ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን እና ሩሲያ ሁለቱም ሊሲቻንስክ ከተማ በእጃችን ናት እያሉ ነው
በዩክሬን ምሥራቃዊ ቁልፍ ከተማ ሊሲቻንስክ ከፍተኛ ዉጊያ እየተደረገ ነው።
ሁለቱም ተዋጊዎች ከተማዋ በኛ እጅ ናት እያሉ ነው።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ወታደሮቼ በከፍተኛ ሁኔታ ከሩሲያ ከባድ መሣሪያ እየተተኮሰባቸው ነው፤ ነገር ግን አሁንም ከተማዋ ከእጃችን አልወጣችም ይላሉ።
በሩሲያ የሚደገፉት ተገንጣዮች ግን ሊሲቻንስክ ሰተት ብለን ገብተን በማዕከላዊ የከተማዋ እምብርት ተደላድለን እንገኛለን ብለዋል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ተገንጣዮቹና የራሺያ ወታደሮች በከተማዋ ጎዳናዎች በወታደራዊ መስመር ሲንቀሳቀሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል አጋርተዋል።
ከዚህ ባሻገር ሌሎች የሩሲያ ሚዲያዎች በከተማዋ የአስተዳደር ሕንጻ የዩክሬን ባንዲራ ወርዶ የሩሲያ ባንዲራ ሲሰቀል ምሥል አሳይተዋል።
ይሁንና እነዚህ ምሥሎች ከገለልተኛ ወገን ሐቀኝነታቸው አልተረጋገጠም።
ይቺ ምሥራቃዊ የዩክሬን ከተማ በሉሃንስክ የመጨረሻዋ በዩክሬን እጅ የነበረች ከተማ ናት። ሉሃንስክ የሰፊው ዶንባስ አውራጃ አካል ነው።
ባለፈው ወር የሩሲያ ወታደሮች በቅርብ የምትገኘውን ሰቭሮዴኒስክ ከተማን መቆጣጠራቸው አይዘነጋም።
የሉሃንስክ ክልል ገዥ ሰሪህ ሐይዳ በሊስቻንስክ ከተማ የሚዘንበው ጥቃት ጋብ እንዳላለ ተናግረው ወታደሮች ከሁሉም አቅጣጫ ከበባ ውስጥ እንደገቡ አምነዋል።
የሉሃንስክ ሕዝብ ሪፐብሊክ የሚባሉት ተገንጣዮች ወኪልና በሩሲያ አምሳደር ሮዲዮ ሚሮሽኒክ በበኩላቸው ሊስቻንስክ በሩሲያ ቁጥጥር ስለመሆኑ ካረጋገጡ በኋላ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ነጻ አልወጣም ብለዋል።
የቼቺኒያ ወታደሮች ከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የሚያሳዩ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ታይተዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ዕለት ጀምሮ 12 ሚሊዮን ሕዝብ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለ ሲሆን በዐሥር ሺህ የሚቆጠሩ የዩክሬን ወታደሮችም ተገድለዋል። በሩሲያ በኩል የሟቾች ቁጥር አልተገለጸም።
በተያያዘ ዜና ማምሻውን የባቡር መስመር ተከትሎ የሚሄድ የኤሌክትሪክ መስመር በሰሜን ካርኪቭ ከተማ ለከፍተኛ ጥቃት ተጋልጧል። እስከአሁን በጥቃቱ የሞተ ሰው አልተዘገበም።
በተመሳሳይ የደቡባዊ ከተማ ማይኮሌቭ ከፍተኛ ፍንዳታዎች እየተሰሙ ነው። ማይኮሌቭ ወደ ኦዴሳ ወደብ የሚወስድ ቁልፍ ከተማ ነው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ወሰድኩት ባለው ተከታታይ የአየር ጥቃት አምስት የዩክሬን ዕዞችን ከጥቅም ውጭ አድርጊያለሁ ብሏል።
የመሣሪያ ማከማቻ መጋዘንም እንዳወደመም ገልጧል። ይሁንና ይህም ለጊዜው በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።
ከትናንት በስቲያ በኦዴሳ አቅራቢያ ከሩሲያ በተወነጨፈ የሚሳኤል ጥቃት 20 ሰዎች በቤታቸው ሳሉ መገደላቸው አይዘነጋም።