አዲሱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠራው የቻትጂፒቲው አትላስ ምንድን ነው? ጉግል ክሮምንስ ይገዳደራል?

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ኦፕንኤአይ ማክሰኞ ዕለት አትላስ የተባለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚጠቀም አዲስ የድረ ገጽ ማሰሻ አስተዋውቋል። ይህም በዓለም ላይ በጣም ታዋቂውን ጉግል ክሮም ጨምሮ ሌሎችንም ለመገዳደር የተዘጋጀ ነው።
አትላስ ወደ ሥራ የገባው የቻትጂፒቲ ባለቤት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና እያደገ ካለው ተጠቃሚው ገቢ ለማግኘት አዳዲስ መንገዶችን በመፈለግ ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳም አልትማን፤ ቻትጂፒቲ 800 ሚሊዮን ሳምንታዊ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ገልጿል። ይህም በየካቲት ወር ከነበረው 400 ሚሊዮን በላይ ከፍ ያለ ነው።
የአትላስ ወደ ሥራ መግባት ደግሞ ኦፕንአይ ስለተጠቃሚዎች መረጃ ለመሰብሰብ የተሻለ ዕድል ይፈጥርለታል።
ዋና ዋና ባህሪያቱ ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አትላስ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ከዕለታዊ የድረገጽ አሰሳ ጋር ማዋሃድን ዓላማው አድረጎ ተነስቷል።
ባህላዊውን የአድራሻ አጠቃቀም በማስወገድ "በቻት ጂፒቲ ዙሪያ የተገነባ" ነው ሲል አልትማን ተናግሯል።
ተጠቃሚዎች መረጃዎችን ጠቅልል አድርገው ለማግኘት፣ ምርቶችን ለማነፃፀር ወይም ዳታ ለመተንተን በማንኛውም ገጽ ላይ የቻት ጂፒቲ መጠመቀም ይችላሉ።
በክፍያ የሚሠራው "ኤጀንት ሞድ" ቻትጂፒቲ ፍለጋዎችን እንዲያከናውን እና ከድረ ገጾች ጋር በተጠቃሚዎች ስም እንዲገናኝ ያግዛል። የጉዞ እቅድ እና የበይነ መረብ ግብይት የመሳሰሉ ተግባራትን እንዲያከናውን ያስችለዋል።
ማክሰኞ ዕለት በተደረገ የማሳያ ዝግጅት ላይ የኦፕንኤአይ ባለሙያዎች አትላስ የምግብ አሰራርን እንዲፈልግ እና ለምግቡ ግብዓቶችን በኢንስታካርት እንዲገዛ አዘዋል። ኢንስታካርት በአሜሪካ የሚገኝ የችርቻሮ ንግድ እና አቅራቢ ተቋም ነው።
ኦፕንኤአይ እንደ ኢትሲ እና ሾፒፋይ ካሉ የኢ-ኮሜርስ መድረኮች እንዲሁም ኤክስፒዲያ እና ቡኪንግዶትኮም ጨምሮ ከሌሎች የጉዞ አገልግሎት ተቋማት ጋር ሽርክና እንዳለው አስታውቋል።
«እንደ አትላስ ያሉ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠሩ የድረ ገጽ አሳሾችን መጠቀም የበለጠ ምቹ ነው። ምክንያቱም የተለያዩ መስመሮችን ከማለፍ፣ ከመጎብኘት እና የትኛው ተገቢ እንደሆነ ከማየት ይልቅ አሁን [ድረ] ገጾቹን ይዘት አሰባስበው ማግኘት ይችላሉ" ይላሉ በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ኃላፊ ፕሮፌሰር ኤሌና ሲምፐርል ተናግረዋል።
ሆኖም የሚያገኟቸው ማጠቃለያዎች ትክክለኛነት አጠራጣሪ ሊሆኑ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
"የእያንዳንዱ የቻትቦት ችግር በታመነ ድረ ገጽ የተጻፈ ጉዳይን ከማይታመን ምንጭ ከተጻፈው መለየት አለመቻሉ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ስጋቶችስ አሉት?

