ትራምፕ የአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት የኤፕስቲን ሰነዶችን እንዲለቅ የሚያዝዘው ረቂቅ ሕግ ላይ ፈረሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወሲብ ንግድ ወንጀል ከተፈረደበት ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ሰነዶች በሙሉ ይፋ እንዲሆኑ በሚያዝዘው ረቂቅ ላይ ረቡዕ ዕለት ፊርማቸውን ማኖራቸውን አስታወቁ።
ረቂቅ ሕጉ፤ የአገሪቱ የፍትሕ መስሪያ ቤት የኤፕስቲንን ምርመራን የተመለከቱ ሁሉም ሰነዶችን "ተፈልገው ሊገኙ እና ሊወርዱ (download) በሚችሉበት ቅርጽ" በ30 ቀናት ውስጥ እንዲለቅ የሚያዝዝ ነው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም የሰነዶቹን መለቀቅ ሲቃወሙ ነበረ ቢሆንም፤ ከኤፕስቲን ተጎጂዎች እና ተወካይ ከሆኑበት ሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በደረሰባቸው ግፊት ምክንያት ባለፈው ሳምንት አቋማቸውን ቀይረዋል።
ከፕሬዝዳንቱ አዲስ አቋም በኋላ ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው ድምጽ የመስጠት ሂደት፤ ረቂቅ ሕጉ በሁለቱም የኮንግረስ ክፍሎች ማለትም በተወካዮች ምክር ቤት እና በሴኔት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ድጋፍ አግኝቶ ጸድቋል።
ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ፤ ጉዳዩን አጀንዳ አድርገዋል ያሏቸውን ዴሞክራቶችን ወቅሰዋል። ዴሞክራቶች ይህንን ጉዳይ በማንሳት የሕዝቡን ትኩረት የትራምፕ አስተዳደር ካገኛቸው ስኬቶች ዘወር ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑን በማንሳት ከስሰዋል።
"ምናልባት ስለ እነዚህ ዴሞክራቶች ያለው እውነት እና ከጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የነበራቸውን ትስስር በቅርቡ ይገለጣል፤ ምክንያቱም የኤፕስቲን ሰነዶች እንዲለቀቁ [የሚያስችለው] ረቂቅ ሕግ ላይ ፈርሜያለሁ" በማለት ጽፈዋል።
እነዚህ ሰነዶች ይፋ እንዲወጡ ለማድረግ ጉዳዩ በኮንግረስ በኩል ድምጽ እንዲሰጥበት ማድረግ ግዴታ አልነበረም። ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው የፍትሕ መስሪያ ቤቱ ሁሉንም መረጃዎች እንዲለቅቅ ትዕዛዝ ሊሰጡ ይችሉ ነበር።
ረቂቅ ሕጉ ለኮንግረስ ከቀረበ በኋላ ግን በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በ427 ድጋፍ እና በአንድ ተቃውሞ ጸድቋል። ከምክር ቤት ቀጥሎ ሕጉ የቀረበለት ሴኔትም እንደደረሰው በሙሉ ድምጽ አጽድቆ፤ ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ልኮታል።
በአዲሱ ሕግ ይፋ የሚወጡት የኤፕስቲን ሰነዶች፤ ታዳጊ ሴቶችን ለወሲብ ንግድ በማቅረብ በተከሰሰው ባለሀብት ላይ ከተደረገው የወንጀል ምርመራ ጋር የተገናኙ ናቸው። እንዲለቀቁ ከሚጠበቁት መረጃዎች መካከል፤ ከተጎጂዎች እና ምስክሮች ጋር ከተደረጉ በኋላ በጽሑፍ የሰፈሩ ቃለ መጠይቆች እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶቹ በተካሄደ ብርበራ የተገኙ ማስረጃዎች ይገኙበታል።
ከምርመራው ጋር የተያያዙ የፍትሕ መስሪያ ቤቱ የመልዕክት ልውውጦች፣ የበረራ መዝገቦች እንዲሁም ከኤፕስቲን ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች እና ተቋማት ዝርዝርም በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
አሁን የሚለቀቁት መዝገቦች ባለፈው ሳምንት ከኤፕስቲን ወራሾች ተገኝተው በኮንግረስ ከተለቀቀው የ20,000 ገጽ ሰነድ የተለዩ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት ከተለቀቁት ሰነዶች ውስጥ የተወሰኑት በቀጥታ ፕሬዝዳንት ትራምፕን ይጠቅሳሉ። በአውሮፓውያኑ 2018 በተላከ እና ስለ ትራምፕ በተጻፈ አንድ መልዕክት ላይ ኤፕስቲን፤ "እርሱን ማውረድ የሚችለው ብቸኛ ሰው እኔ ነኝ" እንዲሁም "ዶናልድ ምን ያህል ቆሻሻ እንደሆነ አውቃለሁ" ማለቱን የባለፈው ሳምንት ሰነዶች ያሳያሉ።
ትራምፕ ለዓመታት የኤፕስቲን ወዳጅ የነበሩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ መጀመሪያ ኤፕስቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመታሰሩ ሁለት ዓመት አስቀድሞ እንደተቃቃሩ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ አንድም ስህተት አለመፈጸማቸውን በመግለጽ ይከራከራሉ።















