ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ተሾሙ
ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ የፌደራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ሆነው የሰሩት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው እንደተሾሙ ተገለጸ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ኃላፊነታቸው በትናንናው ዕለት መግለጫ ሲሰጡ የነበሩትን ዶ/ር ለገሰን ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አድርገው መሾማቸው የተገለጸው ምሽት ማክሰኞ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም.
ዶ/ር ለገሰ አሁን ወደተነሱበት ኃላፊነት የመጡት ከስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ በኋላ በመስከረም 2014 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት መመስረቱን ተከትሎ ነበር።
ከዚያ አስቀድሞ ፈርሶ የቆየውን የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ኃላፊነት ቦታ በድጋሚ "የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት" በሚል የተቋቋመው አዲሱ መንግሥት ሲመሰረት ነበር።
ዶ/ር ለገሰ በመንግስት ምስረታው እንደ አዲስ የተቋቋመውን መስሪያ ቤት እንዲመሩ ከመሾማቸው አስቀድሞ በነበሩት ዓመታት በትምህርት ምክንያት ኃላፊነት ላይ አልነበሩም።
የቀድሞው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ዶ/ር ለገሰ፤ በትምህርት ምክንያት ከፓርቲ ኃላፊነት የተሰናበቱት መስከረም 2011 ዓ.ም. ነበር።
የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከተመለሱ በኋላ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ትናንት ምሽት ዲፕሎማሲያዊ ሹመት እንደተሰጣቸው ይፋ እስከተደረገበት ትናንት ምሽት ድረስም በዚህ ኃላፊነት ላይ ቆይተዋል።
ዶ/ር ለገሰ ትናንት እኩለ ቀን ገደማ ላይ የፌደራል መንግስት ጷጉሜን ለማክበር ለቀናቱ የተሰጧቸውን ስያሜዎች በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።
ትናንት ምሽት የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ከፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የተላከላቸውን መግለጫ በመጥቀስ የዶ/ር ለገሰን ሹመት ቢዘግቡም የተሾሙበት ትክክለኛ ድፕሎማሲያዊ ተልዕኮ በግልጽ አልተጠቀሰም።
በኃላፊነት የቆዩበት የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊነት ላይ አዲስ አመራር ስለመሾሙን እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
የፌደራል መንግሥት ካቢኔ አባላት ዲፕሎማሲያዊ ኃላፊነት ሲያገኙ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ ሁለተኛው ነው።
የቀድሞው የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በዓለም የንግድ ድርጅት የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ከአንድ ወር በፊት ሐምሌ መጨረሻ ላይ ነበር።
በምትኩም አቶ አዲሱ አረጋ የግብርና ሚኒስትር ሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደተሾሙ አይዘነጋም።