የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሰው ልጅን ድምጽ ለይቶ ማወቅ ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Estudio Santa Rita
በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካይነት የሰዎችን ድምጽና የተለያዩ አገራትን የንግግር ቅላጼ ማስመሰል ተችሏል።
ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ንግግር ማድረግም የተቻለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት እንደየአስፈላጊነቱ ይሰጣል።
የታዋቂ ሰዎችን ድምጽ አስመስሎ ንግግር ሊያደርግም ይችላል።
ይህንን መንገድ በመጠቀም ገንዘብ ለማግኘት የሚሞክሩ ወንጀለኞች ተበራክተዋል።
ተፈጥሯዊና አሳማኝ በሆነ መንገድ ሰው ሠራሽ አስተውሎት መነጋገር መቻሉ ለብዙ ጥያቄዎች በር ከፍቷል።
ሰዎች ስሜታቸውን ለመግለጽ የሚጠቀሟቸውን ቅላጼዎች ቻትጂፒቲ ማስመሰል ችሏል።
ቃላትን ብቻ ሳይሆን ትንፋሽን፣ የለቅሶ ወይም የሳቅ ድምጽን ሰምቶም የሚለይበት ደረጃ ደርሷል።
ቻትጂፒቲ አሁን ላይ 50 ቋንቋዎችን ይረዳል።
አስፈላጊ ከሆነ ለሰዎች የስልክ ጥሪ ሊያደርግም ይችላል።
ለመሆኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሰው ልጅን ድምጽ መለያየት ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
በጀርመን፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሙኒክ፣ የፎነቲክስና ዲጂታል ንግግር ባለሙያ የሆነው ጆናታን ሀሪንግተን እንደሚለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት የደረሰበት የንግግር ደረጃ አስደናቂ ነው።
“ባለፉት 50 ዓመታት የቃላትና ድምጽ አወጣጥ እየተሻሻለ መጥቷል። ከሰዎች ድምጽ ጋር ለመለየት አስቸጋሪ እየሆነም ነው” ይላል።
በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ ስተርን ስኩል ኦፍ ቢዝነስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያ የሆነው ኮነር ግሪናን ‘አሊስ ኢን ወንደርላንድ’ ከሚለው መጽሐፍ የተወሰነ አንቀጽ በማንበብ ሙከራ ሠርቷል።
የሱን ድምጽ በኢለቨንላብስ ከተሠራ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ድምጽ ጋር አነጻጽሯል።
ሁለቱንም ድምጾች የሰሙ ሰዎች የትኛው በሰው የተነበበ የትኛው ደግሞ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተነበበ ሆኑን ለመለየት ተቸግረዋል።
በማካፊ የበይነ መረብ ደኅንነት የሚሠራው ስቲቭ ግሮብማ እንደሚለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሰው ልጅን ድምጽ መለያየት የሚቻልበትን መንገድ ለማያውቅ ሰው ልዩነታቸውን ማግኘት ቀላል አይሆንም።
“ንግግር ሲደረግ ትንፋሽ ለመውሰድ የሚወስደው ጊዜና የድምጽ ከፍና ዝቅ ማለትን ማስተዋል ያስፈልጋል” ይላል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሰው ልጅን ድምጽ መለያየት የሚችሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች የተሻለ ዕድል እንዳላቸው ያስረዳል።
የታዋቂ ሰዎችን ድምጽ በማስመሰል ወይም እውነተኛ ድምጻቸውን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ከተሠራ ድምጽ ጋር በማደባለቅ የሚለቀቁ ሐሰተኛ ድምጾችን ለመለየት ጥንቃቄ እንደሚያሻ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የበይነ መረብ ደኅንነት ባለሙያው ፒት ኒኮሌቲ እንደሚለው በንግግር መካከል የሚደረግ እረፍትን አልያም የአረፍተ ነገር አወቃቀርን በማስተዋል ሐሰተኛ ድምጽን ከእውነተኛ ለመለየት መሞከር ይቻላል።
የድምጽ ምጣኔ ከፍና ዝቅ ሲል በማድመጥ እንዲሁም ከንግግሩ ጀርባ የሚሰሙ ድምጾችን እውነተኛነት ለመለየት መሞከርም ሌላኛው መንገድ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Estudio Santa Rita
በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሠሩ ድምጾች “ማንኛውንም ሰው ማሳሳት ይችላሉ” ሲል ባለሙያው ያስረዳል።
ሰዎች ንግግር ሲያደርጉ ትኩረት የሚሰጧቸውን ቃላት በመከተል ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ንግግር ላይ ለመለየት የሞከሩ ባለሙያዎች አሉ።
የንግግሩን ዐውድ ለመረዳት መሞከርም ሌላው መንገድ ነው።
አረፍተ ነገር ውስጥ የትኞቹ ቃላት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል የሚለውን በመከተል አልያም አረፍተ ነገሩ ጥያቄ ነው ወይስ መልስ የሚለውን በመለየት የሰዎችን ድምጽ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ድምጽ ጋር ለመለየት እንደሚቻል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
አንድ አረፍተ ነገር ውስጥ ያሉ ቃላት እንዴት ተከፋፈሉ የሚለውም ልዩነቱን ሊጠቁም ይችላል።
