የእስራኤል ሠራዊት በጋዛ ላይ የሚያካሂደው ጦርነት ደረጃ መቀየሩን ገለጸ

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የአገራቸው ሠራዊት በጦርነቱ የሚያካሂደው ዘመቻ ያለበት ደረጃ “መቀየሩን” በመግለጽ፣ “ተጨማሪ መረጃ አስኪሰጥ ድረስ” ዘመቻው ይቀጥላል ብለዋል።

አርብ ምሽት ሠራዊቱ በወሰደው እርምጃ “የጋዛ ምድር ተንቀጥቅጣለች” በማለት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለአንድ ቴሌዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

“ከመሬት ላይ እና በአየር ጥቃት ፈጽመናል። በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ሽብርተኞች ላይ በያሉበት ጥቃት ፈጽመናል። ለሠራዊታችን የተሰጠው መመሪያ ግልጽ ነው፡ ተጨማሪ መግለጫ አስከሚሰጥ ድረስ ዘመቻው ይቀጥላል” ብለዋል።

ከአርብ ምሽት ጀምሮ በተጠናከረ ሁኔታ የእስራኤል ጦር ኃይል በጋዛ ላይ የሚያካሂደው ጥቃት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ወደ ተወሰኑ የጋዛ ክፍሎች የእስራኤል ወታደሮች ዘልቀው መግባታቸው ተነግሯል።

የእስራኤል ጦር ሠራዊት ወታደሮቹ እና ታንኮቹ ከአርብ ሌሊት ጀምሮ ወደ ጋዛ መግባታቸውን እና “እዚያው እንደሚገኙ” ዛሬ ጠዋት አረጋግጧል። ነገር ግን ወታደሮቹ በትክክል ጋዛ ውስጥ የት እንደሆኑ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ይህንንም ተከትሎ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ኢዘዲን አል-ቃሳም የተባለው የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በቴሌግራም አካውንቱ ባሰራጨው መልዕክት፣ በሰሜን-ምዕራብ ጋዛ ውስጥ በሚገኙ የእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እላይ ጥቃት መሰንዘሩን አሰውቋል።

የእስራኤል ጦር ሠራዊት በጋዛ ውስጥ የሠራዊቱን እንቅስቃሴን የሚያሳይ ቪዲዮ ቅዳሜ ጠዋት ላይ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ቢቢሲ አስካሁን በምስሉ ላይ የሚታየው ስፍራ በትክክል የት እንደሆነ አስካሁን ማረጋገጥ አልቻለም።

ሠራዊቱ አርብ ምሽት በጋዛ ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ “እያስፋፋ” ነው ሲል አሳውቆ የነበረ ሲሆን፣ ተንቃሳቃሽ ምስሉም ጋዛ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ያላቸውን ታንኮችን እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ያሳያል።

የሐማስን ድንገተኛ ጥቃትን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ዛሬ ቅዳሜ ሦስተኛ ሳምንቱን ያያዘ ሲሆን፣ እስራኤል ውስጥ ሐማስ ከ1400 በላይ ሰዎችን ገድሎ፣ ከ220 በላይ የሚሆኑትን አግቶ ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ እስራኤል ያልተቋረጠ የአየር ድብደባ በጋዛ ላይ እያካሄድች ነው።

በእስራኤል የአየር ጥቃት እስከ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ድረስ 7,703 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

ረቡዕ ሌሊት የእስራኤል ታንኮች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ክፍል ዘልቀው በመግባት የተመረጡ እርምጃዎችን ወስደው እንደወጡ መገለጹ ይታወቃል።

ይህም ጥቃት ሠራዊቱ በጋዛ ላይ ለሚያካሂደው ቀጣይ ምዕራፍ ዘመቻ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የታለመ መሆኑን የእስራኤል ጦር ኃይሎች ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃትን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ዛሬ ቅዳሜ ሦስተኛ ሳምነቱን የሚይዝ ሲሆን፣ እስራኤል እግረኛ ሠራዊቷን ወደ ጋዛ ለማስገባት እየተዘጋጀች መሆኑ ሲነገር ቀይቷል።