የቀድሞ ፍቅረኛውን እርቃን ገላ የሚያሳይ ፎቶ ኢንተርኔት ላይ የለቀቀው 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተፈረደበት

ቴክሳስ ፍርድ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ከሴት ፍቅረኛው መለያየቱ አበሳጭቶት ፍቅረኛውን ለመበቀል አስቦ እርቃን ገላዋን የሚያሳዩ ፎቶዎቿን ኢንተርኔት ላይ ያጋራው 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተፈረደበት።

ዲኤል በሚል መጠሪያ ስም ብቻ በፍርድ ቤት ሰነዶች ላይ የተጠቀሰችው ሴት የቀድሞ ፍቅረኛዋ የፈጸመባትን በደል በተመለከት ክስ የመሰረተችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።

ዲኤል በመሰረተችው ክስ ላይ የፍቅር ግንኙነቷን በማቋረጧ የተበሳጨው የቀድሞ ፍቅረኛዋ እርሷን “ለማዋረድ” ሲል እርቃን ገላዋን የሚያሳይ ምስሎች ኢንተርኔት ላይ ለቋል።

ዲኤል ከእአአ 2016 እስከ 2021 ግንኙነት ውስጥ እያለች ለወንድ ለፍቅረኛዋ እርቃን ገላዋን የሚያሳይ ፎቶግራፎች ስትልክ ነበር።

ሁለቱ ጥንዶች እአአ 2021 ላይ ከተለያዩ በኋላ ተከሳሹ ዲኤል እርቃኗን ሆና የሚያሳዩ ምስሎችን በማሕበራዊ ሚዲያዎች እና ልቅ ወሲብ በሚታይባቸው ድረ-ገጾች ላይ ያለ ፍቃዷ ለጥፏል።

ከዚህ በተጨማሪ ተከሳሹ ፎቶዎቹን ድሮፕቦክስ በተባለ ድረ-ገጽ ላይ በአንድ ላይ ሰንዶ የፎቶዎቹ መገኛ ሊንኮችን ለጓደኞቿ እና ለቤተሰብ አባላቷ ልኳል።

ተከሳሹ ሌላው የቀረበበት ክስ በቀድሞ ፍቅረኛው ላይ መሰለል የሚል ይገኝበታል። ተከሳሹ ዲኤል በስልክ የምታደርገውን ከርቀት ሆኖ ይከታተል ነበር። የማሕበራዊ ድረ-ገጾቿን እና የኢሜል አድራሻዋን ከመያዙ በተጨማሪ በእናቷ ቤት ውስጥ ያለ የካሜራ ስርዓት ውስጥ በመግባት በቤት ውስጥ የምታደርገውን ሲመለከት ነበር።

በአንድ ወቅት ላይ ተከሳሹ ለዲኤል፡ “በቀሪው ሕይወትሽ ኢንተርኔት ላይ የወጡ ምስሎችን ለማጥፋት ስትጣጣሪ ትኖሪያታለሽ። ወደፊት የምታውቂያቸው ሰዎች በሙሉ ታሪኩን ሰምተው ወደ ኢንተርኔት ሄደው ይፈልጉታል” የሚል መልዕክት ልኮ ነበር።

የዲኤል ጠበቆች ተከሳሹ የደንበኛቸውን እርቃን ገላ የሚያሳይ ምስሎች ኢንተርኔት ላይ የለቀቀው አእምሯዊ ጉዳት ጉዳት ለማድረስ እንዲሁም ጾታዊ በደል ለመፈጸም አስቦ ነው ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።

እንደ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ተከሳሹ ፍርድ ቤት ሳይገኝ ቀርቷል እንዲሁም እርሱን ወክሎ የሚከራከርለት ጠበቃ አልሰየመም።

ግለሰቡ በቀድሞ ፍቅረኛው ላይ ላደረሰው ጉዳት 200 ሚሊዮን ዶላር እንዲፈል የተፈረደበት ሲሆን ጥፋቱ ለሌሎች መማሪያ እንዲሆን ደግሞ 1 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተፈርዶበታል።