ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ጥቃት ከሰነዘረች አሜሪካ ፊሊፒንስን እንደምትከላከል ባይደን አስጠነቀቁ
በአወዛጋቢው ሳውዝ ቻይና ባሕር ላይ ማንኛውም ጥቃት ቢፈጸም አሜሪካ ፊሊፒንስን እንደምትከላከል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስጠነቀቁ።
አወዛጋቢ በሆነው የባሕር አካባቢ የፊሊፒንስና ቻይና መርከቦች ሁለት ጊዜ መጋጨታቸውን ተከትሎ ነው ባይደን ይህንን ንግግር ያደረጉት።
ፊሊፒንስን አሜሪካ “በጽኑ” እንደምትከላከል ባይደን ተናግረዋል።
በቻይና እና ፊሊፒንስ መካከል ባለፉት ወራት የተፈጠረውን መሻከፍ ተከትሎ የባይደን ንግግር ከሌሎች ጊዜያት የመረረ እንደሆነ ተገልጿል።
“ግልጽ እንዲሆን እፈልጋለሁ፣ በጣም ግልጽ እንዲሆን እፈልጋለሁ። አሜሪካ ፊሊፒንስን በጽኑ ትከላከላለች” ብለዋል።
እአአ በ1951 አሜሪካ እና ፊሊፒንስ የጋራ ወታደራዊ ስምምነት አድርገዋል። ፊሊፒንስ የአሜሪካ የቀድሞ ቅኝ ግዛት ናት።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልቤኒዝን በዋይት ሀውስ ባይደን ሲቀበሉ “በፊሊፒንስ መርከብ፣ አውሮፕላን ወይም ወታደሮች ላይ የሚቃጣ ጥቃት እርምጃ ያስከትላል” ብለዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ አሜሪካ “በቻይና እና ፊሊፒንስ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አንዳችም መብት የላትም” ብለዋል።
አሜሪካ ፊሊፒንስን እከላከላለሁ የምትል ከሆነ ድርጊቱ የቻይናን ሉዓላዊነት እና የሳውዝ ቻይና ባሕር ፍላጎቷን በማይጎዳ መንገድ መሆን እንዳለበት አስጠንቅቀዋል።
ፊሊፒንስ እንዳለችው የቻይና “አደገኛ አካሄድ” በቻይና እና ፊሊፒንስ የባሕር ጥበቃ መርከቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ይህ ግጭት በፊሊፒንስ የምጣኔ ሀብት ክልል ውስጥ እንደተከሰተና በሌላ ጊዜ ደግሞ የቻይና መርከብ የፊሊፒንስ የባሕር ጥበቃ መርከብን “እንደገጨ” ከሳለች።
የፊሊፒንስ መከላከያ ሚኒስትር ጊልበርቶ ቲዮዶሮ የቻይና መርከብ “ሆነ ብሎ” የፊሊፒንስ መርከብ ጋር እንደተጋጨ ገልጸዋል።
ባይደን የቻይና መርከብ “በአደገኛና ሕገ ወጥ መንገድ” ስለተንቀሳቀሰ ነው ግጭቱ የተከሰተው ብለዋል።
የፊሊፒንሱ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ በ2022 ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አድሰዋል።
በሳውዝ ቻይና ባሕር ያላቸውን ጥያቄ ከሌላው ጊዜ በላይ ገፍተው ማሰማትም ጀምረዋል።