የአሜሪካ ኮንግረስ የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ኤፕስቲን ሰነዶች እንዲለቀቁ ወሰነ

የኮንግረስ አባላት መግለጫ እየሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ኮንግረስ አካል የሆኑት የተወካዮች ምክር ቤት እና ሴኔት ትናንት ባካሄዷቸው ስብሰባዎች፤ የአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ታዳጊዎችን ለወሲብ ንግድ በማቅረብ ወንጀለኛ ከተባለው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ይፋ እንዲያደርግ ወሰኑ።

የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን ያጸደቀው በ427 ድጋፍ እና አንድ ተቃውሞ ነው። ረቂቅ ሕጉ ለተጨማሪ ውሳኔ የቀረበለት ሴኔት ደግሞ ተቃውሞ ባለመነሳቱ ከመደበኛው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ውጪ በፍጥነት አጽድቆታል።

ውሳኔው የተላለፈው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም የነበረ አቋማቸውን ቀይረው፤ የኮንግረስ አባላት ሰነዶቹ እንዲለቅቁ ከጠየቁ ከቀናት በኋላ ነው። የፕሬዝዳንቱን የቀደመ አቋም የተቹ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ሰነዶቹ እንዲለቀቁ በይፋ ግፊት ሲያደርጉባቸው ነበር።

ባለሀብቱ ጄፍሪ ኤፕስቲን በአውሮፓውያኑ 2019 ሕይወቱ ያለፈው በኒውዮርክ ከተማ እስር ቤት ውስጥ እያለ ነበር። ግለሰቡ በእስር ቤት ክፍሉ ውስጥ የሞተው ራሱን አጥፍቶ እንደሆነ ተገልጿል።

ኤፕስቲን እስር ላይ የነበረው ሴቶችን ለወሲብ ንግድ በማዘዋወር ወንጀል ተከስሶ ነበር። ከዚህ አስቀድሞ በ2008 ደግሞ ታዳጊ ሴትን ለወሲብ ንግድ ተግባር በመጠቀም ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።

በሁለቱ ክሶች ባለሀብቱ ላይ በተደረጉ ምርመራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ተሰብስበዋል። ከሰነዶቹ ውስጥ ከተጎጂዎች እና እማኞች ጋር የተደረጉ እና በጽሑፍ የሰፈሩ ቃለ መጠይቆች ይገኙበታል።

የትራምፕ እና ኤፕስቲን ማኅበራዊ ግንኙነት ተመሳሳይ ሰዎችን ያሳተፈ ቢሆንም፤ ፕሬዝዳንቱ ኤፕስቲን በ2008 ጥፋተኛ ከመባሉ ብዙ ዓመታትን አስቀድሞ የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ይናገራሉ። ስለ ኤፕስቲን የወንጀል ተግባራት እንደማያውቁም ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ከ20,000 ገጽ በላይ ብዛት ያለው እና ትራምፕ የተጠቀሱበት የኤፕስቲን ሰነድ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ ስማቸው ከግለሰቡ ጋር ተያይዞ ሲነሳ ሰንብቷል። ዋይት ሀውስ በበኩሉ ፕሬዝዳንቱ ምንም ጥፋት እንዳልፈጸሙ በመግለጽ ተከላክሏቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰነዶቹን ይፋ ለማድረግ ድምጽ በተሰጠበት ወቅት ብቸኛ ተቃዋሚ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ክሌይ ሂጊንስ ናቸው። የምክር ቤት አባሉ ሐሳቡን የተቃወሙት በመረጃው መለቀቅ ምክንያት "የሚጎዱ ንጹኃን ሰዎችን" በተመለከተ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ነው።

ትራምፕ ሰነዱ እንዲለቀቅ በሚወተውቱ ሰዎች ላይ ሲያደርሱ የነበረውን ማጣጣል ትተው፤ "ምንም የምንደብቀው ነገር የለም" ማለታቸው እና ሰነዶቹ ይፋ እንዲደረጉ መጠየቃቸው ብዙዎች ያስገረመ ተግባር ነበር።

አዲሱ የትራምፕ ውሳኔ፤ ባለፉት ሳምንታት የፕሬዝዳንቱን አቋም በመደገፍ የሰነዶቹን መውጣት ሲቃወሙ ለነበሩ ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባላትን ያልተጠበቀ ነበር።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን፤ የኤፕስቲን ሰነዶች እንዲለቀቁ የሚደረገውን ግፊት "የዴሞክራቶች የማጭበርበር ተግባር" በማለት ሲያጣጥሉ ቆይተዋል። ሐሙስ ዕለት ግን ሰነዶቹ እንዲለቀቁ የድጋፍ ድምጽ ሰጥተዋል።

ውሳኔው በተወካዮች ምክር ቤት ድምጽ ከተሰጠበት በኋላ ወደ ሴኔት መመራት ያለበት ሲሆን ይህም የሚሆነው ከቀናት በኋላ እንደሆነ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ ውሳኔው ከሰዓት በኋላ ለሴኔቱ ቀርቦ በከፍተኛ ድጋፍ ጸድቋል።

ሴናተር ቸክ ሹመር ውሳኔውን ለሴኔቱ ያቀረቡት የሙሉ ድምጽ ድጋፍ ያገኙ ሐሳቦች በሚስተናገዱበት አሠራር አማካኝነት ነው። ይህም የሆነው ውሳኔው ላይ ተቃውሞ ባለመቅረቡ እና ክርክር ባለመደረጉ እንዲሁም ረቂቅ ላይ የተደረገ ማሻሻያ ባለመኖሩ ነው።

ውሳኔው ከሴኔት በኋላ ወደ ፕሬዝዳንቱ የሚያመራ ሲሆን ትራምፕም ሕግ አድርጎ የሚያጸድቀውን ፊርማ እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

ትራምፕ ከጅምሩ ሰነዶቹ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ቢሰጡ ኖሮ የውሳኔ ሐሳቡ በዚህ በኮንግረስ መልኩ ድምጽ አይሰጥበትም ነበር።

በአሁኑ ውሳኔ መሠረት ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ፓም ቦንዲ ከኤፕስቲን እና ከአጋሩ ግሌን ማክስዌል ጋር የተያያዙ "ሁሉንም ምሥጢራዊ ያልሆኑ መዝገቦች፣ ሰነዶች፣ ግንኙነቶች እና የምርመራ ግኝቶች" በ30 ቀናት ውስጥ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።