የገዛ ልጆቹን እንደገደለ በቻትጂፒቲ በሐሰት የተነገረው ግለሰብ ቅሬታ አቀረበ

አርቬ ሃልማር ሆልማን

የፎቶው ባለመብት, Arve Hjalmar Holmen

ሁለት ልጆቹን እንደገደለ እና ለ21 ዓመታት እንደታሰረ በቻትጂፒቲ በሐሰት የተነገረው የኖርዌይ ዜጋ ቅሬታውን አቀረበ።

አርቬ ሃልማር ሆልማን የተባለው ግለሰብ የኖርዌይን የመረጃ ጥበቃ ባለስልጣን ዘንድ ቀርቦ የቻትቦቱ ባለቤት የሆነው ኦፕንኤአይ እንዲቀጣ ጠይቋል።

ይህም የሰው ሠራሽ አስተውሎቶች (ኤአይ) መረጃን ፈጥረው እንደ እውነት የሚያቀርቡበት "ቅዠት (ሃሉሲኔሽን)" እየተባለ የሚጠራው ምሳሌ ነው።

ሆልማን እንዳለው ከሆነ ይህ ቅዠት በጣም ጎጂ ነው።

"አንዳንዶች እሳት በሌለበት ጭስ አይኖርም ብለው እንደሚሉት፤ አንድ ሰው ይህንን አንብቦ እውነት ነው ብሎ ማመኑ በጣም ነው የሚያስፈራኝ" ብሏል።

ኦፕንኤአይ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቦለታል።

ሆልማን የውሸት መረጃውን ያገኘው ቻትጂፒትን ተጠቅሞ "አርቬ ሃልማር ሆልማን ማነው?" የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ነው።

ከቻትጂፒቲ በሰጠው ምላሽ፡ "አርቬ ሃልማር ሆልማን በመጥፎ ጉዳይ ርዕስ መሆን የቻለ የኖርዌይ ግለሰብ ነው።"

"እአአ ታህሳስ 2020 ትሮንዳሂም ኖርዌይ በሚገኘው ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኝ ኩሬ ውስጥ ሞተው የተገኙ የ7 እና የ10 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበር።"

ሆልማን እንዳለው ከሆነ ቻትቦቱ የልጆቹን የዕድሜ ልዩነት በትክክል እንዳገኘ በመግለጽ፤ ስለ እሱ ትክክለኛ መረጃ እንዳለው ጠቁሟል።

በግለሰቡ ስም ቅሬታውን ያቀረበው የዲጂታል መብት ተሟጋች ቡድኑ ኖይብ በበኩሉ ቻትጂፒቲ የሰጠው መልስ ስሙን ያጠፋ እና በግላዊ መረጃ ትክክለኛነት ዙሪያ የአውሮፓ የመረጃ ጥበቃ ህጎችን የጣሰ ነው ብሏል።

ኖይብ በቅሬታው ላይ ሆልማን "በምንም አይነት ወንጀል ተከሶ እና ተፈርዶበት የማያውቅ ነው" ብሏል።

ቻትጂፒቲ በሚሰጠው ማሳሳቢያ ላይ "ቻትጂፒቲ ሊሳሳት ይችላል። ጠቃሚ መረጃዎችን አረጋግጥ" ይላል።

ኖይብ ግን ይህ በቂ አይደለም ይላል።

"የሐሰት መረጃ ካሰራጨህ በኋላ መጨረሻ ላይ የተናገርከው ሁሉ እውነት ላይሆን ይችላል ብለህ ትንሽ ማስተባበያ መጨመር አትችልም" ብሏል የኖይብ ጠበቃ የሆነው ዮአኪም ሶደርበርግ።

ቻትጂፒቲ ለሆልማን የሰጠው ምላሽ

የፎቶው ባለመብት, Noyb European Center for Digital Rights

ወደ ጄኔሬቲቭ ኤአይ ሲመጣ የኮምፒዩተር ሳይንቲስቶች ለመፍታት ከሚሞክሯቸው ዋና ዋና ችግሮች አንዱ ቅዠት (ሃሉሲኔሽን) ነው።

ይህም ሚሆነው ቻትቦቶች የውሸት መረጃን እንደ እውነታ ሲያቀርቡ ነው።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ አፕል ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የአፕል ኢንተለጀንስ የዜና መተግበሪያው የውሸት አርዕስተ ዜናዎችን አዘጋጅቶ እንደ እውነተኛ ዜና ካቀረበ በኋላ አስወግዶታል።

የጎግል ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሆነው ጀሚኒ ቅዠት ውስጥ ወድቋል። ባለፈው ዓመት ሙጫ በመጠቀም ቺዝን ከፒዛ ጋር እንዲጣበቅ ሃሳብ ከማቅረብ ባለፈ፣ ሰዎች በቀን አንድ ድንጋይ እንዲበሉ ጂኦሎጂስቶች ይመክራሉ ብሏል።

በትልልቅ የቋንቋ ሞዴሎች ውስጥ እነዚህን ቅዠቶች የሚያስከትለው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

"ይህ ምርምር የሚካሄድበት ጉዳይ ነው። እነዚህን የአስተሳሰብ ሰንሰለቶች እንዴት እንገነባለን? በትልቁ የቋንቋ ሞዴል ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ እንዴት እናብራራለን?" ሲሉ በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የኤአይ ፕሮፌሰር የሆኑት ሳይመን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ሞዴሎች ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ለሚሠሩ ሰዎችም ሊተገበር ይችላል ብለዋል።

"በእነዚህ ስርአቶች ላይ ብዙ ጊዜ የሚሳተፉ ቢሆንም እንዴት እንደሚሠሩ፣ ለምን ይህን የተለየ መረጃ ይዘው እንደሚመጡ አያውቁም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቻትጂፒቲ እአአ ነሀሴ 2024 ላይ የሆልምስ ፍለጋ ተከትሎ ሞዴሉን በመቀየር አሁን ተዛማጅ መረጃዎችን ሲፈልግ ወቅታዊ የዜና ዘገባዎችን ይዳስሳል።

ኖይብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሆልማን በዕለቱ በርካታ ጥያቄዎችን ማቅረቡን እና የወንድሙን ስም በቻትቦቱ ላይ ሲያሰፍር "የተሳሳቱ ብዙ የተለያዩ ታሪኮችን" አግኝቷል።