ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የግጭቱ ሰለባ ሆነው ሞታቸው ያልታመነላቸው የ4 ዓመቶቹ የፍልስጥኤም እና የእስራኤል ሕጻናት
የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ‘ሀ’ ተብሎ ሲጀመር ነው ሁለቱም ሕጻናት የተቀጠፉት።
ሁለቱም አራት ዓመታቸው ነበር። አንዱ ፍልስጥኤማዊ ሌላኛው እስራኤላዊ።
ብዙዎች በእነዚህ ሕጻናት ግድያ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያዝኑ አልታዩም፤ እንዲያውም አልተገደሉም ብለው የሚሞግቱም ነበሩ።
ፍልስጥኤማዊው ኦማር ቢላል አል-ባና እና እስራኤላዊው ኦመር ሲማን-ቶቭ በቅርብ ርቀት ነው ይኖሩ የነበሩት።
በሁለቱ ሕጻናት መካከል ያለው ልዩነት 23 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው።
ነገር ግን መሐል ላይ እስራኤል በኮንክሪት የገነባችው የግንብ አጥር አለ።
በግንብ አጥር ተለያይው እስራኤል እና ጋዛ ውስጥ በቅርብ ርቀት የሚኖሩት ሕጻናት አይተዋወቁም።
ነገር ግን የልጅ ነገር ሆኖ ሁለቱም ከእኩዮቻቸው ጋር መቦረቅ የሚወዱ ታዳጊዎች ናቸው።
የሁለቱ ሕጻናት ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲመላለስ ሰንብቷል።
ሁለቱም በግጭቱ ነው ሕይወታቸውን ያጡት።
የሁለቱም ቤተሰቦች አሳዛኝ ታሪካቸውን አካፍለውናል።
ኦመር ሲማን-ቶቭ በሐማስ ጥቃት ነው የተገደለው።
ታጣቂው ቡድን ጥቅምት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ኪቡትዝ ኒር ኦትዝ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ነበር ሕይወቱ ያለፈው።
ኦማር ቢላል አል-ባና ደግሞ ከአራት ቀን በኋላ ነው የተገደለው - እስራኤል በምሥራቅ ጋዛ በምትገኘው ዜይቱን በፈጸመችው የአየር ጥቃት።
የሁለቱን ሕጻናት ግድያን የማይቀበሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ትርክቶች እየተካሄደ ያለው የመረጃ ጦርነት ማሳያ ናቸው።
በሕጻናት ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማሳነስ፣ ጭራሹንም የለም ለማለት የሚዳዱም አሉ።
ሐሰተኛ መረጃዎቹ በሐዘን ልባቸው ለተሰበረው ቤተሰቦች ሌላ ድርብ ሐዘን ሆኖባቸዋል።
ያስሚን የኦማር ቢላል አል-ባና እናት ናት። የሞተውንም ሆነ ልጆቿን “የሕይወቴ ቀንዲሎች” ስትል ነው የምትገልጻቸው።
ኦማር ከታላቅ ወንድሙ ማጂድ ጋር ሲጫወት ነበር የተገደለው። ማጂድ ይህንኑ ያረጋገጠበትን ቪዲዮ ቢቢሲ ተመልክቷል።
ማጂድ በቪዲዮው ላይ እንደሚናገረው የአየር ጥቃቱ ጎረቤት ያለ ሕንጻ ያፈረሰ ሲሆን፣ ፍርስራሹ ኦማር ላይ ወድቆ ተገድሏል።
ማጂድም ጉዳት ደርሶበት እግሩ ታሽጎ በተደናገጠ ሁኔታ ላይ እንደነበር ቪዲዮው ላይ ይታያል።
በኦማር ግድያ ዙሪያ ቀድመው ከወጡት ማኅበራዊ ልጥፎች መካከል አንዱ በእስራኤል ደጋፊ የቀረበ ነው።
