ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ዙርያ ከፑቲን ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር አገራቸው በዩክሬን ጦርነት ዙርያ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ያደረጉትን ውይይት "ጥሩ እና ውጤታማ" ሲሉ አደነቁ።

ይህ የሆነው ፑቲን እና የአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በሞስኮ ከተገናኙ በኋላ፣ ጽህፈት ቤታቸው በሰላም ሂደቱ ላይ የአሜሪካን "ግራ ቀኙን ያየ እና ተስፋ የተሞላበት" ሃሳብ እንደሚደግፉ ካስታወቀ በኋላ ነው።

ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ውይይቱ "ይህ አሰቃቂ እና ደም አፋሳሽ ጦርነት በመጨረሻ እንዲያበቃ የሚያደርግ በጣም ጥሩ ዕድል ነው" ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ግን ፑቲንን ጦርነቱን ለመቀጠል ንግግሮችን ለማጓተት ሞክረዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።

ሰር ኬር ስታርመር በበኩላቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት የተኩስ አቁም ሀሳቦችን በማንሳት "ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ" ሊፈቀድላቸው እንደማይችል ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዩክሬን በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት የተቀበለች ሲሆን ፣ሩሲያ ግን እስካሁን አልተስማማችም።

ሐሙስ ዕለት ፑቲን የተኩስ አቁም ሃሳብ "ትክክል ነው፤ እኛም እንደግፋለን… ግን ልዩነቶች አሉ" ካሉ በርካታ ጠንካራ ቅድመ ሁኔታዎቸን አስቀምጠዋል።

በዚህ የፕሬዝዳንቱ ቅድመ ሁኔታ የተበሳጩት ዜሌንስኪ "ሸፍጥ የተሞላበት" በሚል ኮንነዋቸዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት አርብ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ በተለጠፉት ተከታታይ ጽሑፍ ላይ ትችታቸውን በመቀጠል "ፑቲን ከዚህ ጦርነት መውጣት አይፈልግም፤ ምክንያቱም ያ ባዶውን ያስቀረዋል።

"ለዚህም ነው ገና ከጅምሩ፣የተኩስ አቁም ከመደረጉ በፊት እንኳ እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና ተቀባይነት የሌላቸው ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ዲፕሎማሲውን ለማበላሸት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ያለው" ብለዋል።

ፑቲን ሁሉንም አካላት "ማለቂያ ወደሌለው ውይይቶች ይጎትታል... ወታደሮቹ ዜጎቻችንን እየገደሉ ቀናትን፣ ሳምንታትን እና ወራትን በከንቱ ንግግሮች ያባክናል" ሲሉ ጽፈዋል።

"ፑቲን ያቀረቡት እያንዳንዱ ቅድመ ሁኔታ ማንኛውንም ዲፕሎማሲ ለመግታት የሚደረግ ሙከራ ብቻ ነው። ሩሲያ የምትሰራው በዚህ መንገድ ነው። እናም ደግሞ ስለዚህ ጉዳይ አስቀድመን አስጠንቅቀናል።"

የዩናይትድ ኪንግደም ጠ/ሚ ሰር ኪር የትራምፕን የተኩስ አቁም ሃሳብ ክሬምሊን "ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱ" ፑቲን "ለሰላም ግድ እንደሌለው" ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም "ሩሲያ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ከመጣች የተኩስ አቁም ስምምነቱ የምር እና ለዘላቂ ሰላም መሆኑን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆን አለብን" ብለዋል ።

"ይህ ካልሆነ ግን ጦርነቱ እንዲያበቃ በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር እያንዳንዱን ብሎን ማጠባበቅ አለብን።"

ቅዳሜ ሰር ኬር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በለንደን በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ የቀረበውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተወያይቶ ከስምምነት ለመድረስ ከ25 መሪዎች ጋር የቪዲዮ ስብሰባ ያደርጋሉ።

