በጣሊያን 32 ሺህ አባላት ያሉት የፌስቡክ ገጽ የሴቶችን ፎቶዎች ያለፈቃዳቸው ማጋራቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፌስቡክ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Beata Zawrzel/NurPhoto via Getty Images

ፌስቡክ እርቃናቸውን የተጋለጡ፣ ተኝተው እና በሌሎች ሁኔታዎች ያሉ የሴቶችን ፎቶዎች ያለፈቃዳቸው ያጋራውን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች አባላት ያሉት አንድ ገጽ መዝጋቱን አስታወቀ።

ሚያ ሞግሊ (የኔ ሚስት) የሚል መጠሪያ ያለው ይህ የፌስቡክ ገጽ በዚህ ሳምንት ከመዘጋቱ በፊት 32 ሺህ አባላት ነበሩት።

በሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሉት የዚህ ገጽ ግኝት በጣሊያን ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።

የፌስቡክ ባለቤት ሜታ "የአዋቂዎች የወሲባዊ ይዘቶችን ፖሊሲዎች በመጣሱ" ገጹን እንደዘጋው አስታውቋል።

የፌስቡክ ገጹ ከመዘጋቱ በፊት የተነሱ ፎቶዎች (ስክሪንሾት) ሴቶች በተለያየ መንገድ ራቁታቸውን ተጋልጠው፣ ተኝተው እንዲሁም በፍትወት ሁኔታዎች ላይ እያሉ ያሳያል።

በልጥፎቹ ስር ከወንዶች ግልጽ የሆኑ ወሲባዊ መልዕክቶች ተላልፈውባቸዋል።

አንዳንዶች በፎቶው ላይ የምትታየውን ሴት ለመድፈር እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ የአንዳንዶቹን ፎቶዎች ምስጢራዊነት አወድሰዋል።

ገጹን አስመልክቶ ጣሊያናዊቷ ጸሐፊ ካሮላይና ካፒራ "ማቅለሽለሽ" እንደተሰማት እና ባየችውም ነገር "እንደደነገጠች" አስፍራለች።

"ጥቃትን ከወሲባዊ ግንኙነት ጋር ማቆራኘት በባህላችን ስር በመስደዱ ህዝብ በሚያያቸው ጽሁፎች ላይ ወንዶችን ፊታቸውን እና ስማቸውን ሳይደብቁ በዚህ መንገድ አስተያየታቸውን እየገለጹ ነው" ብላለች።

የአውሮፓ ግሪን ፓርቲ አባል የሆኑት ፊዮሬላ ዛባታ በበኩላቸው "ምንም ጉዳት የሌለው መዝናኛ" አይደለም "ይሄ በኦንላይን መደፈር ነው" ብለዋል።

"እነዚህን መድረኮቸን ልንታገላቸው ይገባል፤ ይህን መርዛማ የወንድነት እሳቤ እንዲሁ ትግል ያስፈልገዋል። ሁላችንም፣ የሲቪል ማህበረሰቡ፣ ፖለቲካው እርምጃ ልንወስድ ይገባል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በግል የተቀረጹ ወሲባዊ ትዕይንቶችን ሰዎችን ለመበቀል ቪዲዮዎችን ማጋራት ወይም የበቀል ወሲብ (ሪቬንጅ ፖርን) ተብሎ የሚጠራው በጣልያን በአውሮፓውያኑ 2019 ህገወጥ ሆኗል።

ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ይህንን ገጽ የሳይበር ወንጀልን ለሚመረምረው የፖሊስ ክፍል አስቀድመው ሪፖርት ማድረጋቸውን የጣልያን የሚዲያ ዘገባዎች አሳይተዋል።

"ወሲባዊ ጥቃቶችን፣ ብዝበዛዎችን የሚያበረታቱ እንዲሁም ሰዎችን የሚያስፈራሩ ይዘቶችን በመድረካችን እንዲተዋወቁ አንፈቅድም" ሲል ሜታ በመግለጫው አትቷል።

የጣልያን ፌስቡክ በፈረንሳይ ከተከሰተው ጂዜል ፔሊኮት ጋር በርካቶች አመሳስለውታል።

ባለፈው ዓመት ዶሚኒክ ፔሊኮት የተባለ ግለሰብ ባለቤቱን ጂዜል ፔሊኮትን አደንዝዞ በመድፈር እና ከ50 በላይ በማያውቋት ወንዶች በማስደፈሩ የ20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

የፔሊኮት ጉዳይ ለብቻው የተነጠለ ሳይሆን ከዚህም ጋር እንደሚያያዝ የጠቀሰችው ካፕሪያ "ባለቤቱን መቆጣጠር እንደሚችል የሚያምንና ወሲባዊ ግንኙነትን ከጭቆና ጋር ያቆራኘ ሰው ነበር" ስትል ገልጻለች