ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ ውስጥ በሁለት ሳምንት ልዩነት ሌላ ግዙፍ ዝርፊያ ተፈጸመ
የፈረንሳይ ፖሊስ፤ 13.8 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት በመዝረፍ የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦችን በሊዮን ከተማ አቅራቢያ በቁጥጥር ሥር አዋለ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በፓሪስ ከተማ ከሚገኘው ሉቭ ሙዚየም 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ እጅግ ውድ ጌጣጌጦች የተዘረፉባት ፈረንሳይ፤ ሌላ ዝርፊያ ያስተናገደችው ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ዕለት ነው።
በዕለቱ ሦስት ዘራፊዎች ፈንጂ በመጠቀም የውድ ብረቶች ማጣሪያ ድርጅትን ሰብረው የገቡ ሲሆን በአብዛኛው ወርቅ የሆነ እና 13.8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት ሰርቀዋል።
ዘራፊዎቹን ለመያዝ አንድ ላይ የነበረው አገሪቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን እና የተሰረቁትን ንብረቶች ማስመለሱን አስታውቋል።
ሰሞነኛው ዘረፋ የተሰማው ከሁለት ሳምንት በፊት ከሉቭ ሙዚየም ውድ ጌጣጌጦችን በመስረቅ የተጠረጠሩ አምስት ተጨማሪ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይፋ በተደረገበት ጊዜ ነው።
በሊዮን ከተማ የተዘረፈው ተቋም አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የለቀቋቸው የቪዲዮ ምሥሎች ሁለት ሰዎች ነጭ መኪና አጠገብ ቆመው ያሳያሉ። አንድ ግለሰብ ከኩባንያው አጥር አጠገብ መሰላል ካስቀመጠ በኋላ ሲንጠላጠል ቪዲዮው አሳይቷል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለቀቀ ሌላ ቪዲዮ ላይ መሣሪያ የያዘ ግለሰብ የመኪናውን ኋላ በር ሲከፍት ታይቷል። ሌላ ግለሰብ ደግሞ በእቃዎች የተሞላ ቦርሳ ወደ መኪናው ሲጭን ተቀርጿል።
ስሟ ያልተጠቀሰ አንዲት ጎረቤት፤ ትልቅ ፍንዳታ እንደሰማች መናገሯን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል። ነዋሪዋ "በጣም የሚያስገርም ነበር" ብላለች።
የኤኤፍፒ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ዘረፋው የተፈጸመበት 'ፑህኩሪ ላብራቶሪስ' አምስት ሠራተኞች በፍንዳታው መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ከዘረፋው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ውስጥ አንዷ ሴት እንደሆነች ተገልጿል። ጠመንጃ እና ፈንጂ እንደተያዘም ፖሊስ አስታውቋል።
በሌላ በኩል በሉቭ ሙዚየም ዘረፋ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ብዛት ሰባት ደርሷል።
ጥቅምት 9/2018 ዓ. ም. የተካሄደውን ዝርፊያ ያከናኑት ግለሰቦች መኪና ላይ የተገጠመ መሰላልን ተጠቅመው 'ጋላሪ ኦፍ አፖሎ' ወደተሰኘው ክፍል በመግባት በቀን ሰርቀው ወጥተዋል።
የንጉሣውያን ጌጣጌጦች የተቀመጡባቸውን መሣያዎች የሰበሩት እነዚህ ግለሰቦች፤ 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት ዘርፈዋል።
ከተያዙት ሰዎች መካከል ሦስቱ ዘራፊዎች እንደሆኑ ያስታወቀው ፖሊስ፤ አራተኛውን ግለሰብ ለመያዝ አሁንም ክትትል ላይ መሆኑን ገልጿል።