በካናዳ በፈቃዳቸው በሕክምና ድጋፍ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ሪፖርት አመለከተ

በማይድን ህመም ተይዘው በሕክምና ድጋፍ እንዲሞቱ የሚደረጉ ካናዳውያን ብዛት ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት ማደጉን ተገለጸ።

ይህ ዩቲኔዢያ በመባል የሚታወቀው 'የርህራሄ ግድያ'፤ በስቃይ ውስጥ ያሉ እና የማይድኑ ሰዎች በፈቃዳቸው ወይም በቤተሰቦቻቸው ይሁንታ በሕክምና ድጋፍ እስትንፋሳቸው እንዲያበቃ የሚደረግበት መንገድ ነው።

ካናዳ፤ በአውሮፓውያኑ 2016 በድጋፍ የሚፈጸም ሞትን ሕጋዊ ካደረገች በኋላ በየዓመቱ ሪፖርት የምታወጣ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት በዚህ መንገድ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ መሆኑ ተመላክቷል።

ባለፈው ዓመት ወደ 15,300 የሚጠጉ ሰዎች በሕክምና ድጋፍ ያረፉ ሲሆን ይህም በአገሪቱ ውስጥ ከተመዘገበው ሞት 4.7 በመቶው ነው። የካናዳ ሕግ አውጪዎች ይህ በራስ ፈቃድ የሚፈጸመው ሞት በ2027 የአእምሮ ህመም ያለባቸውን ሰዎች ጭምር እንዲያካትት ጥረት እያደረጉ ነው።

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በሕክምና ድጋፍ መሞትን የሚፈቅደውን ሕግን ካወጡ ጥቂት አገራት መካከል ካናዳ አንዷ ካናዳ ስትሆን፤ አውስትራሊያ፣ ኒው ዚላንድ፣ ስፔን እና ኦስትሪያም ተመሳሳይ ህግ አውጥተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2023 በሕክምና ድጋፍ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በ16 በመቶ ገደማ መጨመሩን የካናዳ ጤና ጉዳዮች ያወጣው ሪፖርት አሳይቷል። ነገር ግን ይህ አሃዝ በቀደሙት ዓመታት ከነበረው አማካይ የ31 በመቶ ጭማሪ ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ሪፖርቱ መጠኑ እንዲቀንስ ያደረገው ምን እንደሆነ ለማወቅ "በጣም ገና" መሆኑን ጨምሮ አስጠንቅቋል።

በሕክምና ድጋፍ ለመሞት የጠየቁት በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መጠን፣ 96 በመቶ አካባቢ የሚሆኑት ሊገመት በሚችል ተፈጥሯዊ ሁኔታ ለሞት የተቃረቡ ናቸው። ቀሪዎቹ 4 በመቶዎች ደግሞ የረጅም ጊዜ ሥር የሰደደ ህመም ያለባቸው ነገር ግን ሞታቸው የማይጠበቅ ናቸው።

በፈቃዳቸው ድጋፍ አግኝተው ለመሞት የፈለጉት ሰዎች አማካይ ዕድሜ 77 አካባቢ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹን እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሳቸው የጤና እክል ካንሰር ነው።

ጥናቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕክምና ድጋፍ የሞቱ ሰዎችን ዘር ለይቷል። በዚህም ብዙኃኑ ማለትም 96 በመቶ የሚሆኑት ነጮች ሲሆኑ፣ 70 በመቶው ከካናዳ ሕዝብ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። ይህ የሰፋ ልዩነት እንዴት እንደተፈጠረ ግን ግልጽ አይደለም።

በሪፖርቱ ላይ በሁለተኛነት የተጠቀሱት ምሥራቅ እስያውያን (1.8%) ሲሆን፣ እነሱም ከአጠቃላይ ካናዳውያን 5.7 በመቶውን የሚሸፍኑ ናቸው።

ምንም እንኳን ግዛቱ ከካናዳ ሕዝብ 22 በመቶውን ብቻ የሚይዝ ቢሆንም፣ በሕክምና ድጋፍ የሚፈጸም ሞት በኩቤክ ውስጥ ከፍተኛውን መጠን ይዞ ቀጥሏል። ይህም ከሁሉም የርህራሄ ሞት ውስጥ 37 በመቶ ያህል ነው።

በዚህም የተነሳ የኩቤክ ግዛት መንግሥት በሕክምና ድጋፍ የሚፈጸም ሞት ለምን ከፍተኛ ሊሆን እንደቻለ ለመመርመር በዚህ ዓመት መጀመሪያ ጥናት ማድረግ ጀምሯል።

በካናዳ ውስጥ በሕክምና ድጋፍ የሚፈጸሙ ሟቾች ቁጥር እያደገ ቢሄድም ከቁጥር አንጻር አገሪቱ አሁንም ከኔዘርላንድስ ኋላ ትገኛለች። በኔዘርላንድስ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው አጠቃላይ ሞት ውስጥ የርህራሄ ግድያው 5 በመቶውን ይይዛል።

የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባላት ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ በእንግሊዝ እና በዌልስ ውስጥ በጠና የታመሙ ጎልማሶች በሕክምና ድጋፍ የመሞት መብት የሚሰጠውን ተመሳሳይ ሕግ ለማጽደቅ ድምጽ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን ይህ ሕግ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለወራት ተጨማሪ ክትትል ይጠብቀዋል።

የብሪታንያ የፓርላማ አባላት በሕጉ ዙሪያ ባደረጉት ክርክር ወቅት ካናዳ በምሳሌነት ተነስታ ሕጓ ጥበቃ እንደሚጎድለው ለማስጠንቀቂያነት ቀርቦ ነበር።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ሁሉ ካናዳ መጀመሪያ ላይ በፍላጎት የሚፈጸመውን ሞት ሕጋዊ ያደረገችው "በአሳማኝ ሁኔታ" የማይቀር ሞት ለሚጠብቃቸው ሰዎች ብቻ ነበር።

ቢሆንም ግን ካናዳ በ2021 ምርመራ ያልተደረገላቸው ነገር ግን ሥር በሰደደ እና በእየተባባሰ በሚሄድ ህመም የተያዙ ሰዎች በሕክምና ድጋፍ ለመሞት ፍላጎት ካላቸው እንዲፈቀድ አድርጋለች።

በተጨማሪም ይህ መብት የአእምሮ ህመም ላለባቸው ሰዎች ለመፍቀድ እየታሰበ ነው።

ነገር ግን ሥርዓቱ እንዲህ ያለውን አገልግሎቱን የማስፋት ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆን እና አለመሆኑ የጤና እንክብካቤ አቅርቦትን በሚቆጣጠሩት የካናዳ ግዛቶች ላይ ስጋት በመፍጠሩ እንዲዘገይ ተደርጓል።

ይህ የመንግሥት በፈቃድ መሞትን የማስፋፋት ውሳኔ ከተለያዩ ወገኖች ድጋፍ እና ተቃውሞ እየገጠመው ነው።

ካርዱስ የተባለው የክርስቲያን ምሁራን ቡድን የቅርብ ጊዜ አሃዞች ጠቅሶ ሁኔታው "አሳሳቢ ነው" በማለት ካናዳ በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ በሕክምና ድጋፍ በብዛት ሞት ከሚፈጸምባቸው አገራት አንዷ ሆናለች ብሏል።

በጥቅምት ወር የወጣ ሪፖርት፤ በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ግዛት በሆነችው በኦንታሪዮ ውስጥ ሰዎች በተፈጥሯዊ ሁኔታ ለሞት በማይቃረቡበት ክስተቶች ጭምር በሕክምና ድጋፍ እንዲሞቱ መፈቀዱን ማሳየቱ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።

አንዱ ምሳሌም በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ድባቴ እና ራስን የማጥፋት ፍላጎት እንዲሁም ኬሚካሎች ለህመም የሚዳርጓት አንዲት ሴትን ያጠቃልላል።

ግለሰቧ በሕክምና ድጋፍ የመሞት ጥያቄዋ ተቀባይነት ያገኘው ለጤና ሁኔታዋ ተስማሚ የሆነ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ያቀረበችው ጥያቄ ሳይሳካ በመቅረቱ ነበር።

በተጨማሪም የካናዳ የዜና ማሰራጫዎች አካል ጉዳተኞች በመኖሪያ ቤት ወይም በአካል ጉዳተኝነት ጥቅማጥቅሞች እጦት ምክንያት በሕክምና ድጋፍ ለመሞት ያሰቡባቸውን አጋጣሚዎች መኖራቸውን ዘግበዋል።