በኤአይ አማካይነት ወሲብ ቀስቃሽ ይዘት ለመፍጠር የተሰረቀው የሕንዳዊቷ ማንነት

ቤቢዶል አርቺ

የፎቶው ባለመብት, Babydoll Archi

የምስሉ መግለጫ, ቤቢዶል አርቺ

የቤቢዶል አርቺ ኢንስታግራም ተከታዮች ቁጥር በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ 1.4 ሚሊዮን ጨምሯል፤ አዳዲስ አድናቂዎቿ በየቀኑ እየገቡ ፎቶዎቿን እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎቿን ይመለከታሉ።

በሕንድ ውስጥ በብዙ በተሠራጨ አንድ ቪዲዮ ላይ የቀይ የሕንድ ባህላዊ ልብስ ለብሳ 'ዳም ኡን ግር' በተሰኘ የሮማኒያ ዘፈን በሚያማልል ሁኔታ ስትጨፍር ታየች።

በሌላ ፎቶ ከአሜሪካዊቷ ጎልማሳ የፊልም ተዋናይ ኬንድራ ለስት ጋር ትታያለች።

ቪዲዮው እና ፎቶው ድንገት ዝነኛ እንድትሆን አድርጓታል።

ስሟ በጎግል መፈለጊያ ላይ በብዙዎች ተተይቧል፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የአድናቂዎች ገጽ እና ቧልቶች ተንሰራፍተዋል።

ከሰሜን ምሥራቅ የአሳም ግዛት የመጀመሪያዋ ሰው ሆና የዩናይትድ ስቴትስ የወሲብ ኢንዱስትሪን እንደምትቀላቀል የሚገምቱ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ እሷን "ተፅእኖ ፈጣሪ" ሲሉ ገለፃ በማድረግ ወጀቡን ተቀላቅለው ስለማንነቷ ዘገባዎች ለመሥራት ሞክረዋል።

"ቤቢዶል አርቺ ማን ናት?" የሚለው የፍለጋ ቃል አርዕስተ ዜና እስከመሆን ደርሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን ከዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ወጀብ ጀርባ እውነተኛ ሴት የለችም።

የኢንስታግራም አካውንቱ የውሸት ነበር። ነገር ግን የተጠቀመበት ፊት በአሳም ውስጥ በዲብሩጋርህ ከተማ ውስጥ የምትኖር ሳንቺ እያልን ከምንጠራት ከእውነተኛ ሴት ጋር እንግዳ በሆነ መልኩ የሚመሳሰል ነበር።

ወንድሟ ለፖሊስ ቅሬታ ካቀረበ በኋላ እውነቱ ተገለጠ። የሳንቺ የቀድሞ ፍቅረኛ ፕራቲም ቦራ ታሰረ።

ምርመራውን የሚመሩት ፖሊስ ሲዛል አጋርዋል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሳንቺ እና ቦራ ወደ ጠብ መግባታቸውን እና የፈጠረው በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተቀነባበረ ምሥል በእሷ ላይ "ንፁህ የበቀል እርምጃ" ሊወስድባት ነው ብለዋል።

ቦራ ራሱን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ያስተማረ የሜካኒካል መሐንዲስ ሲሆን፣ የሳንቺን የግል ፎቶዎች የውሸት መገለጫ ለመፍጠር ተጠቅሟል ሲሉ አጋርዋል ተናግረዋል።

ቦራ በእስር ላይ ነው፤ እና እስካሁን ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጠም።

ቢቢሲ ቤተሰቦቹን ለማነጋገር ሙከራ አድርጓል።

ቤቢዶል አርች እአአ በ2020 የተፈጠረች ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ ልጥፎች በግንቦት 2021 ተደርገዋል።

የመጀመሪያዎቹ ፎቶግራፎች የተቀረጹ እውነተኛ ምሥሎች ናቸው ሲሉ አጋርዋል ተናግረዋል።

"ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ቦራ የኤአይ ምሥሎቹን ለመፍጠር እንደ ቻት ጂፒቲ እና ድሪንዝ ያሉ መተግበሪያዎችን ተጠቅሟል። ከዚያም የኢንስታግራም ገጹን በውሸት ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ሞላው።"

ገጹ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሰዎችን ትኩረት ማግኘት ቢጀምርም በዚህ ዓመት ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ብዙዎችን መሳብ እንደጀመረ ተናግረዋል።

በዚህ ወር ሐምሌ መጀመሪያ ምሽት በሳንቺ ቤተሰቦች ለፖሊስ የቀረበው አጭር ባለ ሁለት አንቀፅ ቅሬታ የተወሰኑ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን በማስረጃነት አያይዟል።

አጋርዋል ከድርጊቱ ጀርባ ያለው ሰው ማን እንደሆነ ስለማያውቁ ቤተሰቦቿ የማንንም ስም በቅሬታቸው ላይ አልጠቀሱም ይላሉ።

ኤአይ የሚል ጽሁፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቤቢዶል አርቺ ለፖሊስ የማይታወቅ ስም አልነበረም።

አጋርዋል እሷ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈጠረች ናት ብለው የሚዲያ ዘገባዎችን እና አስተያየቶችን እንዳዩ ነገር ግን በእውነተኛ ሰው ላይ የተመሠረተች ናት የሚል አስተያየት አልቀረበም ይላሉ።

ቅሬታው እንደደረሳቸው ፖሊስ የገጹን ፈጣሪ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ለኢንስታግራም ጽፏል።