ግራጫ ሸሚዝ የለበሰ አንድ ግለሰብ በነጭ ብርድ ልብስ የተጠቀለለ ሕጻን አቅፎ የያዘ ቪዲዮም ነው ይህ ሰው የለጠፈው። ቢቢሲ ይህ ሕጻን ኦማር መሆኑን አረጋግጧል። ይህ ግለሰብ በዚህ ቪዲዮ ላይ “ሐማስ ተስፋ ቆርጧል” የሚል ጽሁፍም አስፍሮበት በኤክስ ገጹ አጋርቷል።
ጽሁፉ አክሎም እስራኤል እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በሌሎች አገራት አሸባሪ የተባለው ቡድን “የሞተ ፍልስጥኤማዊ ሕጻን አስከሬን ይፋ አድርጓል። ጉዱን ግን ተመልከቱ። ሕጻን አይደለም፣ አሻንጉሊት ነው” ሲል አክሏል።
ቀጥሎም “በቅጥፈት የተሞላውን የሐማስ እና የፍልስጥኤም ፕሮፖጋንዳ አጋልጣለሁ” ይላል።
በዚህ ብቻ ሳያበቃ የሐማስ ደጋፊዎች ሲቀባበሉት ቢቆዩም ውሸት መሆኑን ሲያውቁ ቪዲዮውን ሰርዘውታል ብሏል።
እንደ ኤክስ ከሆነ ቪዲዮው እና ይህ ሐሰተኛ ልጥፍ 3.8 ሚሊዮን ጊዜ ታይቷል። የእስራኤል መንግሥት ይፋዊ የኤክስ ገጾችም ጉዳዩን አራግበውታል።
ግለሰቡ በተጨማሪ ከቪዲዮው ላይ በነጭ ፎጣ የታቀፈውን ሕጻን እንዲሁም ከቪዲዮው ላይ የተወሰደውን ፎቶ የሕጻኑን ፊት በማክበብ ሌላ ጽሁፍ አጋርቷል።
“ሐማስ በድንገት የአሻንጉሊት ቪዲዮ አጋርቷል። (አዎ አሻንጉሊት ነው) በእስራኤል ጥቃት የሞተ ሕጻን አስመስሎ ነው ያቀረበው” ሲል ጽፏል።
በፈረንሳይ እና በኦስትሪያ የሚገኙ የእስራኤል ኤምባሲዎችን ጨምሮ ሌሎች ኤክስ ላይ የሚገኙ የእስራኤል ተቋማትም ተቀባብለውታል።
መቀመጫቸውን እስራኤል ያደረጉ እስራኤልን በሚደግፉ እና ፀረ ሐማስ በሆኑ ቡድኖችም ጽሁፋ መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ተጋርቷል። በሕንድ የሚገኙ ቡድኖችም ይህንኑ ተመሳሳይ ሃሳብ አስተጋብተዋል።
ሁሉም ሲለጥፉ ሕጻን ሳይሆን አሻንጉሊት ነው እያሉ ነበር። ቪዲዮውን ላየው ግን አሻንጉሊት ሳይሆን ሕጻን መሆኑን መረዳት ይቻላል።
የመጀመሪያውን ቪዲዮ ይፋ ያደረገው ፍልስጥኤማዊው ፎቶ አንሺ ሞአመን ኤል ሃላቢ ሲሆን፣ ያጋራውም በኢንስታግራም ገጹ ላይ ነው። ግራጫ ቲ ሸርት የለበሰ ግለሰብ ኦማርን ተሸክሞ የሚያሳየውን የመጀመሪያ ቪዲዮ የቀረጸው ሞአመን ነው።
በቦታው ከነበሩት አንዱ የኤኤፍፒው የፎቶ አንሺ ሞሐመድ አቤድም ተመሳሳይ ግለሰብ በነጭ አምሶላ የተጠቀለለ ልጅ ይዞ የሚያሳይ የሚመስል ፎቶ አንስቷል። ይህ ፎቶ ጌቲ ኢሜጅ ድረገጽ ላይም ይገኛል።
“በጋዛ ከተማ በሚገኘው አል-ሺፋ ሆስፒታል አስከሬን ማቆያ ፊት ለፊት” የሚል ጽሁፍ እና ጥቅምት 1/ 2016 ዓ.ም. መነሳቱም ሰፍሮበታል። በተመሳሳይ ቀን ነው ሞአመን ኤል ሃላቢ ቪዲዮውን ኢንስታግራም ገጹ ላይ ያጋራው።
መረጃ በማጣራት የሚታወቁ እንደ አልት ኒውስ ያሉ ተቋማትም የፎቶዎቹን እና የቪዲዮዎቹን መነሻ ለማጣራት ሞክረዋል።
ሁለቱም የፎቶ ጋዜጠኞች ቪዲዮው እና ምስሉ በአል-ሺፋ ሆስፒታል አስከሬን ማቆያ ፊት ለፊት መነሳቱን ተናግረዋል። ግራጫ ቲ ሸርት ስለለበሰው ሰው እና በዕለቱ በሆስፒታሉ ስለነበረው ጉዳይም በዝርዝር ተናግረዋል።
