ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጃፓን ሁለት አውሮፕላኖች ተጋጭተው አምስት ሰዎች ሞቱ
በጃፓን መዲና ቶኪዮ በሚገኘው ሃኔዳ አየር ማረፊያ ሁለት አውሮፕላኖች ተጋጭተው አምስት ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ንብረትነቱ የጃፓን አየር መንገድ የሆነው ግዙፍ ዘመናዊ ኤየርባስ ኤ350 አውሮፕላን ሃኔዳ አየር ማረፊያ እንዳረፈ ከሌላ የባሕር ጥበቃ አነስተኛ አውሮፕላን ጋር መጋጨቱ ተገልጿል።
በግዙፉ የመንገደኞች አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ 379 ሰዎች ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው ከአደጋው ማምለጥ የቻሉ ሲሆን በአስተኛው አውሮፕላን ተሳፍረው ከነበሩት ስድስት ሰዎች መካከል ግን አምስቱ ሕይወታቸው አልፏል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ አደጋውን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ግዙፉ ኤየርባስ ኤ350 አውሮፕላን በከባድ እሳት ሲጋይ አሳይተዋል።
ምስሎቹ ኤርባስ ኤ350 በአውሮፕላን መንደርደሪያ ላይ እንዳረፈ በእሳት እየነደደ በፍጥነት ሲሄድ አሳይተዋል።
የመንገደኞች አውሮፕላኑን በሙሉ በሙሉ በእሳት ከመያያዙ በፊት ተሳፋሪዎች እና የበረራ አስተናጋጆች በአደጋ ጊዜ መውጫ በኩል አምልጠዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የጃፓን ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው በአነስተኛው አውሮፕላን ተሳፍረው የነበሩት በአገሪቱ በተከሰተው ሱናሚ ጉዳት ለደረሰባቸው የአደጋ ጊዜ ቁሳ ቁስ ጭነው ለመብረር ዝግጅ ሲያደርጉ የነበሩት ናቸው።
የጃፓን መገናኛ ብዙሃን የአነስተኛው አውሮፕላን አብራሪ ከአደጋው ቢተርፍም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት እየዘገቡ ይገኛሉ።
አደጋውን ተከትሎ ወደ ቶኪዮ ሃኔዳ አየር ማረፊያ የሚደረጉ በረራዎች ተሰርዘዋል አልያም አቅጣጫቸውን ወደሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲቀይሩ ተደርጓል።
አውሮፕላን አምራቹ ኤየርባስ ክስተቱን በተመለከተ ከጃፓን አየር መንገድ ጋር ግንኙነት መፍጠሩን ገልጾ ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙ ይፋ አደርጋለሁ ብሏል።
ኤየርባስ ኤ350 አውሮፕላን ትልቅ የሚባል አደጋ ሲያጋጥመው ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት አውሮፕላኑ ላይ ከተያያዘው ትልቅ እሳት አንጻር በካርበን ፋይበር የተለበጠው የአውሮፕላኑ ፕላስቲክ አካል በፍጥነት በእሳት ሳይያያዝ በመቆየት ተሳፋሪዎች እንዲያመልጡ ዕድል ሰጥቷል።