የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዛከርበርግ እጅግ ዘመናዊ ያለውን በኤአይ የሚሠራ መነፅር ይፋ አደረገ

የሜታ ባለቤት የሆነው ማርክ ዛከርበርግ በኤአይ የሚታገዝ መነፅር ሲያስተዋውቅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሜታ ባለቤት የሆነው ማርክ ዛከርበርግ በኤአይ የሚታገዝ መነፅር ሲያስተዋውቅ

የፌስቡክ እናት ድርጅት የሆነው ሜታ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አሊያም ኤአይ የታገዙ የተለያዩ የዓይን መነፅሮችን ይፋ አድርጓል።

የሜታ ኃላፊ የሆነው ማርክ ዛከርበርግ 'ሜታ ኮኔክት' በተሰኘው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ነው ከመነፅር አምራቾቹ ሬይ ባን እና ኦክሊ ጋር በተመባበር በኤአይ የሚሠሩ የዓይን መነፅሮች መሥራቱን ያስታወቀው።

ኩባንያው አክሎም 'ኒውራል ሪስትባንድ' የተባለ ከሜታ ሬይ-ባን መነፅሮች ጋር በመጣመር በእጅ ምልክት ብቻ የፅሑፍ መልዕክት መላክ የሚችል ቴክኖሎጂ መፍጠሩንም አስታውቋል።

የፌስቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ የሚያመርታቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሕፃናት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሱ ነው የሚል ክስ ይቀርብበታል።

ሲሊከን ቫሊ በሚገኘው የድርጅቱ ቅጥር ግቢ በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኘው ዛከርበርግ፣ አዲሱ መነፅር ቴክኖሎጂው ዘርፍ "ትልቅ እመርታ የሚያመጣ እና እጅግ ዘመናዊ" ሲል በመቶዎች ለሚቆጠሩ ታዳሚዎች ተናግሯል።

ሜታ ሬይ-ባን ዲስፕሌይ የተሰኘ ስም የተሰጠው ይህ መነፅር ከፍተኛ ጥራት ያለው (ሀይ ሪዞሉሽን) ተጠቃሚዎች የቪድዮ የስልክ ልውውጥ የሚያደርጉበት ስክሪን ተገጥሞለታል። 12 ሜጋፒክስል ካሜራም አለው።

ዛከርበርግ ሜታ የሚያመርታቸው የቴክኖለጂ ውጤቶች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በማጣመር የሰዎችን ሕይወት ቀለል ያደርጋሉ የሚል ተስፋ እንዳለው ተናግሯል።

ተንታኞች ኩባንያው ቢሊዮን ዶላሮች ካወጣበት ሜታቨርስ ፕሮጀክት ይልቅ ስማርት መነፅሮች በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነት ሊያተርፉ እንደሚችሉ ገምተዋል።

ኩባንያው ስማርት መነፅሮችን ካስተዋወቀበት ከ2023 ጀምሮ ቢያንስ 2 ሚሊዮን መነፅሮችን መሸጡን አስታውቋል።

ሜታ ሬይ-ባን ዲስፕሌይ በዚህ ወር (መስከረም) ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ ዋጋውም 799 ዶላር አሊያም 110 ሺህ ብር ገደማ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ ዋጋ አሁን ገበያ ላይ ካሉት የሜታ ስማርት መነፅሮች እጅግ የላቀ ነው።

ዛከርበርግ ከዚህ በተጨማሪ በ499 ዶላር ኦእከሊ ሜታ ቫንጋርድ የተባሉ ስፖርት ለሚያዘወትሩ ሰዎች የተሠሩ መነፅሮችን እንዲሁም 379 ዶላር የሚያወጡ የሬይ-ባን 'ሰከንድ ጄኔሬሽን' መነፅሮችን አስተዋውቋል።

በኤአይ የሚታገዙ ምርቶችን ለተጠቃሚዎቹ እያስተዋወቀ የሚገኘው ሜታ ይህን ዕቅዱን ለማሳካት ቢሊዮን ዶላር እያፈሰሰ ይገኛል።

ማርክ ዛከርበርግ ባለፈው ሐምሌ ኩባንያው በአሜሪካ የኤአይ ዳታ ማዕከላትን ለመገንባት ቢሊዮን ዶላሮችን እንደሚያወጣ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።

ሜታ 'ሱፐርኢንተለጀንስ' የተባለ ከሰዎች የማሰብ አቅም የላቀ ችሎት ያለው ቴክኖሎጂ ለመገንባት እየተሯሯጠ እንደሆነም አስታውቋል።

ረቡዕ ዕለት አክቲቪስቶች እና ልጆቻቸውን በራስ ማጥፋት ያጡ ወላጆች በኒው ዮርክ የሜታ ቅርንጫፍ ተገኝተው ሕፃናት የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።