ሁለቱም አሻንጉሊት አለመሆኑን እና ሕይወቱ ገና በለጋነቱ የተቀጠፈው ሕጻኑ ኦማር ቢላል አል-ባና መሆኑን ገልጸዋል። የልጁን ማንነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተጨማሪ ምስሎችንም አጋርተዋል።
በኋላ ላይም ሞሐመድ አቤድ በርካታ ምስሎችን ኢንስታግራም ላይ አጋርቷል። “ይህ የአሻንጉሊት ምስል አይደለም። ትክክለኛ እና በአል-ሺፋ ሆስፒታል ያነሳሁት ነው” ሲል አስፍሮበታል።
የኦማር ፎቶ ከሕጻን ይልቅ አሻንጉሊት እንዲመስላቸው የሆነው በፎቶው ላይ የሚታየው የሕጻኑ ቆዳ ቀለም ነው። እስራኤል በጋዛ በፈጸመቻቸው የእስራኤል የአየር ጥቃቶች የተገደሉ በርካታ ህሕጻናትን ፎቶ ማንሳቱን የሚገልጸው አቤድ የቆዳቸው ቀለም እንደ ኦማር ተመሳሳይ መሆኑን ገልጿል።
ያስሚንም ልጇ ኦማር በአየር ጥቃት ስለመገደሉ አረጋግጣለች።
በጥቃቱ “ሕጻናት እና ንጹሃን ዜጎች አልተገደሉም” የሚሉት ፍጹም ሐሰት ነው ስትልም ተናግራለች።
የተገደለውን ልጇን “አሻንጉሊት ነው የማለት መብት የላቸውም” ብላለች።
“የእስራኤል መንግሥት እየዋሸ፣ ወንጀሉን እና ጭፍጨፋውን እየደበቀ ነው” ስትል አክላለች።
በዩናይትድ ኪንግደም የእስራኤል ኤምባሲ ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ምላሽ ካለመስጠቱም በላይ ስለ ኦማር አገዳደልም ምንም አላለም።
“የተሳሳተ መረጃን መገምገም አስፈላጊ ነው” ከማለት ባለፈ ቢቢሲ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያስፋፋ ነው በማለትም ከሷል።
ኤክስ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ አስተያየት አልሰጠም።
የእስራኤሉ ኦመር
“ኦመር መልዓክ ነው። እሱ በጣም በጣም ቆንጆ እና ንጹህ ነው። ከእህቶቹ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረው። ሁሌም አብረው ይጫወቱ ነበር። ለእሱም ደጎች ነበሩ” ሲል ሞር ላኮብ የተባለች የሲማን-ቶቭ ቤተሰብ ጓደኛ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጋዛ አጥር ደርምሶ ቅዳሜ ጠዋት ኪቡትዝን ሲያጠቃ ዋትስአፕ ላይ ለቤተሰቡ መልዕክት ልካላቸው ነበር። ከጥቃቱ ለማምለጥ ተደብቀው እንደነበር አሳውቀዋት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ከእነሱ ምንም አልሰማችም።
ሌሎች በተጨማሪ የላከቻቸው መልዕክቶች አልተነበቡም።
የኦመር ወላጆች ታማር እና ዮናታን በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን ቆይታ ሰማች። ኦመርን ጨምሮ ታላላቅ እህቶቹ ሻቻር እና አርቤልም ቤታቸው ሲቃጠል ሕይወታቸው አልፏል። ሞታቸው በበርካታ መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ሽፋን አግኝቷል።
አንድ ፎቶ ላይ ኦመር በቤተሰቦቹ ተከቦ ሲስቅ ይታያል።
