ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድን ስምምነት ተከትሎ ሃገራትና አህጉራት ምን አሉ?
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ተከትሎ ሃገራት እና የአህጉር ኅብረቶች አቋማቸውን በመግለጥ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረሟ ይታወሳል።
ይህን ስምምነት ተከትሎ አስቸኳይ ስብሰባ የጠራችው ሶማሊያ ስምምነቱ “ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው” ብላለች።
የአፍሪካ ኅብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ፤ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የግዴታ ተፈፀማኒት የሌለውን የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙት አዲስ አበባ ላይ በተካሄድ ሥነ-ሥርዓት ነው።
በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ወደብ 20 ኪሎ ሜትር ገደማ ወደብ ታገኛለች። በምትኩ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አሊያም ከኢትዮ ቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ እንደምታገኝ መንግሥት ገልጧል።
በተባበሩት መንግሥታትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ዕውቅና ያልተሰጣት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ዕውቅና ልታገኝ እንደምትችል ቢጠቆምም እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ሶማሊላንድ እንደ አንድ ክፍሏ የምትቆጥረው ሶማሊያ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት በመቃወም አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ ጠርታለች።
ይህን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከግብጽ ፕሬዝዳንት እና ከኳታር መሪ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
ግብፅ እና የአረብ ሊግ
የግብጽ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አሕመድ ፋሚ ሁለቱ መሪዎች በስልክ በነበራቸው ውይይት ላይ አል-ሲሲ “ግብጽ ከሶማሊያ ጎን ለመቆም ያላትን ጠንካራ አቋም” ገልጸዋል ብለዋል።
አሕራም ኦንላይን ይዞ በወጣው ዘገባ ግብፅ “የሶማሊያን ሉዓላዊነት ማክበር” አስፈላጊ ነው ማለቷን አትቷል።
አሕራም የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው "መሰል ድርጊቶች እንዲሁም ከውስጥም ሆነ ከውጭ እየወጡ ያሉ መግለጫዎች” የአፍሪካ ቀንድን አለመረጋጋት ውስጥ ሊከቱት ይችላሉ።"
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ረቡዕ 24/2016 ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት "ማንንም የሚጎዳ አይደለም፤ ሕግም አልተጣሰም" ብሏል።
አሕራም ኦንላይን እንዳስነበበው የግብፅ መግለጫ “በቀጣናው እየተስተዋሉ ያሉ ድርጊቶች በአፍሪካ ሃገራት መካከል ውጥረት የሚፈጥሩ ናቸው” ይላል።
ግብፅ፤ የአፍሪካ ሕብረት መርሆ የሆነው “ማንኛውም ሃገር በየትኛውም ሃገር ውስጣዊ ጉዳይ መግባት የለበትም፤ የሌላኛውን ሃገር ድንበር ሊያከብር ይገባል” የሚለው አንቀፅ ሊከበረ ይገባል ትላለች።
ሞጋዲሹ ከዓመታት አለመግባባት በኋላ በሰሜናዊ የሃገሪቱ አቅጣጫ ካሉ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር ውይይት ለማድረግ ዘግጅት ላይ ባለችበት ወቅት ነው ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ ከስምምነት የደረሱት።
በተያያዘ ዘገባ የአረብ ሊግ ረቡዕ ታኅሣሥ 24 ባወጣው መግለጫ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጋፋን ማንኛውንም ስምምነት “አንቀበልም “ ብሏል።
በተለይ “የሶማሊያ መንግሥት ከሶማሊያ ክልሎች ጋር እያደረገ ያለውን ድርድር አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል” ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብሏል ሊጉ።
የሊጉ ቃል አቀባይ ጋማል ሮሽዲ “መሰል ድርጊቶች ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጥሱ እና የሶማሊያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው” ማለታቸውን መግለጫው አስነብቧል።
ሮሽዲ፤ “ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በወደብ ጉዳይ አብረው ለመሥራት መወሰናቸውን የሶማሊያ ካቢኔ «ተቀባይነት የለውም» ማለቱን የአረብ ሊግ ሙሉ በሙሉ ይደግፈዋል” ማለታቸውን መግለጫው አትቷል።
ቃል አቀባዩ አክለው “ይህ ድርጊት መዘዝ ሊኖረው እንዲሁም አክራሪ ኃይሎች አንዲባዙ ሊያደርግ ምክንያት ሊሆን ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላቸው መግለጫው ጠቁሟል።
የአፍሪካ ኅብረትና ዩናይትድ ስቴትስ
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የገቡትን ስምምነት ተከትሎ መግለጫው ለማውጣት ያልቸኮለው የአፍሪካ ኅብረት ሐሙስ ታኅሣሥ 25 በለቀቀው መግለጫ ሁለቱ ሃገራት “ውጥረታቸውን እንዲያረግቡ” ጥሪ አቅርቧል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት “ሁለት ጎረቤት ሃገራት ሳይታሰብ ሰላማቸውን ወደሚያደፈርስ ድርጊት ከመጓዝ ሊቆጠቡ ይገባል” ማለታቸውን ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ሊቀ-መንበሩ፤ ሁሉም የአፍሪካ ኅብረት ሃገራት የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር እንዳለበት አሳስበው ሁለቱ ሃገራት የአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዳይደፈርስ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በለቀቀው አጠር ያለ መግለጫ ኅብረቱ ሁለቱ ሃገራት ውጥረታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያረግቡ ጥሪ ከማቅረብ ውጭ ጠንከር ያለ አቋም ከመሰንዘር ተቆጥቧል።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ስለተፈጠረው አለመግባባት ጥያቄ የቀረበላቸው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር “ዩናይትድ ስቴትስ በ1960 [በአውሮፓውያኑ] የድንበር ወሰን መሠረት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ታከብራለች” ሲሉ አስተያየት ምላሽ ሰጥተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ የስምምነቱን መፈረም አስመልክቶ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ በሶማሊያ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተሮች መሠረት “የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ጠቃሚ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን” ብሏል።
የሕብረቱ ቃል አቀባይ በኩል ማክሰኞ 23/206 የወጣው መግለጫ “በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋገትን ለማስፈን የሶማሊያ ሉዓላዊነትን ማክበር ቁልፍ ነው” ብሏል።
የምስራቅ አፍሪካ መንግሥታት በይነ መንግሥት [ኢጋድ] ባወጣወ መግለጫ ደግሞ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል "የተፈጠረው አለመግባባት እንዳሳሰበው" ገልጧል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ የሆኑት ወርቅነህ ገበየሁ [ዶ/ር] ሁኔታውን እየተከታተሉት እንዳለና ሁኔታው በቀጣናው መረጋጋት ላይ የሚያመጣውን ጫና እንደሚረዱ መግለጫው ያትታል።
ይህን የኢጋድ ማሳሰቢያ ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ ያወጣ ሲሆን "የሶማሊያ መንግሥት በኢጋድ መግለጫ እንዳልተደሰተ መግለጥ ይወዳል" ብሏል።
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “መግለጫው ለኢትዮጵያ መንግሥት ያደላ እንደሆነ ያምናል። ዋና ፀሐፊው ይቅርታ ጠይቀው መግለጫውን ሰርዘው ትክክለኛ እርምጃ ይወስዳሉ ብለን እናስባለን" ብሏል።