"ከኢንስታግራም መረጃ እንደደረሰን ሳንቺ ፕራቲም ቦራ የሚባል ሰው ታውቅ እንደሆነ ጠየቅናት። አንዴ ካረጋገጠች በኋላ በአጎራባች የቲንሱኪያ አውራጃ አድራሻውን ፈልገን አገኘነው። ቅሬታው በቀረበ ማግስት ምሽት ላይ በቁጥጥር ስር አውለነዋል።"

አጋርዋል ፖሊስ "ላፕቶፑን፣ ሞባይል ስልኮቹን እና ሃርድ ድራይቭ እና የባንክ ሰነዶቹን ይዟል" ብለዋል።

"ገጹ በሊንክትሪ ላይ 3 ሺህ ተመዝጋቢዎች ነበሩት እና ከእሱ ከ10 ሺህ ዶላር በላይ እንዳገኘ እናምናለን። እሱ ከመያዙ በፊት ባሉት በአምስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ3 ሺህ ዶላር በላይ እንዳገኘ እናምናለን" ሲሉ አክለዋል።

አጋርዋል፣ ሳንቺ "በጣም ተጨንቃለች፤ አሁን ግን እሷ እና ቤተሰቧ ምክር እየተሰጣቸው ነው፤ እናም በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው" ብለዋል።

እንደዚህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት ለመከላከል ምንም ዓይነት መንገድ የለም። ነገር ግን ቀደም ብለን እርምጃ ወስደን ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ትኩረት እንዳያገኝ ልንከለክለው እንችል ነበር ብለዋል አጋርዋል ።

"ሳንቺ ግን ምንም ዓይነት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ስለሌላት ስለጉዳዩ ምንም የምታውቀው ነገር የለም። ቤተሰቦቿም ገጹን እንዳያዩ በቦራ ታግደዋል" ሲሉ አክለዋል።

ሜታ በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም፤ ነገር ግን በአጠቃላይ እርቃንን ወይም ወሲባዊ ይዘት ያለውን ልጥፍ አይፈቅድም።

የቆመች አንዲት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምንም እንኳን ማኅበራዊ ሚዲያ በፎቶዎቿ እና በቪዲዮዎቿ የተሞላ ቢመስልም 282 ልጥፎች የነበረው የቤቢዶል አርቺ ኢንስታግራም ገጽ አሁን ለሕዝብ ተደራሽ አይደለም።

ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ ሜታን ጠይቋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያ እና ጠበቃ የሆኑት ሜግና ባል፣ ሳንቺ ላይ የተከሰተው ነገር "አስፈሪ ነው፤ ነገር ግን ለመከላከል ፈጽሞ የማይቻል ነው" ይላሉ።

ወደ ፍርድ ቤት ሄዳ የእሷን ስም የያዙ ይዘቶች በሙሉ እንዲወገዱ ልትጠይቅ ትችላለች፤ ፍርድ ቤትም ስሟን የያዙ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንዲወርዱ ሊያዝዝ ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉንም ከእሷ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ከኢንተርኔት ማጽዳት ከባድ ነው።

በሳንቺ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ በሌሎች ሴቶች ላይም እየደረሰ ነው፣ ፎቶዎቻቸው እና ቪዲዮዎቻቸው እንደ በቀል እየተሠራጩ ነው ይላሉ ጠበቃዋ።

የኤአይ ባለሙያዋ እና ጠበቃዋ "አሁን በኤአይ ምክንያት ነገሩ በጣም ቀላል ነው፤ ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ክስተቶች እኛ የምንጠብቀውን ያህል የተለመዱ አይደሉም። ወይም ደግሞ በመገለል ምክንያት ሪፖርት ሊደረጉ ወይም የተጠቁ ሰዎች አሁን ባለው ሁኔታ ስለ እሱ እንኳን ላያውቁ ይችላሉ" ይላሉ።

የሚመለከቱት ሰዎች ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ወይም የሳይበር ወንጀል መከታተያ ላይ ሪፖርት ለማድረግ ምንም ማበረታቻ አልነበራቸውም ሲሉ ያክላሉ።

ፖሊስ በቦራ ላይ ፆታዊ ትንኮሳን፣ የጸያፍ ነገሮችን ሥርጭት፣ ስም ማጥፋትን፣ ስምን ለመጉዳት ሐሰተኛ ማጭበርበር፣ በሰው ማጭበርበር እና የሳይበር ወንጀልን የሚመለከቱ የሕግ ክፍሎችን ጠቅሶ አቤቱታ አቅርቧል።

ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣን ያስከተለው ጉዳይም አንዳንዶች መሰል ሁኔታዎችን ለመፍታት ጠንከር ያሉ ሕጎችን ሲፈልጉ ተመልክቷል።

የኤአይ ባለሙያዋ እና ጠበቃዋ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን የተመለከቱ በቂ ሕጎች እንዳሉ ታምናለች።

ነገር ግን ከኤአይ ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት ለአዳዲስ ሕጎች ወሰን አለ ወይ የሚለው መታየት አለበት።

"ነገር ግን 'ዲፕ ፌክ' መጥፎ እንዳልሆኑ እና ሕጎች በጥንቃቄ መቀረጽ እንዳለባቸው ማስታወስ አለብን ምክንያቱም [ሕጎች] የመናገር ነፃነትን ለማፈን ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።"