በዚህ ስብሰባ ላይ ሰር ኬር "የፈቃደኞች ጥምረት" ሲሉ የሚጠሩት የአውሮፓውያኑ ሀሳብ፣ አሜሪካ ያቀረበችው የተኩስ አቁም ሥራ ላይ ከዋለ የወደፊት የሩስያ ጥቃትን ለመከላከል ይሰራል የሚለው ላይ እንደሚወያዩ ተሰምቷል።

ዜሌንስኪ አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "በሩሲያ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁሉ፣ በተለይም ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሊያግዙ የሚችሉ ጠንካራ እርምጃዎችን ቢወስዱ መልካም ነው" ሲሉ አሳስበዋል።

አክለውም ምክንያቱም ፑቲን ጦርነቱን በራሱ ፈቃድ አያቆመውም ብለዋል።

"ፑቲን በጦር ሜዳ ላይ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ... ስለተጎዱት" እንዲሁም "ኢኮኖሚው ስላለበት ትክክለኛ ቁመና እየዋሸ ነው" ፑቲን "ዲፕሎማሲው እንዳይሳካ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን በዋይት ሐውስ እምነት ሁለቱ ወገኖች "በፍፁም ለሰላም የዚህ ያህል ቅርብ ሆነው አያውቁም።"

የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ሐሙስ ዕለት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በሞስኮ በፑቲን እና በዊትኮፍ መካከል የተደረገው ውይይት "አመርቂ ነበር" ብለዋል።

ትራምፕ "በፑቲን እና ሩሲያውያን ላይ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉ ግፊት አድርገዋል" ብላለች።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፋቸው ላይም ፑቲን በሩሲያ ወታደሮች የተከበቡትን የዩክሬን ወታደሮች ሕይወት እንዲታደጉ የጠየቁ ሲሆን፣ ያ ባይሆን ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያልታየ "አሰቃቂ እልቂት" ይሆናል ብለዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የተሰማው ሩሲያ ባለፈው ዓመት በዩክሬን የተያዘውን ግዛቷን ለማስመለስ ጥረቷን አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት፣ በኩርስክ የሚገኙት የዩክሬን ወታደሮች "መነጠላቸውን" እና ለቅቀው ለመውጣት እየሞከሩ መሆኑን ፑቲን ሐሙስ ዕለት ከገለጹ በኋላ ነው።

ነገር ግን አርብ እለት የዩክሬን የጦር ኃይሎች ጄነራል ባልደረባ ወታደሮቻቸው ተከብበዋል መባሉን "ውሸት እና ፈጠራ" ሲሉ አስተባብለዋል።

በመግለጫቸው የዩክሬን ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው ወደ ተሻለ የመከላከያ ስፍራ " ውጤታማ በሆነ መልኩ መሰባሰባቸውን" እና የማጥቃት እርምጃው መቀጠሉን ገልፀዋል።

"በእኛን ክፍል የመከበብ ስጋት የለም" ብለዋል።

ፑቲን ለትራምፕ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ በኩርስክ የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች መሳሪያቸውን አስቀምጠው እጃቸውን ከሰጡ "በዓለም አቀፍ እና ከሩሲያ ፌዴሬሽን ሕጎች ጋር በተጣጣመ መልኩ በክብር" እንደሚስተናገዱ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቡድን 7 አባላት በኩቤክ የተገናኙ ሲሆን የአስተናጋጇ የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ሁሉም አባላት በዩክሬናውያን ተቀባይነት ያገኘውን እና በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት መደገፋቸውን ተናግረዋል።

"አሁን የሩስያን ምላሽ እየተመለከትን ነው፤ ስለዚህ በመጨረሻ ዩክሬንን በሚመለከት ኳሱ በሩሲያ ሜዳ ውስጥ ነው።"

በስብሰባው ላይ የተገኙት የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በበኩላቸው የቡድን ሰባት አባል አገራት "ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ" የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከስብሰባው በኋላ መሪዎቹ በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በተናገሩት መሠረት አገራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን እንደማትወስን ገልጸው "ይህን ጦርነት ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ድርድር ነው" ብለዋል።