ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናዚዎችን የሞገተው ኖርዌያዊው የመሃል ሜዳ ሞተር
በፈረንጆቹ መስከረም 1933 ሃምቡርግ ባቡር ጣቢያ - ሁለቱ የረዥም ጊዜ የኳስ ሜዳ ተጣማሪዎች ሊለያዩ ግድ ሆነ።
አስብዮርን ሃልቮርሰን ወደ ኖርዌይ እያቀና ነው። ለረዥም ጊዜ የሃምቡርግ አማካይ ሆኖ ተጫውቷል።
በጀርመን ሊግ ከተጫወቱ ቀደምት የውጭ አገር ተጫዋቾች አንዱ ነበር።
ጓደኛው ኦቶ ፍሪትዝ ሃርደር ደግሞ ከሃልቮርሰን የሚሻገርለትን ኳስ ከመረብ በማሳረፍ ይታወቃል።
ዕድሜ ለሃርደር ጎሎች ሃምቡርግ የጀርመን ሊግ ዋንጫን በ1923 እና በ1928 ማንሳት ችሏል።
ሃርደር ወደ ሃምቡርግ ባቡር ጣቢያ ያቀናው የረዥም ጊዜ የክለብ ጓደኛውን ለመሰናበት እንጂ ሕይወቱን የሚቀይር ድራማ ለማየት አልነበረም።
ሃልቮርሰን በወቅቱ 34 ዓመቱ ነበር። ጫማ ሰቅሎ ወደ አገሩ ኖርዌይ በማቅናት የእግር ኳስ ማኅበር አባል በመሆን ማገልገል ነበር ዓላማው።
ሃልቮርሰን፤ በ1936 ኦሊምፒክ ኖርዌይን እየመራ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል። ይህ እስከ ዛሬ ድረስ የብሔራዊ ቡድኑ ብቸኛው ዓለም አቀፍ ክብር ነው።
ነገር ግን ሃልቮርሰን ይበልጥ የሚታወቀው በሜዳሊያው ሳይሆን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በፈፀመው ጀብድ ነው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሃልቮርሰን ኖርዌይን የሚያስተዳድረው የናዚ ወራሪ ኃይልን ተዋግቷል። ነገር ግን በኋላ ተይዞ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ ካምፕ ተወሰደ።
ሃርደር የሃልቮርሰን የስድስት ዓመት ታላቁ ነው። ጦርነቱ እየጋለ ሲመጣ ኤስኤስ የተባለውን የአዶልፍ ሂትለር ጠባቂ የሆነውን ቡድን ተቀላቀለ።
ሃርደር፤ በዕድገት ላይ ዕድገትን እያገኘ ከናዚ የጭፍጨፋ ማዕከላት የአንዱ አዛዥ ሆኖ ተሾመ። ይህ ካምፕ ሃልቮርሰን የታሰረበት ነበር።
ነገር ግን ሁለቱ የሃምቡርግ ተጫዋቾች ድጋሚ እንዳልተገናኙ ነው የሚነገረው።
ዮርገን ኮዋሌውስኪ የታሪክ አስተማሪ ናቸው። ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን የሃልቮርሰን ሕይወትን የሚመረምር አንድ ጥናት ሠርተዋል።
ሃልቮርሰን፤ በ18 ዓመቱ የአምበል አርማውን አጥልቆ ላደገበት ከተማ ክለብ ተጫውቶ የኖርዌይ ዋንጫን ማንሳት ችሏል።
ከእግር ኳስ ተጫዋችነቱ ባለፈ የመርከብ ደላላ ሆኖ ኑሮውን ይገፋ ነበር። ወደ ጀርመን የሚያቀናበት ዕድል ሲመቻች ዓይኑን አላሸም ነበር።
ሃልቮርሰን፤ ሃምቡርግን ከተቀላቀለ በኋላ ክለቡን ለዋንጫ ማብቃት ቻለ።
ታላላቅ የኖርዌይ ዜጋ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ታሪክ የቀረበበት አንድ መፅሐፍ እንደሚተርከው ሃልቮርሰን የጀመርን ብሔራዊ ቡድን አምበል እንዲሆን ጥሪ ቢቀርብለትም ዜግነቱ መቀየር አልፈለገም ነበር።
ተጫዋቹ በአንድ ወቅት በኖርዌይ ካለው ስም ይልቅ በጀመርን ያካበተው ዝና ይገዝፍ ነበር።
ነገር ግን በ1933 መስከረም ወር ላይ ሃርደር ተሰናብቶ ከሃምቡርግ ባቡር ጣቢያ በተነሳው ፉርጎ ሸከተፍ እያለ ወደ ኖርዌይ አቀና።
የታሪክ አስተማሪው እንደሚሉት ሃልቮርሰን ጀርመንን ለቆ የወጣው በፖለቲካው ምክንያት ነው ማለት ይከብዳል።
ሃልቮርሰን፤ ከሦስት ዓመታት በኋላ በ1936 በበርሊን ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ብሔራዊ ቡድኑን ይዞ ወደ ጀመርን ተመለሰ።
በሩብ ፍፃሜው ኖርዌይ ከጀመርን ተገናኙ። እግር ኳስ ወዳዱ አዶልፍ ሂትለር ጨዋታውን ለመታደም ስታድዬም ተገኘ።
ነገር ግን ብዙ የተባለለት የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በኖርዌይ 2 ለ 0 ተረትቶ ከውድድሩ ውጪ ሆነ።
ሂትለርም በንዴት ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ከስታድዬሙ እንደወጣ ይነገራል።
በ1940 ናዚዎች ኖርዌይን ወረሩ። ኖርዌይን በተቆጣጠሩት በአገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ የሆኑት ናዚዎች የእግር ኳስ ማኅበሩንም ማስተዳደር ፈለጉ።
በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ እና የእግር ኳስ ማኅበሩ ኃላፊ የነበረው ሃልቮርሰን ይህን የናዚዎች እርምጃ ተቃውሞ ደብዳቤ ፃፈ።
አልፎም የናዚ ባለሥልጣናት በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ ተገኝተው የናዚ አርማን እንዳያውለበለቡ የሚከለክል ሕግ አወጣ።
በ1942 ሃልቮርሰን በድብቅ ጋዜጣ እያተመ ነው ተብሎ በናዚ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር ዋለ። ለአንድ ዓመት ያህልም ኖርዌይ ውስጥ በእሥር ላይ ቆይቷል።
ለወንድሙ በላከው ደብዳቤ “ርቦኛል። ወደ ጀርመን ሊወስዱኝ እንደሚችሉ አስባለሁ” ሲል ጽፎ ነበር። ያለው አልቀረም ወደ ጀመርን እንዲጋዝ ተደረገ።
ሃልቮርሰን፤ የታሠረበት ካምፕ ያሉ ሰዎች እንደ የኮንስትራክሽን ሥራን የመሳሰሉ ከባድ የጉልበት ሥራዎች መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የኖርዌይ ጆይዝማር የተባለው ጋዜጣ እንደሚለው በዚህያ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙ ከ504 ኖርዌያዊያን እስረኞች መካከል 266 ብቻ ናቸው በሕይወት መትረፍ የቻሉት።
የካምፑ ጠባቂዎች ጨካኝ መሆን፣ የሰውነት መገርጣት እና በሽታ ለበርካታ እስረኞች ሞት ምክንያቶች ከሆኑት መካከል ናቸው።
ሃልቮርሰን በጀርመን የታወቀ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መሆኑ ጠቅሞታል። የካምፑ ጠባቂዎች ለእሱ የተሻለ እንክብካቤ ያደርጉለት ነበር።
በ1944 ሃልቮርሰን ወደ ሌላ ካምፕ ተዘዋወረ። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ደቡባዊ ጀርመን ወደ ሚገኝ የማጎሪያ ካምፕ ተወሰደ።
እዚህ ካምፕ እስረኛ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው ክሪስቲያን ኦቶሴን በዕለት የግል ማስታወሻው ላይ እንደጻፈው የካምፑ አልጋዎች በቅማል እና ቁንጫ የተወረሩ ነበሩ።
ኦቶሴን በጽሑፉ እንዳሰፈረው ሃልቮርሰን ለእስረኞች ድምፅ በመሆን የተሻለ ምግብ እንዲያገኙ ያደርግ ነበር።
ከዕለታት በአንዱ ቀን ከካምፑ ጠባቂዎች አንዱ ሃልቮርሰን ሌላ እስረኛ እንዲመታ ሲያስገድደው እምቢኝ በማለቱ ስቃይ እንደደረሰበት ጽፏል።
ሚያዚያ 1945 ሃልቮርሰን ድጋሚ ሃምቡርግ አቅራቢያ ወደሚገኝ ካምፕ እንዲዘዋወር ተደረገ። ሃልቮርሰን አንድ ሰሞን ታዋቂ ወደ ነበረባት ከተማ እስረኛ ሆኖ መጣ።
ረሃብ እና በሽታ ያሰቃዩት ያዙ። በተለይ ደግሞ በወቅቱ ተስፋፍቶ የነበረው የታይፈስ በሽታ ሰውነቱን እያደቀቀው ይመጣ ጀመር።
ኒውንጋም ተብሎ በሚጠራው ካምፕ እስረኛ የነበሩ ቢያንስ 42 ሺህ 900 ሰዎች እንደሞቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሃርደር የካምፑ ኃለቃ እያለ ለፈፀመው ግፍ 15 ዓመት ተፈርዶበት አራቱን ዓመት በእስር ካሳለፈ በኋላ በ1956 በ63 ዓመቱ ሞተ።
ሃልቮርሰን እና ሃርደር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአካል ተገናኝተው ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር የለም።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ሽንፈት ሲጠናቀቅ፣ በረሃብ እና በሽታ ሲሰቃይ የነበረው ሃልቮርሰን በ1945 በቀይ መስቀል እርዳታ ከካምፑ ወጣ።
“ረሃብን የመሰለ በጣም አሰቃቂ ነገር የለም” ሲል ካገገመ በኋላ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ተናግሮ ነበር።
ሃልቮርሰን ተመልሶ የኖርዌይ እግር ኳስ ማኅበር ዋና ፀሐፊ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በ1954 የዓለም ዋንጫ ኖርዌይ እና ጀመርን ሲጫወቱ ሃልቮርሰን ተመልሶ ወደ ሃምቡርግ ተጉዞ ነበር።
የሃልቮርሰን ጤና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጣ። እስር ላይ እያለ ያሳለፈው አካላዊ ስቃይ እና በሽታ አዳከሙት።
በስተመጨረሻም ሰኔ 1955 ሃልቮርሰን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።