የፎቶው ባለመብት, PA Wire/PA Images
ኦፕንኤአይ ለአትላስ መከላከያዎችን መገንባቱን ቢገልጽም ግን በተጠቃሚዎች ምትክ እርምጃዎችን መውሰድ የሚችለው ወኪሉ አደጋዎች እንደሚኖሩት አምኗል።
በእነዚህ ጥበቃዎች መሠረት፣ አሳሹ ኮድን መስጠት፣ ፋይሎችን ማውረድ ወይም ሌሎች መተግበሪያዎችን መድረስ አይቻለውም። እንደ ባንኮች ባሉ ሚስጥራዊ ድረ-ገጾች ላይም ማቆም አይችልም። ተጠቃሚዎች ተጋላጭነትን ለመገደብ ማንነታቸውን ሳያሳውቁ ማከናወን ይችላሉ።
በድረ-ገጾች ወይም በኢሜይሎች ውስጥ የተደበቁ ተንኮል አዘል መመሪያዎችን ጨምሮ ስሀተቶች እንደሚኖሩ ኦፕንኤአይ ያስጠነቅቃል። እነዚህም ወደ ያልተፈለጉ እርምጃዎች ወይም የዳታ ስርቆት ሊያመሩ ይችላሉ።
ኩባንያው ሰፊ ሙከራ እንዳደረገ እና ተጋላጭነቶችን መቅረፉን እንደሚቀጥል ቢናገርም፣ ተጠቃሚዎች መረጃዎቻቸውን ሲያጋሩ እና ግብይቶችን ሲፈጽሙ እንዲጠነቀቁ መክሯል።
"መረጃዎቻችንን እስካሁን እምነት ባልተጣልበት ኩባንያ እጅ ውስጥ እያስቀመጥን ነው" ብለዋል ፕሮፌሰር ሲምፐርል።
"ይህም ለመሞከር ትንሽ ጠንቃቃ ያደርገኛል" ሲሉ አክለዋል።
አትላስ የአሰሳ ታሪክዎን የሚያስታውስ እና ሲጠየቅም ማቅረብ የሚያስችለውን 'ብራውዘር ሚሞሪስ'ን አካቷል። ኦፕን ኤአይ ግን ይህ 'ሙሉ በሙሉ አማራጭነት ቀረበ ስለሆነ ሁልጊዜም በእርስዎ ቁጥጥር ስር ነው' ብሏል።
ጉግልን እንዴት ሊገዳደር ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በርካታ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መልሶችን እና ምክሮችን ሲፈልጉ እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ትላልቅ የቋንቋ ሞዴሎችን (ኤልኤልኤምስን) ለመጠቀም እየመረጡ ነው።
ተጠቃሚዎች ጉግልን ከመሰሉ ከተለመዱ የበይነ መረብ መፈለጊያዎች ይልቅ መረጃን የሚያዋህዱ የውይይት መሳሪያዎችን ወደ ሚጠቀሙ እንደ አትላስ ያሉ የኤአይ መፈለጊያዎች በስፋት እንዲጎርፉ ሊያደርግ ይችላል።
የምርምር ተቋሙ ዳቶስ እንደገለጸው ከሆነ ከሐምሌ 2025 ጀምሮ በዴስክቶፕ ማሰሻዎች ላይ ከተደረጉት ፍለጋዎች 5.99 በመቶ የሚሆኑት በኤልኤልኤምስ በኩል ተከናውነዋል። ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው አሃዝ በእጥፍ ይበልጣል።
ጉግልም ግን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ አድርጓል። ባለፈው ዓመት በፍለጋ ውጤቶቹ ውስጥ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጁ መልሶችን ቅድሚያ ሰጥቶ ማቅረብ ጀምሯል።
ባለፈው ወር ደግሞ ጉግል የጄሚናይ ኤአይ ሞዴሉን ከክሮም ጋር አዋህዶ ለአሜሪካ ተጠቃሚዎች አቅርቧል። ጀሚናይን ወደ አይኦሴእ ክሮም መተግበሪያ ለማምጣትም አቅዷል።
"ቀደምት ተጠቃሚዎች በአዲሱ ኦፐንኤአይ አሳሽ ላይ ጫና እንደሚፈጥሩ አምናለሁ" ሲሉ የሙር ኢንሳይትስ ኤንድ ስትራቴጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓት ሙርሄድ ተናግረዋል።
አትላስ ክሮም ወይም ማይክሮሶፍት ኤጅ ላይ ከባድ ፈተና ይፈጥራል ወይ በሚለው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። "ብዙ ዋና ዋና ተዋናዮች፣ ጀማሪዎች እና የኮርፖሬት ተጠቃሚዎች ይህንን አሰራር እስኪያገኙ ድረስ ይጠብቃሉ" ብለዋል።
ማይክሮሶፍት ኤጅ ዛሬ ላይ እነዚህን አሠራሮች ያቀርባል ሲሉ ሙርሄድ አክለዋል።
የኦፕንኤአይ አትላስ ወደ ገበያ የገባው ጉግል በበይነ መረብ ፍለጋ ላይ ህገወጥ የበላይነት (ሞኖፖሊ) እንዳለው ከተረጋገጠ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው።
መስከረም 2025 የጉግልን የበላይነት ለመግታት የታሰበ ውሳኔ ቢሰጥም ኩባንያው የክሮም መፈለጊያውን እንዲያጠፋ ማስገደድ አልተቻለም።
ፉክክሩ ቢጨምርም ጉግል ክሮም የበላይነቱን ይዞ ቆይቷል። በመስከረም ወር በዓለም አቀፍ የመረጃ ማሰስ ገበያ ውስጥ 71.9% የገበያ ድርሻ እንዳለው ስታት ካውንተር ዘግቧል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ከኦፕንኤአይ የቀረበው አዲስ አማራጭ ለማስታወቂያ ገቢ አዲስ ተወዳዳሪ ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራሉ።
"ቻትን ወደ ድረ ገጽ ማሰሻ ማስገባት ለኦፕንኤአይ ማስታወቂያዎችን መሸጥ ለመጀመር ቅድመ ሁኔታ ነው። ይህንንም እስካሁን ድረስ እስካሁን አላደረገውም። ኦፕንኤአይ ከጉግል የማስታወቂያ ድርሻ ከፍተኛ ድርሻን ሊወስዱ የሚችሉ ማስታወቂያዎችን መሸጥ ይጀምራል። ጉግል ከገቢው 90% አካባቢ የሚሆነውን ከማስታወቂያ ያገኛል" ይላሉ የዲኤ ዴዳቪድሰን ተንታኑ ጊል ሉሪያ።
መቼ ወደ ሥራ ይገባል?
ቻትጂፒቲ አትላስ አሁን በአፕል ማክኦኤስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ላይ ለነፃ፣ ለፕላስ፣ ለፕሮ እና ለጎ ተጠቃሚዎች ቀርቧል።
በቤታ ደረጃ ደግሞ ለቢዝነስ (በፈቃድ ላይ ተመስርቶ)፣ ለኢንትርፕራይዝ እና ለኤዱ ተጠቃሚዎች ማግኘት ይቻላል።
ኦፕንኤአይ እንዳለው ከሆነ ለዊንዶውስ፣ ለአይኦኤስ እና ለአንድሮይድ ተጠቃሚዎች ደግሞ ከጊዜ በኋላ ይቀርባል።















