አምልጠው የወጡት ሰዎች ተናግረዋል።
ተጨማሪ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን በመገንባት አገሪቱን እንደሚከላከሉ እንዲሁም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት እንደሚያሳድጉ ቃል ገብተው ነበር።
ነገር ግን የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው ኪም ከምዕራቡ ዓለም እና ከ2019 ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ ሲመጣ የጦር መሣሪያ ፕሮግራማቸው ላይ ብቻ በማተኮራቸው የዜጎች ሕይወት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች "እያሽቆለቆሉ" መጥተዋል።
ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አብዛኞቹ ሰዎች የሚበሉት እንዳልነበራቸው እና በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ "ቅንጦት" ነበር ብለዋል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት እንደነበር አንዲሁም በርካታ ሰዎች መሞታቸውን አብዛኞቹ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ተናግረዋል።
በተጨማሪም መንግሥት በአነስተኛ የገበያ ስፍራዎች የሚያደርገው አሰሳ እና እስር ሰዎች ነግደው የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን የሚያደርጉትን ጥረት ከባድ አድርጎታል።
አገሪቱ ከቻይና ጋር ባላት ድንበር ላይ ጠንካራ ጥበቃ ማድረግ በመጀመሯ እና ወታደሮች ለማቋረጥ የሚሞክሩትን ተኩሰው እንዲመቷቸው በመታዘዙ አምልጠው ለመውጣት የሚሞክሩ አስቸጋሪ ሆኗል።
"በኪም ጆንግ ኡን የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን አካባቢ ተስፋ የነበረን ቢሆንም ያ ተስፋ ግን አብሮን አልዘለቀም" ያለችው በአውሮፓውያኑ 2018 በ17 ዓመቷ አምልጣ የወጣች ሴት ናት።
"መንግሥት ቀስ በቀስ ሕይወታቸውን በነጻነት መምራት እንዳይችሉ መገደብ ጀመረ። በሕይወት መቆየትን በስቃይ እና በሰቀቀን እንዲታጀብ አደረገው" ስትል ለጥናት ቡድኑ አባላት ተናግራለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት "ባለፉት 10 ዓመታት መንግሥት በዜጎቹ ሕይወት ላይ ሙሉ ቁጥጥር በማድረግ በራሳቸው ሕይወት ላይ መወሰን እንዳይችሉ አድርጓል" በማለት በምጣኔ ሃብት፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳረፉን ገልጿል።
ሪፖርቱ አክሎም የቁጥጥር ማድረጊያ ቴክኖሎጂዎች መሻሻል መንግሥት በዜጎች ሕይወት ላይ የበለጠ ቁጥጥር እንዲኖረው አድርጓል ሲል አክሏል።
አንድ አምልጦ የወጣ እና ስሙ እነዳይገለጽ የጠየቀ ግለሰብ ለጥናት ባለሙያዎቹ የመንግሥት እርምጃ "የሕዝቡን ዓይን እና ጆሮ ለመገደብ" ያለመ ነው ብሏል።
"ትንሽ እንኳ ደስተኛ አለመሆንን ወይንም ቅሬታ ቢኖር እርሱን ለማጥፋት በማሰብ የሚደረግ የቁጥጥር መንገድ ነው" ሲል ተናግሯል።