ፎቶውን የእስራኤል መንግሥት ኤክስ ላይ አጋርቶታል።
“መላው ቤተሰብ በአሸባሪው ሐማስ ተገድሏል። ምንም ቃላት የለንም። መታሰቢያቸው ለበረከት ይሁን” የሚል ጽሑፍ አስፍሮበታል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ናፍታሊ ቤኔትም አጋርተውታል።
በርካታቶች መደናገጣቸውን በመግለጽ ፎቶው ስር ጽፈዋል። አንዳንዶች ግን ያልተጠበቀ ሃሳብ አስፍረዋል።
ሐማስን የሚደግፉ በርካታ ገጾች ኦመርን “የተከፈለው ተዋናይ” ብለውታል።
ምክንያት ያሉት ደግሞ ሐማስ “ሕጻናትን አይገድልም” የሚል ነው። ሌሎች ደግሞ “ይህ የአይሁዶች ምርጥ ፕሮፖጋንዳ ነው” በማለት ኦመርም ሆነ እህቶቹ አለመገደላቸውን በመግለጽ ሞግተዋል።
ሌላው ደግሞ “ስለመገደላቸው ምንም ማስረጃ የለም” ሲል ጽፏል። “መዋሸቱን አቁሙ” ሲልም ጠይቋል።
በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለ ሲማን-ቶቭ ቤተሰብ ተመሳሳይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
አንዳንዶች እሱ እና እህቱ “የቀውስ ተዋናዮች”- ሲሉም ጠርተዋቸዋል።
የአስተያየት ሰጪዎቹን ማንነት ለማየት ሞክረናል። ብዙዎቹ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ናቸው። ብዙዎቹም ሐማስን በቋሚነት የሚደግፉ ናቸው። ሁለቱ ደግሞ በዌስት ባንክ የሚኖሩ ናቸው።
እነዚህ ብዙም ተከታይ የላቸውም። በርካታ ማስረጃዎች ቢቀርቡም ሐማስ ሕጻናትን አላጠቃም ወይንም አልገደለም የሚለው ትርክታቸው ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ይስተጋባል።
ሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ግድያው መፈጸሙን ቢያምኑ የሐማስ ታጣቂዎች እጅ የለበትም ብለዋል። “እስራኤሎች ራሳቸው ይመስሉኛል” ሕጻናቱን ገድለው “ሐማስን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚሞክሩት” ሲል አንዱ ጽፏል።
በወዳጆቿ ሞት ምክንያት ሐዘን የገባት ሞር ላኮብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰፍሩት አስተያየቶች ተጨማሪ ጭንቀት እንደፈጠሩባት ገልጻለች።
“ዓለም እንዲያስታውስ እና ምን እንደተፈጠረ እንዲያውቅ እፈልጋለሁ። ሞታቸውን መቀበል በራሱ ከባድ ነው። እነዚህ አስተያየቶች ደግሞ ይበልጥ ያከብዱታል።”
“እንዴት ምላሽ እሰጣለሁ? መሞታቸውን ማረጋገጥ አለብኝ? ለምንስ አምስት መቃብሮች በአስከሬናቸው ተሞሉ?” ስትል ጠይቃለች።
ይህን መሰሉን የበይነ መረብ የሐሰት መረጃ “ሰይጣን እና ክፉ” ስትል ገልጻዋለች።
በተመሳሳይ እንደ ኦማር ላሉ የፍልስጥኤማውያን ሕጻናት ሞት ካለመታመኑም በላይ ጥያቄ ተነስቶበታል ስትባል ደግሞ ቁጣዋ ይበልጥ ጨምሯል።
“በሐማስ ምክንያት ለተገደሉ ንጹሃን ሁሉ ከልቤ ሐዘኔን እገልጻለሁ። የሚሆነው ግን ደስ አይልም” ብላለች።