ሆኖም ግን ሰው ሠራሽ አስተውሎት እያደገ ሲመጣ የበለጠ የሰው ልጆችን ስለሚያስመስል ለመለየት ይከብዳል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የፎነቲክስና ዲጂታል ንግግር ባለሙያ የሆነው ጆናታን ሀሪንግተን “ቴክኖሎጂ ኃያል ሊሆንበት የሚችለው ያህል ሆኗል። 60% ሰውን ማስመሰል ቢችል እንኳን ቀላል አይደለም። በቀጣይም ዋጋው እየረከሰ፣ ፍጥነቱ እየጨመረና ትክክለኛነቱ እያደረገ ይሄዳል” ይላል።
ዊዝ በተባለው የበይነ መረብ ደኅንነት ተቋም የሚሠራው አሳፍ ራፓሮት እንደሚለው የሰዎችን ድምጽ የሚያስመስሉ መተግበሪያዎች ንግድን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች አስጊ እየሆኑ ነው።
የአንድ መምህርን ድምጽ በማስመሰል ዘረኛ ንግግር በበይነ መረብ ከተለቀቀ በኋላ መምህሩ የግድያ ዛቻ ሲደርስበት ነበር።
የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች የባንክ ዝርፊያን ጨምሮ ለሌሎችም ወንጀሎች ድምጽ የሚያስመስሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች መጠቀማቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
“ቤተሰቦቻችን ሲደውሉልን ወይም መሥሪያ ቤት ሆነን ሲደወልልን በትክክል የደወለው ማነው ብለን ማጣራት ሊኖርብን ነው” ይላል ባለሙያው።
ማረጋገጫ ለማግኘት ግላዊ ጥያቄዎች መጠየቅ ወይም መልሶ በመደወል ለማጣራት መሞከርን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የበይነ መረብ ደኅንነት ባለሙያው ማይክል መክነሪ እንደሚለው ሰዎች ሲናገሩና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲናገር ለመለየት ስህተቶችን መከተል ይቻላል።
በጣም ጥርት ያለ ወይም የተስተካከለ ድምጽን በመለየት የትኛው ድምጽ የሰዎች እንደሆነ ለመለየት ይሞክራል።
የሥራ ባልረቦቻቸው ወይም አለቆቻቸው አልያም ደግሞ ደንበኞቻቸው እንደደወሉላቸው አምነው ገንዘብ የሚያስተላልፉ፣ ፖለቲከኞች አንድን ንግግር እንዳደረጉ አምነው የሚታለሉም ጥቂት አይደሉም።

የፎቶው ባለመብት, Estudio Santa Rita
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች በሰዎችና በሰው ሠራሽ አስተውሎት መካከል ያለውን የድምጽ ልዩነት ለማግኘት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
“ሰው ሠራሽ አስተውሎት ልክ እንደ ሰው የንግግር ስህተትን ለማስመሰል መሞከሩ ያስገርማል። አስፈሪም ነው” ሲል ከባለሙያዎቹ አንደኛው የበይነ መረብ ደኅንነት ባለሙያው ማይክል መክነሪ ተናግሯል።
በንግግር ወቅት ሰዎች ከቀደመ ተሞክሯቸው ወይም እውቀታቸው ተነስተው በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ ካሉ ቃለት መካከል ለየትኛው ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይችላሉ የሚለውን ለመለየት መሞከር ሌላው ባለሙያዎች የሚሰጡት ምክር ነው።
ሆኖም ግን ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሰጠው መረጃ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ሰውን የማስመሰል አቅሙም መጨመሩ አይቀርም።
ቻትጂፒቲ መሳቅና ማንሾካሾክ ይችላል። ሰዎች የሚሉትን ነገር በቀጣይ ማስታወስም ይችላል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰው ሠራሽ አስተውሎት መሆኑን ለሰዎች እንዲገልጽ ማድረግ ይቻላል።
በቻትጂፒቲ የቋንቋ ክፍል ባለሙያዋ ጃኪ ሻኖን እንደምትለው ቻትጂፒቲ ድምጽን እንዳያስመስል ለማድረግ ይሞክራሉ።
“የሰዎችን ትክክለኛ ድምጽ እንዳያስመስል ለማድረግ እንሞክራለን። ግን ሰው ሠራሽ አስተውሎት መሆኑን ለሰዎች እንዲገልጽ አይደረግም” ትላለች።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ድምጽ በጣም ከሰው ልጆች ድምጽ ጋር ተመሳስሎ ጥንጣሬ ከፈጠረ እንዲጮህ በመጠየቅ ማጣራት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከመደበኛው የድምጽ አወጣጥ ለመውጣት ይቸገራል። ሆኖም ግን ይህንን እንዲያደርገም ማሠልጠን ይቻላል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የበይነ መረብ ደኅንነት ባለሙያው ፒት ኒኮሌቲ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲጮህ ሲጠይቀው “አልችልም” ብሎ እንደመለሰ ይናገራል።
ሰዎች ንግግር ሲያደርጉ ሊሳሳቱ ወይም ሐሳባቸውን ለማስተካከል ወደ ኋላ ሊመለሱ ይችላሉ። ይህም ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ለመለያየት ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ሌላ መንገድ ነው።
እንደ ማክፊ ያሉ የበይነ መረብ ደኅንነት ተቋሞች ከዴል፣ ኤችፒ፣ ለኖቮ፣ ሳምሰንግ፣ አሰር እና አሰስ ጋር በመሆን ሐሰተኛ ድምጽ ለመለየት ይሞክራሉ።
በስልክ የሚጫኑ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሰው ልጅን ድምጽ ለመለያየት መሞከርም ይጠቀሳል።















